በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ” ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

“በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ” ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

“በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ አሳያለሁ።”—ሚክ. 7:7 NW

1. ትዕግሥት እንድናጣ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?

መሲሐዊው መንግሥት በ1914 ሲቋቋም የሰይጣን ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ጀመሩ። በሰማይ በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ ኢየሱስ ዲያብሎስንና አጋንንቱን ወደ ምድር ጣላቸው። (ራእይ 12:7-9ን አንብብ።) ሰይጣን “ጥቂት ጊዜ እንደቀረው” ያውቃል። (ራእይ 12:12) ይሁን እንጂ ይህ “ጊዜ” ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የዘለቀ በመሆኑ አንዳንዶች የመጨረሻዎቹ ቀኖች እንደረዘሙ ይሰማቸው ይሆናል። ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ ስንጠባበቅ እኛስ ትዕግሥታችን እያለቀ መጥቶ ይሆን?

2. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

2 ትዕግሥት ማጣት የችኮላ እርምጃ እንድንወስድ ሊያደርገን ስለሚችል አደገኛ ነው። ታዲያ በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ይህ የጥናት ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ይህን ዝንባሌ ማዳበር እንድንችል ይረዳናል። (1) በትዕግሥት በመጠበቅ ረገድ ነቢዩ ሚክያስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (2) በትዕግሥት በመጠበቅ ያሳለፍነው ጊዜ ማብቃቱን የሚያመላክቱት ክስተቶች ምንድን ናቸው? (3) ይሖዋ ላሳየው ትዕግሥት ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?

ሚክያስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

3. በሚክያስ ዘመን በእስራኤል የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

3 ሚክያስ 7:2-6ን አንብብ። የይሖዋ ነቢይ የሆነው ሚክያስ እስራኤል ውስጥ የነበረው መንፈሳዊ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሲሄድ የተመለከተ ሲሆን በንጉሥ አካዝ የግዛት ዘመን ሁኔታው የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ሚክያስ ታማኝ ያልሆኑትን እስራኤላውያን ‘ከአሜከላ’ እና ‘ከኩርንችት’ ጋር አመሳስሏቸዋል። አሜከላ ወይም ኩርንችት የረገጠውን ሰው እግር እንደሚያቆስል ሁሉ ምግባረ ብልሹ የሆኑት እስራኤላውያንም ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ሰው ለጉዳት ይዳርጉ ነበር። በወቅቱ የነበረው ሁኔታ እጅግ ከማሽቆልቆሉ የተነሳ በቤተሰብ መካከል ያለ ዝምድና እንኳ  ሳይቀር ተበላሽቶ ነበር። ሚክያስ በራሱ አቅም ሁኔታውን መለወጥ እንደማይችል ስለተገነዘበ የልቡን ስሜት ለይሖዋ አፈሰሰ። ከዚያም አምላክ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በትዕግሥት መጠባበቅ ጀመረ። ሚክያስ ይሖዋ በራሱ ጊዜ ጣልቃ እንደሚገባ ሙሉ እምነት ነበረው።

4. ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል?

4 እንደ ሚክያስ ሁሉ እኛም የምንኖረው ራስ ወዳድ በሆኑ ሰዎች መካከል ነው። ብዙዎች “የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ [እና] ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:2, 3) የሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን የሚማሩ ልጆችና ጎረቤቶቻችን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ የሚያንጸባርቁ መሆናቸው ሕይወታችንን አስጨናቂ ያደርገዋል። ሆኖም አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ከዚህ የባሰ ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ኢየሱስ ተከታዮቹ የቤተሰብ ተቃውሞ እንደሚያጋጥማቸው ተናግሮ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የሚያስተምረው ትምህርት ምን እንደሚያስከትል ለመግለጽ ሚክያስ 7:6 ላይ የሰፈሩትን ዓይነት ቃላት ተጠቅሟል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ እንዲሁም ሙሽሪትን ከአማቷ ለመለያየት ነው። በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ።” (ማቴ. 10:35, 36) እምነታችንን የማይጋሩ የቤተሰባችን አባላት የሚሰነዝሩብንን ፌዝና ተቃውሞ ተቋቁሞ መኖር ምንኛ ከባድ ነው! እንዲህ ዓይነት ፈተና የሚያጋጥመን ከሆነ ለቤተሰብ ተጽዕኖ እጅ አንስጥ። ከዚህ ይልቅ ታማኝነታችንን ጠብቀን እንኑር፤ እንዲሁም ይሖዋ ለችግሩ እልባት እስኪሰጥ ድረስ በትዕግሥት እንጠባበቅ። ይሖዋ እንዲረዳን ሳናሰልስ የምንለምን ከሆነ በጽናት መቀጠል እንድንችል የሚያስፈልገንን ጥንካሬና ጥበብ ይሰጠናል።

