በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንደበታችሁ ያለውን ኃይል ለመልካም ነገር ተጠቀሙበት

አንደበታችሁ ያለውን ኃይል ለመልካም ነገር ተጠቀሙበት

“ይሖዋ ሆይ፣ የአፌ ቃል . . . አንተን ደስ የሚያሰኝ ይሁን።”—መዝ. 19:14

መዝሙሮች፦ 82, 77

1, 2. ምላስ ያለውን ኃይል ለመግለጽ እሳት ግሩም ምሳሌ ይሆናል የምንለው ለምንድን ነው?

ጥቅምት 1871 መጀመሪያ አካባቢ በሰሜን ምሥራቅ ዊስካንሰን በሚገኘው ደን ውስጥ ሰደድ እሳት ተነሳ፤ ይህ እሳት በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ውስጥ የብዙዎችን ሕይወት በማጥፋት ረገድ ተወዳዳሪ እንደሌለው ይነገራል። እሳቱ እየተባባሰ ሲሄድ በነበልባሉና በወላፈኑ የተነሳ ከ1,200 የሚበልጡ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ሁለት ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ዛፎች ወድመዋል። ደኑ እንዲጋይ ምክንያት የሆነው በዚያ ከሚያልፉ ባቡሮች ላይ የተስፈነጠረ የእሳት ፍንጣቂ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም በያዕቆብ 3:5 ላይ የሚገኘው “በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል” የሚለው ሐሳብ ምንኛ እውነት ነው! ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲህ ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው?

2 ያዕቆብ በዚህ ምሳሌ ላይ ሊያጎላው የፈለገውን ነጥብ ቁጥር 6 ላይ ግልጽ አድርጎታል። ጥቅሱ “ምላስም እሳት ናት” ይላል። ምላስ የሚለው ቃል የመናገር ችሎታችንን ያመለክታል። እንደ እሳት ሁሉ ንግግራችንም ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበት የሞትና የሕይወት ኃይል አላት” ይላል። (ምሳሌ 18:21) እርግጥ ነው፣ እሳት የሚያስከትለውን ጉዳት በመፍራት በእሳት መጠቀማችንን እንደማናቆም ሁሉ፣ ጎጂ ነገር እንዳንናገር በመስጋት መናገራችንን እስከ ጭራሹ አናቆምም። ቁልፉ አንደበታችንን መቆጣጠር መቻላችን ላይ ነው። እሳትን በተገቢው መንገድ የምንጠቀምበት ከሆነ ምግባችንን ለማብሰልና ሰውነታችንን ለማሞቅ ሊያገለግለን እንዲሁም ብርሃን ሊሰጠን ይችላል። ምላሳችንንም ከገራነው አምላክን በሚያስከብርና ሌሎችን በሚጠቅም መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን።—መዝ. 19:14

3. ከንግግር ጋር በተያያዘ የትኞቹን ሦስት ነጥቦች እንመረምራለን?

3 ድምፅ አውጥተን በመናገርም ይሁን በእጃችን ምልክት በመስጠት ሐሳባችንንና ስሜታችንን የመግለጽ ችሎታ ከአምላክ ያገኘነው ድንቅ ስጦታ ነው። ታዲያ ይህን ስጦታ፣ ለማፍረስ ሳይሆን ለማነጽ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? (ያዕቆብ 3:9, 10ን አንብብ።) ከዚህ ቀጥሎ ከንግግር ጋር በተያያዘ ሦስት አስፈላጊ ነጥቦችን ይኸውም መቼ፣ ምን እና እንዴት መናገር እንዳለብን እንመረምራለን።

መቼ እንናገር?

