በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

“እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።”—1 ዮሐ. 4:19

መዝሙሮች፦ 56, 138

1, 2. ሐዋርያው ዮሐንስ በተናገረው መሠረት አምላክ እሱን እንድንወደው ራሱ ምሳሌ የሆነን እንዴት ነው?

አንድ አባት ልጆቹን ማስተማር የሚችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ራሱ ምሳሌ ሆኖ በመገኘት እንደሆነ የታወቀ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ “[አምላክ] አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐ. 4:19) በመሆኑም ይሖዋ እሱን እንድንወደው የሚያስችል የላቀ አባታዊ ፍቅር በማሳየት ምሳሌ እንደተወልን ግልጽ ነው።

2 አምላክ ‘አስቀድሞ የወደደን’ በምን መንገድ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” ብሏል። (ሮም 5:8) ይሖዋ ይህን ከፍተኛ መሥዋዕትነት በመክፈል ይኸውም በልጁ ለሚያምኑ ሰዎች የገዛ ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት እውነተኛ ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ አሳይቷል። ይህ ፍቅር የተገለጠው በተግባር ማለትም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ወይም የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ነው። አምላክ ያሳየን ታላቅ ቸርነት ወደ እሱ በመቅረብ ከፍቅሩ እንድንጠቀምና እኛም በአጸፋው ለእሱ ፍቅር እንድናሳይ አስችሎናል።—1 ዮሐ. 4:10

3, 4. አምላክን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

3 ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ነው፤ በመሆኑም ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠው የመጀመሪያው ትእዛዝ የቱ እንደሆነ ጥያቄ ላቀረበለት ሰው “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” በማለት መልስ የሰጠው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። (ማር. 12:30) ኢየሱስ፣ አምላክን ስለ መውደድ ሲናገር መጀመሪያ ላይ የጠቀሰው ልብን እንደሆነ መመልከት እንችላለን። ይሖዋ የተከፈለ ልብ አያስደስተውም። ይሁን እንጂ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ አእምሯችንና በሙሉ ኃይላችን አምላክን መውደድ እንዳለብንም መዘንጋት አይኖርብንም። ይህም ማለት ለአምላክ ያለን እውነተኛ ፍቅር እንዲሁ ከልባችን ብቻ የሚመነጭ ስሜት እንዳልሆነ ያስገነዝበናል። ለአምላክ ያለን ፍቅር ከልብ የሚመነጭ ከመሆንም አልፎ መንፈሳዊና አካላዊ ችሎታዎቻችንን በሙሉ የሚጨምር መሆን አለበት። ነቢዩ ሚክያስ በገለጸው መሠረት ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ይህን ነው።—ሚክያስ 6:8ን አንብብ።

4 በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ከልብ እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በሁለንተናችን ልንወደው ይገባል። ኢየሱስ እንደጠቀሰው መላ አካላችንን፣ ስሜታችንንና መንፈሳዊነታችንን ተጠቅመን ለእሱ ያለንን ፍቅር መግለጽ ይኖርብናል። ይሖዋ ለልጆቹ ያለውን ታላቅ ፍቅር ያሳየባቸውን አራት መንገዶች ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። አሁን ደግሞ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ባለውና እሱ በሚፈልገው መንገድ ለእሱ ያለንን ፍቅር መግለጽና ማሳደግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ይሖዋ ላደረጋቸው ዝግጅቶች አመስጋኝ መሆን

5. ይሖዋ ያደረገልንን ነገር ሁሉ ስናስብ ምን ለማድረግ ያነሳሳናል?

5 ስጦታ ሲሰጥህ ምን ታደርጋለህ? መቼም አድናቆትህን በሆነ መንገድ መግለጽህ አይቀርም። በተጨማሪም ስጦታውን በአግባቡ በመጠቀም እንደ ተራ ነገር እንደማትቆጥረው ታሳያለህ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት ሲሆን እሱ ደግሞ ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም” ሲል ጽፏል። (ያዕ. 1:17) ይሖዋ ለመኖር የሚያስፈልጉንንና ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮችን ምንም ሳያጓድል ይሰጠናል። ይህ ታዲያ እኛም በአጸፋው እንድንወደው አያነሳሳንም?