5, 6. ይሖዋ ሚክያስን የካሰው እንዴት ነው? ይሁንና ነቢዩ የየትኛውን ትንቢት ፍጻሜ አላየም?

5 ሚክያስ ትዕግሥት በማሳየቱ ይሖዋ ክሶታል። የንጉሥ አካዝንም ሆነ የእሱን ክፉ አገዛዝ ፍጻሜ ለማየት በቅቷል። የአካዝ ልጅ የሆነው ንጉሥ ሕዝቅያስ ዙፋኑን ወርሶ ንጹሑን አምልኮ መልሶ ሲያቋቁም አይቷል። በተጨማሪም ይሖዋ በሚክያስ አማካኝነት በሰማርያ ላይ ያስተላለፈው ፍርድ አሦራውያን በስተ ሰሜን ያለውን የእስራኤልን መንግሥት በወረሩ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል።—ሚክ. 1:6

6 ይሁን እንጂ ሚክያስ በይሖዋ መንፈስ ተመርቶ የተናገራቸው ሁሉም ትንቢቶች ሲፈጸሙ አላየም። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፦ “በመጨረሻው ዘመን፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ፣ ከተራሮች ልቆ ይታያል፤ ከኰረብቶች በላይ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ ‘ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ . . . እንሂድ።’” (ሚክ. 4:1, 2) ሚክያስ የሞተው ይህ ትንቢት ከመፈጸሙ ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር። ያም ሆኖ በዙሪያው ያሉት ሰዎች ምንም አደረጉ ምን እስከ ሞት ድረስ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ለመኖር ቆርጦ ነበር። ሚክያስ “አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን” ሲል ጽፏል። (ሚክ. 4:5) ሚክያስ በአስቸጋሪ ጊዜም እንኳ በትዕግሥት መጠባበቅ የቻለው ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት ስለነበረው ነው። ይህ ታማኝ ነቢይ በይሖዋ ታምኗል።

7, 8. (ሀ) በይሖዋ እንድንተማመን የሚያደርግ ምን ምክንያት አለን? (ለ) ጊዜው በቶሎ እንዳለፈ ሆኖ እንዲሰማን የሚያደርገው ምንድን ነው?

7 እኛስ በይሖዋ ላይ እንዲህ ያለ ትምክህት አለን? በእሱ እንድንተማመን የሚያደርገን አጥጋቢ ምክንያት አለን። የሚክያስ ትንቢት ሲፈጸም በገዛ ዓይናችን አይተናል። “በመጨረሻው ዘመን” ከብሔራት፣ ከነገዶችና ከቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ “ቤተ መቅደስ ተራራ” ጎርፈዋል። እነዚህ የይሖዋ አምላኪዎች በጠላትነት ከሚተያዩ ብሔራት የተውጣጡ ቢሆኑም “ሰይፋቸውን ማረሻ” ለማድረግ የቀጠቀጡ ከመሆኑም ሌላ “የጦርነት ትምህርት አይማሩም።” (ሚክ. 4:3) ሰላማዊ ከሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች መካከል መቆጠር መቻላችን ታላቅ መብት ነው!

8 ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት በቶሎ ቢያጠፋው ደስ እንደሚለን ግልጽ ነው። ይሁንና ጊዜውን በትዕግሥት መጠበቅ እንድንችል ነገሮችን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ማየት ያስፈልገናል። እሱ “በሾመው  ሰው አማካኝነት” ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሰው ዘር ላይ የሚፈርድበት ቀን ቀጥሯል። (ሥራ 17:31) ያ ጊዜ ከመድረሱ በፊት ግን አምላክ ሁሉም ዓይነት ሰዎች “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ፣” ያወቁትን ነገር በተግባር እንዲያውሉ እንዲሁም ለመዳን እንዲበቁ አጋጣሚውን ክፍት አድርጓል። ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል። (1 ጢሞቴዎስ. 2:3, 4ን አንብብ።) ሰዎች ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ በመርዳቱ ሥራ ከተጠመድን የይሖዋ ፍርድ ከመጀመሩ በፊት ያለው ጊዜ በፍጥነት እንዳለፈ ሆኖ ይሰማናል። ወዲያውኑ ብሎም ሳናስበው ጊዜው ይደርሳል። መጨረሻው ሲመጣ መንግሥቱን በመስበኩ ሥራ ተጠምደን በመቆየታችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል!