4. “ዝም ለማለት ጊዜ አለው” የሚለው ጥቅስ ተግባራዊ መሆን የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ጥቀስ።

4 መናገር፣ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል ቢሆንም ሁልጊዜ ማውራት አለብን ማለት አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው” ይላል። (መክ. 3:7) ሌሎች ሲናገሩ ዝም ማለት አክብሮት እንዳለን ያሳያል። (ኢዮብ 6:24) ሚስጥር ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አንደበታችንን በመቆጣጠር ዝም ማለታችን ደግሞ የማስተዋልና የማመዛዘን ችሎታ እንዳለን ይጠቁማል። (ምሳሌ 20:19) የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥመን አንደበታችንን መግታትም የጥበብ እርምጃ ነው።—መዝ. 4:4

5. ከአምላክ ላገኘነው የመናገር ስጦታ አድናቆታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?

5 በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክ. 3:7) አንድ ጓደኛህ የሚያምር ስጦታ ቢሰጥህ ማንም የማያየው ቦታ አታስቀምጠውም። ከዚህ ይልቅ በስጦታው በተገቢው መንገድ በመጠቀም አድናቆትህን ታሳያለህ። በተመሳሳይም ከይሖዋ ባገኘነው የመናገር ስጦታ በጥበብ በመጠቀም አመስጋኝነታችንን እናሳያለን። ይህም ስሜታችንን መግለጽን፣ የሚያስፈልገንን ነገር መናገርን፣ ሌሎችን ማበረታታትንና አምላክን ማወደስን ሊጨምር ይችላል። (መዝ. 51:15) ይሁንና “ለመናገር” ተገቢ የሆነውን ጊዜ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

6. መጽሐፍ ቅዱስ ለመናገር ተገቢውን ጊዜ የመምረጥን አስፈላጊነት የሚያጎላው እንዴት ነው?

6 ምሳሌ 25:11 ለመናገር ተገቢውን ጊዜ የመምረጥን አስፈላጊነት ያጎላል፤ ጥቅሱ “በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው” ይላል። የወርቅ ፖም በራሱ የሚያምር ነገር ነው። ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ ሲቀመጥ ደግሞ ውበቱ ይበልጥ ደምቆ ይታያል። በተመሳሳይም ተስማሚ የሆነውን ጊዜ መርጠን መናገራችን፣ የምንናገረው ነገር ይበልጥ ማራኪና ውጤታማ እንዲሆን ያደርጋል። እንዴት?

7, 8. በጃፓን የሚኖሩት ወንድሞቻችን ስለ ትንሣኤ ተስፋ ለመናገር ተገቢውን ጊዜ መምረጣቸው የኢየሱስን ምሳሌ እንደተከተሉ የሚያሳየው እንዴት ነው?

7 የምንናገረው ነገር ለሚሰማን ሰው በጣም አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ መቼ መናገር እንዳለብን ካላወቅን ንግግራችን ዋጋ ሊያጣ ይችላል። (ምሳሌ 15:23ን አንብብ።) መጋቢት 2011 በጃፓን ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በዚያ ወቅት የምሥራቃዊ ጃፓን የተወሰነ ክፍል በምድር መናወጥና በሱናሚ የተመታ ሲሆን አንዳንድ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ወደሙ። ከ15,000 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ልክ እንደ ሌሎቹ ሰዎች በአደጋው የተጠቁ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ያዘኑትን ለማጽናናት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመዋል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የቡድሂዝምን እምነት በጥብቅ የሚከተሉ ከመሆናቸውም ሌላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አያውቁም፤ አሊያም እውቀታቸው በጣም ውስን ነው። ወንድሞቻችን፣ ለአካባቢው ሰዎች ስለ ትንሣኤ ተስፋ ለመናገር ጥሩ የሆነው ጊዜ ሱናሚው የተከሰተበት ወቅት እንዳልሆነ አስተዋሉ። በመሆኑም ወንድሞች በንግግር ስጦታቸው ተጠቅመው ሰዎችን በማጽናናትና እንዲህ ያለው መከራ በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ በማብራራት ላይ ትኩረት አደረጉ።