6. እስራኤላውያን የይሖዋን በረከት በቀጣይነት ማግኘት ከፈለጉ ምን ማድረግ ነበረባቸው?

6 ይሖዋ እስራኤላውያንን ለበርካታ መቶ ዓመታት በፍቅር የተንከባከባቸው ሲሆን የተትረፈረፈ ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ በረከት አፍስሶላቸዋል። (ዘዳ. 4:7, 8) ይሁንና እነዚህን በረከቶች በቀጣይነት ማግኘታቸው የተመካው ምድሪቱ ያፈራችውን “መጀመሪያ የደረሰውን ምርጥ ፍሬ” ዘወትር ለይሖዋ መስጠትን የሚያዘውን ሕግ ጨምሮ መላውን የአምላክ ሕግ በመታዘዛቸው ላይ ነበር። (ዘፀ. 23:19) እስራኤላውያን እንዲህ በማድረግ የይሖዋን ፍቅርና በረከት አቅልለው እንደማይመለከቱ ማሳየት ይችላሉ።—ዘዳግም 8:7-11ን አንብብ።

7. ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳየት ባሉን “ውድ ነገሮች” መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

7 ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? በዛሬው ጊዜ ቃል በቃል መሥዋዕቶች እንድናቀርብ ባንጠየቅም እንኳ ባሉን “ውድ ነገሮች” አምላክን በማክበር እሱን እንደምንወደው ማሳየታችን ተገቢ ነው። (ምሳሌ 3:9) እንዲህ ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? በአገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ ባለን ሀብት መደገፍ እንችላለን። በቁሳዊ ረገድ ያለን ብዙም ይሁን ጥቂት ለይሖዋ ያለንን ፍቅር በዚህ መንገድ መግለጽ እንደምንችል የታወቀ ነው። (2 ቆሮ. 8:12) ይሁን እንጂ ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ።

8, 9. ይሖዋ በገባው ቃል መታመን ለእሱ ካለን ፍቅር ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

8 ኢየሱስ ለተከታዮቹ ስለ ምግብና ልብስ መጨነቃቸውን ትተው መንግሥቱን እንዲያስቀድሙ ማሳሰቢያ እንደሰጣቸው አስታውስ። ኢየሱስ በሰማይ የሚኖረው አባታችን የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያውቅ ተናግሯል። (ማቴ. 6:31-33) አምላክ በገባልን በዚህ ቃል ላይ ያለን እምነት ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው ያሳያል፤ ምክንያቱም ፍቅርና እምነት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። የማናምነውን ሰው ልንወደው አንችልም። (መዝ. 143:8) በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘የማወጣቸው ግቦችና አኗኗሬ ይሖዋን በእርግጥ እንደምወደው ያሳያሉ? በእያንዳንዱ ቀን የማደርገው ነገር ይሖዋ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ሊያሟላልኝ እንደሚችል እምነት እንዳለኝ ያሳያል?’

9 ማይክ የተባለ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነት ፍቅርና እምነት እንዳለው አሳይቷል። ማይክ ወጣት እያለ ወደ ሌላ አገር ሄዶ አምላክን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። አግብቶ ሁለት ልጆች ከወለደ በኋላም እንኳ ወደ ሌላ አገር ሄዶ የማገልገል ፍላጎቱ አልጠፋም። የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ስለማገልገል የሚናገሩ በርካታ ተሞክሮዎችን ማንበባቸው ስላበረታታቸው ማይክና ቤተሰቡ ኑሯቸውን ለማቅለል ወሰኑ። ቤታቸውን ሸጠው አፓርታማ ላይ መኖር ጀመሩ። ከዚያም ማይክ የጽዳት ሥራ ድርጅቱን ደንበኞች ቁጥር የቀነሰ ከመሆኑም በተጨማሪ በሌላ አገር እየኖረ ሥራውን በኢንተርኔት እንዴት ማካሄድ እንደሚችል ተማረ። ማይክና ቤተሰቡ ወደ ሌላ አገር ተዛወሩ፤ በዚያም ለሁለት ዓመት በደስታ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ማይክ “ኢየሱስ በማቴዎስ 6:33 ላይ የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን ማየት ችለናል!” ብሏል።