በትዕግሥት በመጠበቅ ያሳለፍነው ጊዜ ማብቃቱን የሚያመላክቱ ክስተቶች

9-11. አንደኛ ተሰሎንቄ 5:3 ፍጻሜውን አግኝቷል? አብራራ።

9 አንደኛ ተሰሎንቄ 5:1-3ን አንብብ። በቅርቡ ብሔራት “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” ብለው ያውጃሉ። በዚህ አዋጅ እንዳንዘናጋ ‘ነቅተን መኖርና የማመዛዘን ችሎታችንን መጠበቅ’ ያስፈልገናል። (1 ተሰ. 5:6) በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖር እንዲረዳን ይህ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ አዋጅ እንዲታወጅ መንገድ እየጠረጉ ያሉትን ክንውኖች በአጭሩ እንመልከት።

10 ከሁለቱም የዓለም ጦርነቶች በኋላ ብሔራት ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። አንደኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በምድር ላይ ሰላም ያሰፍናል በሚል ተስፋ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተቋቋመ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት በምድር ላይ ሰላም ያሰፍናል የሚል ታላቅ ተስፋ ተጣለበት። የመንግሥትም ሆነ የሃይማኖት መሪዎች እነዚህ ድርጅቶች ለሰው ዘር ሰላም ያመጣሉ የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የተባበሩት መንግሥታት 1986ን ዓለም አቀፍ የሰላም ዓመት ብሎ በመሰየም ጉዳዩ በሰፊው እንዲወራ አድርጎ ነበር። በዚያ ዓመት ከበርካታ አገሮችና ሃይማኖቶች የተሰባሰቡ መሪዎች ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ ጋር በመሆን ስለ ሰላም ለመጸለይ በጣሊያን በምትገኘው የአሲሲ ከተማ ተሰብስበው ነበር።

11 ይሁን እንጂ ሰላምና ደኅንነት ተብሎ የታወጀው ይህ አዋጅም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ አዋጆች በ1 ተሰሎንቄ 5:3 ላይ የተመዘገበው ትንቢት ፍጻሜ አልነበሩም። እንዲህ የምንለው ለምንድን  ነው? “ድንገት ይመጣባቸዋል” የተባለው ጥፋት ገና ያልመጣ በመሆኑ ነው።

12. “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለውን አዋጅ በተመለከተ ምን የምናውቀው ነገር አለ?

12 “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለውን ትልቅ ትርጉም ያዘለ አዋጅ የሚያውጀው ማን ነው? በዚህ ረገድ ሕዝበ ክርስትናም ሆነ የሌሎች ሃይማኖቶች መሪዎች ምን ሚና ይኖራቸዋል? የተለያዩ መንግሥታት መሪዎች ከዚህ አዋጅ ጋር በተያያዘ ተሳትፎ የሚኖራቸው እንዴት ነው? ቅዱሳን መጻሕፍት የሚገልጹልን ነገር የለም። ልፈፋው በምንም መልኩ ይቅረብ ወይም ምንም ያህል አሳማኝ ይሁን፣ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር አዋጁ ከወሬ አያልፍም። ይህ አሮጌ ሥርዓት በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንዳለ ይቀጥላል። ሥርዓቱ ከላይ እስከ ታች በስብሷል፤ ደግሞም አይሻሻልም። ማናችንም ብንሆን ይህን ሰይጣናዊ ፕሮፓጋንዳ አምነን ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን ብንጥስ ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል!

13. መላእክት አውዳሚ ነፋሳቱን አግተው የያዙት ለምንድን ነው?