ከአምላክ የተማራችሁትን እውነት በልባችሁ አኑሩ

10. ከንጉሥ ዳዊት ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው ስለ ይሖዋ ባወቅነው እውነት ላይ ማሰላሰላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

10 ከዛሬ 3,000 ዓመታት ገደማ በፊት የኖረው ንጉሥ ዳዊት በግዑዙ ሰማይ ላይ ባየው ነገር ተደንቆ ነበር። ዳዊት “ሰማያት የአምላክን ክብር ይናገራሉ፤ ጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያውጃል” ሲል ጽፏል። ከዚያም የአምላክ ሕግ በያዘው ጥበብ ስለተደመመ “የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው፤ ኃይልን ያድሳል። የይሖዋ ማሳሰቢያ አስተማማኝ ነው፤ ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ ያደርጋል” ብሏል። ዳዊት በዚህ መንገድ በአድናቆት ማሰላሰሉ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል? “ዓለቴና አዳኜ ይሖዋ ሆይ፣ የአፌ ቃልና በልቤ የማሰላስለው ነገር አንተን ደስ የሚያሰኝ ይሁን” ሲል ተናግሯል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደምንችለው ዳዊት ከአምላክ ጋር የተቀራረበና የጠበቀ ዝምድና መሥርቶ ነበር።—መዝ. 19:1, 7, 14

11. ለአምላክ ያለን ፍቅር በዛሬው ጊዜ እያገኘነው ባለነው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ እውቀት ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

11 በዛሬው ጊዜ ስለ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎችና ዓላማው እየተፈጸመ ስላለበት መንገድ ሰፊ እውቀት በማግኘት ተባርከናል። ዓለም ከፍተኛ ትምህርትንና ብዙ መማርን ያበረታታል። ይሁንና የብዙዎች ተሞክሮ እንደሚያሳየው እንዲህ ዓይነቱን ግብ መከታተል አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው እምነቱንም ሆነ ለአምላክ ያለውን ፍቅር እንዲያጣ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እውቀትን እንድንወድ ብቻ ሳይሆን ጥበብና ማስተዋልም እንዲኖረን ያበረታታናል። ይህም አምላክ የሰጠንን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን መጥቀም የምንችልበትን መንገድ ማስተዋል እንደሚገባን ያሳያል። (ምሳሌ 4:5-7) የአምላክ “ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:4) ለሰዎች ሁሉ የመንግሥቱን ምሥራች ለመንገርና ሰዎች አምላክ ለሰው ዘር ያለውን ታላቅ ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት ልባዊ ጥረት ስናደርግ ይሖዋን እንደምንወደው እናሳያለን።—መዝሙር 66:16, 17ን አንብብ።

12. አንዲት ልጅ ይሖዋ ላደረጋቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች አድናቆቷን የገለጸችው እንዴት ነው?

12 ለተደረጉልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ልጆችም እንኳ አድናቆታቸውን በመግለጽ ለይሖዋ ፍቅር እንዳላቸው ማሳየት ይችላሉ። ሻነን የ11 ዓመት ልጅ ሳለች እሷና የ10 ዓመት ልጅ የነበረችው እህቷ “ለአምላክ ማደር” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከወላጆቻቸው ጋር ተገኝተው እንደነበር ታስታውሳለች። በአንድ የስብሰባው ክፍለ ጊዜ ልጆች ለእነሱ በተመደበው ቦታ ላይ እንዲቀመጡ ተጠየቁ። ሻነን በተወሰነ መጠን ፍርሃት ቢሰማትም ሄዳ ተቀመጠች። ከዚያም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የሚል ርዕስ ያለው የሚያምር መጽሐፍ ለእያንዳንዳቸው በስጦታ ሲበረከትላቸው እጅግ ተደሰተች። ይህ ሁኔታ ሻነን ለይሖዋ አምላክ ባላት አመለካከት ላይ ምን ለውጥ አመጣ? እንዲህ ብላለች፦ “በዚህ ጊዜ ይሖዋ እውን የሆነልኝ ከመሆኑም ሌላ በግለሰብ ደረጃ እኔን በጣም፣ በጣም እንደሚወደኝ ተገነዘብኩ። ታላቁ አምላካችን ይሖዋ እንዲህ ያሉ እንከን የማይወጣላቸው፣ ድንቅ ስጦታዎች በነፃ የሚሰጠን በመሆኑ እጅግ ደስተኞች ነን!”

አምላክ የሚሰጠውን ምክርና ተግሣጽ መቀበል

13, 14. ይሖዋ ለሚሰጠን ተግሣጽ ያለን አመለካከት ለእሱ ያለንን ፍቅር በተመለከተ ምን ያሳያል?

13 መጽሐፍ ቅዱስ “አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚወቅስ ሁሉ ይሖዋም የሚወዳቸውን ይወቅሳል” ይላል። (ምሳሌ 3:12) ይሁንና ምላሻችን ምን መሆን ይኖርበታል? ሐዋርያው ጳውሎስ “ማንኛውም ተግሣጽ ለጊዜው የሚያስደስት አይመስልም፤ ይልቁንም ያስከፋል” ብሎ ሲጽፍ ሐቁን በግልጽ እየተናገረ ነበር። ይሁንና ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሲናገር የተግሣጽን አስፈላጊነት ወይም ዋጋማነት ማቃለሉ አልነበረም፤ ምክንያቱም ከዚያ በመቀጠል “በኋላ ግን በተግሣጽ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች የጽድቅን ሰላማዊ ፍሬ ያፈራላቸዋል” ብሏል። (ዕብ. 12:11) ይሖዋን የምንወደው ከሆነ ምክር ሲሰጠን ሰምተን እንዳልሰማን ከመሆን ወይም ቅር ከመሰኘት እንቆጠባለን። ለአንዳንዶች ይህ ከባድ ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል። በዚህ ረገድ ለአምላክ ያለን ፍቅር በእጅጉ ይረዳናል።

14 በሚልክያስ ዘመን ብዙ አይሁዳውያን አምላክ የሰጣቸውን ምክር ሳይቀበሉ ቀርተዋል። ለአምላክ የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን በተመለከተ ሕጉ ምን እንደሚል ያውቃሉ፤ ይሁንና አሳፋሪ ቸልተኝነት በማሳየታቸው ይሖዋ ጠንከር ያለ ምክር መስጠት አስፈልጎታል። (ሚልክያስ 1:12, 13ን አንብብ።) ሁኔታው ምን ያህል አሳሳቢ ነበር? ይሖዋ ምን እንዳላቸው እንመልከት፦ “በእናንተ ላይ እርግማን እሰዳለሁ፤ በረከታችሁንም ወደ እርግማን እለውጣለሁ። አዎ፣ [ትእዛዜን] በልባችሁ ስላላኖራችሁት እያንዳንዱን በረከት ወደ እርግማን ለውጫለሁ።” (ሚል. 2:1, 2) ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የሚሰጠንን ምክር ያለመቀበል ልማድ ካለን ወይም ሆን ብለን ቸል የምንል ከሆነ መዘዙ የከፋ ሊሆን ይችላል።

የዓለምን መሥፈርቶች ሳይሆን የአምላክን ምክር ተከተሉ (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15. ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ በስፋት የሚታየው የትኛው ዝንባሌ እንዳይጋባብን መጠንቀቅ አለብን?

15 ዛሬ ባለው ራስ ወዳድና እኔ ልቅደም ባይ በሆነ ትውልድ ውስጥ ምክርና ተግሣጽ መቀበል ይቅርና ስለ እነዚህ ነገሮች ማንሳት በራሱ አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ምክር ወይም ተግሣጽ ሲሰጣቸው ቢቀበሉም እንኳ ይህን የሚያደርጉት እያጉረመረሙ ነው። ክርስቲያኖች ግን “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ ይልቅ “ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” መገንዘብና መፈጸም ይኖርብናል። (ሮም 12:2) ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት የተለያየ ወቅታዊ ምክር ይሰጠናል፤ ለምሳሌ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት፣ ስለ ጓደኛ ምርጫና ስለ መዝናኛ ምክር እናገኛለን። እንዲህ ያለውን መመሪያ በፈቃደኝነት በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ አመስጋኝ መሆናችንን እንዲሁም ይሖዋን ከልባችን እንደምንወደው እናሳያለን።—ዮሐ. 14:31፤ ሮም 6:17

ይሖዋ እንደሚረዳችሁና እንደሚጠብቃችሁ ተማመኑ

16, 17. (ሀ) ውሳኔ ስናደርግ የይሖዋን ፈቃድ ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) እስራኤላውያን ለይሖዋ ፍቅር እንደጎደላቸውና በእሱ እንዳልታመኑ ያሳዩት እንዴት ነው?