13 ራእይ 7:1-4ን አንብብ። የ1 ተሰሎንቄ 5:3ን ፍጻሜ እየተጠባበቅን ባለንበት በዚህ ጊዜ ኃያላን መላእክት የታላቁን መከራ አውዳሚ ነፋሳት አግተው ይዘዋል። ምን እየጠበቁ ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ አስቀድሞ መከናወን ያለበትን አንድ ወሳኝ ክስተት ገልጿል፤ የተቀቡት ‘የአምላክ ባሪያዎች’ የመጨረሻው ማኅተም ሊደረግባቸው ይገባል። * የመጨረሻውን ማኅተም የማድረጉ ሥራ ሲጠናቀቅ መላእክቱ አውዳሚ ነፋሳቱን ይለቃሉ። በዚህ ጊዜ ምን ይፈጸማል?

14. የታላቂቱ ባቢሎን ፍጻሜ መቅረቡን የሚጠቁመው ምንድን ነው?

14 የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን የሚገባትን ቅጣት ታገኛለች። ‘ወገኖች፣ ሕዝቦች፣ ብሔራትና ቋንቋዎች’ አመርቂ ድጋፍ ሊሰጧት አይችሉም። አሁንም እንኳ ፍጻሜዋ መቅረቡን የሚጠቁሙ ነገሮች እያየን ነው። (ራእይ 16:12፤ 17:15-18፤ 18:7, 8, 21) እንዲያውም መገናኛ ብዙኃን በሃይማኖትና በሃይማኖት መሪዎች ላይ እየሰነዘሩ ያሉት ትችት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መሄዱ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ድጋፍ እያጣች መሆኑን ያሳያል። ያም ሆኖ የታላቂቱ ባቢሎን መሪዎች ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይደርስባቸው ይሰማቸዋል። ይሁንና እጅግ ተሳስተዋል! “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለውን አዋጅ ተከትሎ በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በሐሰት ሃይማኖት ላይ በድንገት ተነስተው ጠራርገው ያጠፏታል። ከዚህ በኋላ ታላቂቱ ባቢሎን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትጠፋለች! እንዲህ ያሉ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ክንውኖች የሚፈጸሙበትን ጊዜ በትዕግሥት መጠባበቅ ፈጽሞ አያስቆጭም።—ራእይ 18:8, 10

የአምላክን ትዕግሥት እንደምናደንቅ እንዴት ማሳየት እንችላለን?

15. ይሖዋ ቸኩሎ እርምጃ የማይወስደው ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ፣ ሰዎች በስሙ ላይ ነቀፋ ቢከምሩም እርምጃ የሚወስድበት ትክክለኛው ጊዜ እስኪደርስ በትዕግሥት ሲጠብቅ ቆይቷል። ይሖዋ ልበ ቅን ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዳቸውም እንዲጠፉ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9, 10) እኛስ እንዲህ ዓይነት ስሜት አለን? የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት ለትዕግሥቱ ያለንን አድናቆት በሚከተሉት መንገዶች ማሳየት እንችላለን።

16, 17. (ሀ) የቀዘቀዙትን መርዳት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) የቀዘቀዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ መመለሳቸው አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?

16 የቀዘቀዙትን እርዱ። ኢየሱስ ጠፍቶ የነበረ አንድ በግ እንኳ ሲገኝ በሰማይ ታላቅ ደስታ እንደሚሆን ተናግሯል። (ማቴ. 18:14፤ ሉቃስ 15:3-7) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እያገለገሉት ባይሆንም እንኳ ለስሙ ፍቅር እንዳላቸው ላሳዩ ሁሉ በጥልቅ እንደሚያስብ ግልጽ ነው። እንዲህ ያሉ ሰዎች ወደ ጉባኤ እንዲመለሱ ስንረዳ ይሖዋና መላእክት እንዲደሰቱ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።