16 ትናንሽ ልጆች ፍርሃት ሲሰማቸው በደመ ነፍስ ወደ ወላጆቻቸው ይሮጣሉ። እያደጉ ሲሄዱ ግን በራሳቸው የማመዛዘን ችሎታ ይጠቀማሉ፤ እንዲሁም የራሳቸውን ውሳኔ ያደርጋሉ። ይህ የጉልምስና አንዱ መገለጫ ነው። ይሁን እንጂ ከወላጆቻቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ልጆች ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት የወላጆቻቸውን አመለካከትና ምክር ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። በመንፈሳዊም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ‘ፍላጎት እንዲያድርብንም ሆነ ለተግባር እንድንነሳሳ በማድረግ ኃይል ይሰጠናል።’ ይሁንና የእሱን ፈቃድ ግምት ውስጥ ሳናስገባ ውሳኔ የምናደርግ ከሆነ ፍቅርና እምነት እንደሚጎድለን ያሳያል።—ፊልጵ. 2:13

17 በሳሙኤል ዘመን በአንድ ወቅት እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር ባደረጉት ውጊያ ከባድ ሽንፈት ደርሶባቸው ነበር። በዚህ ጊዜ አምላክ እንዲረዳቸውና እንዲጠብቃቸው ፈልገው ነበር። ታዲያ ምን አደረጉ? “አብሮን እንዲሆንና ከጠላቶቻችን እጅ እንዲያድነን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ ይዘነው እንሂድ” አሉ። ውጤቱስ ምን ሆነ? “በጣም ብዙ ሕዝብ አለቀ፤ ከእስራኤላውያንም ወገን 30,000 እግረኛ ወታደር ሞተ። የአምላክም ታቦት ተማረከ።” (1 ሳሙ. 4:2-4, 10, 11) እስራኤላውያን ታቦቱን ይዘው መሄዳቸው ይሖዋ እንዲረዳቸው የፈለጉ ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት አላደረጉም፤ ከዚህ ይልቅ በራሳቸው አመለካከት በመመራታቸው ለከፋ ጥፋት ተዳርገዋል።—ምሳሌ 14:12ን አንብብ።

18. በይሖዋ መታመንን በተመለከተ ምን ነገር ማስተዋል ይኖርብናል?

18 መዝሙራዊው “አምላክን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ እሱን እንደ ታላቅ አዳኜ አድርጌ ገና አወድሰዋለሁና። አምላኬ ሆይ፣ ተስፋ ቆርጫለሁ። . . . የማስብህ ለዚህ ነው” ብሎ በጻፈ ጊዜ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዳለው አሳይቷል። (መዝ. 42:5, 6) ለይሖዋ ያለውን ልዩ ስሜትና ፍቅር የሚገልጽ እንዴት ያለ ግሩም ሐሳብ ነው! በሰማይ ለሚኖረው አባታችን እንዲህ ዓይነት ፍቅር አለህ? በእሱስ ትታመናለህ? አዎ የሚል መልስ ብትሰጥም እንኳ ከሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አንጻር በእሱ ላይ ያለህ እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ እንዳለበት ማስተዋል ይኖርብሃል፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6

19. ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ እኛን አስቀድሞ በመውደድ እሱን መውደድ የምንችልበትን መንገድ አሳይቶናል። እሱ የተወልንን የላቀ ምሳሌ ምንጊዜም እናስታውስ። እንዲሁም እሱን ‘በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ አእምሯችንና በሙሉ ኃይላችን’ በመውደድ ለእሱ ያለን ፍቅር ምንጊዜም እየጨመረ ይሂድ!—ማር. 12:30