17 በአሁኑ ጊዜ አምላክን ማገልገል ካቆሙት ሰዎች አንዱ ነህ? ምናልባት በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ስሜትህን ጎድቶት ከይሖዋ ድርጅት ጋር  ያለህን ግንኙነት አቋርጠህ ሊሆን ይችላል። ይህ ከሆነ የተወሰነ ጊዜ አልፎ ሊሆን ስለሚችል ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በአሁኑ ጊዜ ሕይወቴ ከበፊቱ የበለጠ ትርጉም ያለው ሆኗል? ይበልጥ ደስተኛስ ሆኛለሁ? እኔን ያስቀየመኝ ይሖዋ ነው ወይስ ፍጽምና የሚጎድለው ግለሰብ? ይሖዋ አምላክ እኔን የሚጎዳ ነገር አድርጎ ያውቃል?’ እንደ እውነቱ ከሆነ ይሖዋ እስከ ዛሬ ድረስ መልካም ነገር ሲያደርግልን ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችንን ለእሱ ስንወስን የገባነውን ቃል አክብረን እየኖርን ባንሆንም እንኳ እሱ ባዘጋጃቸው መልካም ነገሮች እንድንጠቀም ፈቅዶልናል። (ያዕ. 1:16, 17) ይሁንና በቅርቡ የይሖዋ ቀን ይመጣል። በሰማይ ወደሚኖረው አፍቃሪ አምላካችን እቅፍና ወደ ጉባኤው የምንመለስበት ጊዜ አሁን ነው፤ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ያለ ስጋት የምንኖርበት ቦታ ይህ ብቻ ነው።—ዘዳ. 33:27፤ ዕብ. 10:24, 25

የይሖዋ ሕዝቦች የቀዘቀዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ለመርዳት አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ያደርጋሉ (አንቀጽ 16ንና 17ን ተመልከት)

18. አመራር እየሰጡ ያሉትን መደገፍ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

18 ግንባር ቀደም ሆነው አመራር የሚሰጡትን በታማኝነት ደግፉ። ይሖዋ አፍቃሪ እረኛ እንደመሆኑ መጠን ይመራናል እንዲሁም ይጠብቀናል። ልጁን በመንጋው ላይ የእረኞች አለቃ አድርጎ ሾሞታል። (1 ጴጥ. 5:4) ከ100,000 በላይ በሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ለአምላክ በጎች በግለሰብ ደረጃ እረኝነት ያደርጋሉ። (ሥራ 20:28) አመራር እንዲሰጡ የተሾሙትን ወንድሞች በታማኝነት ስንደግፍ ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉልን ነገር ሁሉ ያለንን አድናቆት እናሳያለን።

19. ግንባር መፍጠር የምንችለው እንዴት ነው?

19 እርስ በርስ ተቀራረቡ። ይህ ምን ማለት ነው? አንድ በሚገባ የሠለጠነ ሠራዊት ከጠላት ጥቃት ሲሰነዘርበት ወታደሮቹ ግንባር ይፈጥራሉ፤ በሌላ አባባል እርስ በርስ ተቀራርበው ይሰለፋሉ። በዚህ መንገድ በቀላሉ የማይደፈር መከላከያ ያበጃሉ። ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት እያፋፋመ ነው። አሁን እርስ በርስ የምንሻኮትበት ጊዜ አይደለም። ይልቁንም እርስ በርስ የምንቀራረብበት፣ የሌሎችን አለፍጽምና የምናልፍበትና በይሖዋ አመራር ላይ እምነት የምንጥልበት ጊዜ ነው።

ይህ ወቅት በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ግንባር የምንፈጥርበት ጊዜ ነው (አንቀጽ 19ን ተመልከት)

20. አሁን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

20 ሁላችንም በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንኑር፤ ደግሞም በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ እናሳይ። “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” ተብሎ እስኪታወጅና የአምላክ ምርጦች የመጨረሻው ማኅተም እስኪደረግባቸው ድረስ በትዕግሥት እንጠብቅ። ከዚያ በኋላ አራቱ መላእክት አውዳሚ ነፋሳቱን ይለቅቃሉ፤ ታላቂቱ ባቢሎንም ትደመሰሳለች። እነዚህ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ክንውኖች የሚፈጸሙበትን ጊዜ እየተጠባበቅን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ አመራር እንዲሰጡ ከተሾሙት ወንድሞች የሚመጣውን መመሪያ እንቀበል። በዲያብሎስና በአጋንንቱ ላይ ግንባር እንፍጠር! ይህ ወቅት መዝሙራዊው፣ ይሖዋን “ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤ በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና” በማለት የሰጠንን ማበረታቻ በሥራ የምናውልበት ጊዜ ነው።—መዝ. 31:24

^ አን.13 በቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ በሚደረገው የመጀመሪያ ማኅተምና የመጨረሻ ማኅተም መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት በጥር 1, 2007 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 30-31 ላይ የወጣውን ሐሳብ ተመልከት።