8 ኢየሱስ መቼ መናገር እንደሌለበት ያውቃል፤ ያም ቢሆን ለመናገር ተገቢ የሆነው ጊዜ መቼ እንደሆነም ያውቅ ነበር። (ዮሐ. 18:33-37፤ 19:8-11) በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 16:12) በምሥራቃዊ ጃፓን የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮችም የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለዋል። ሱናሚው ከተከሰተ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ፣ “የሞቱ ሰዎች እንደገና በሕይወት መኖር ይችላሉ?” የተባለውን የመንግሥት ዜና ቁ. 38 ለማሰራጨት በተካሄደው ዓለም አቀፍ ዘመቻ ተካፍለዋል። በዚህ ጊዜ ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ስለ ትንሣኤ የሚናገር አስደሳችና የሚያጽናና መልእክት ለመስማት ዝግጁ ነበሩ፤ በርካታ ሰዎች ትራክቱን በደስታ ወስደዋል። እርግጥ ነው፣ የሰዎች ባሕልና ሃይማኖት ከቦታ ቦታ ይለያያል፤ በመሆኑም ለመናገር ተገቢ የሆነውን ጊዜ ስንመርጥ አስተዋዮች መሆን አለብን።

9. ለመናገር ተገቢውን ጊዜ መምረጣችን አስፈላጊ የሚሆነው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው?

9 ለመናገር ተገቢውን ጊዜ መምረጣችን አስፈላጊ የሆነባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ግልጽ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው መልካም አስቦ የተናገረው ነገርም እንኳ ቅር ሊያሰኘን ይችላል። የጉዳዩን ክብደት ለማጤንና ግለሰቡን ልናነጋግረው ይገባ እንደሆነ ለመወሰን ጊዜ ወስደን ማሰባችን አስተዋይነት ነው። ቅር ያሰኘንን ሰው ለማነጋገር ከወሰንን፣ በተበሳጨንበትና ነገሮችን ሳናመዛዝን ልንናገር በምንችልበት ወቅት መናገራችን ጥበብ አይሆንም። (ምሳሌ 15:28ን አንብብ።) በተመሳሳይም ለማያምኑ ዘመዶቻችን እውነትን ስንነግራቸው አስተዋይ መሆን አለብን። ይሖዋን እንዲያውቁ እንደምንፈልግ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ትዕግሥተኛ መሆንና ነገሮችን ማመዛዘን ይኖርብናል። በተገቢው ጊዜ ተገቢውን ቃል መናገራችን ልባቸው እንዲነካ ሊያደርግ ይችላል።

ምን እንናገር?

10. (ሀ) የምንናገራቸውን ቃላት በጥንቃቄ መምረጥ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ምን ዓይነት አነጋገርን ማስወገድ ይኖርብናል?

10 ቃላት ሰዎችን የመጉዳት አሊያም የመፈወስ ኃይል አላቸው። (ምሳሌ 12:18ን አንብብ።) በሰይጣን ዓለም ውስጥ በቃላት ተጠቅሞ ሌሎችን መጉዳት የተለመደ ነው። የመዝናኛው ዓለም፣ ሰዎች “ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ [እንዲስሉ]” እንዲሁም “መርዘኛ ቃላቸውን እንደ ቀስት [እንዲያነጣጥሩ]” ያበረታታል። (መዝ. 64:3) አንድ ክርስቲያን እንዲህ ካለው ጎጂ ልማድ መራቅ ይኖርበታል። ‘መርዘኛ ቃላት’ ተብለው ሊፈረጁ ከሚችሉት አነጋገሮች አንዱ ሽሙጥ ነው፤ ሽሙጥ ሌሎችን ለማቃለል ወይም ለመዝለፍ ተብሎ የሚሰነዘር ስሜትን የሚጎዳ አነጋገር ነው። ብዙውን ጊዜ ለቀልድ ተብሎ የሚነገር ቢሆንም ሳይታሰብ መልኩን ሊቀይርና ሌሎችን የሚያንኳስስ ወይም ስድብ አዘል መልእክት የሚያስተላልፍ ሊሆን ይችላል። መርዘኛ የሆነ ሽሙጥ፣ ስድብ በመሆኑ ክርስቲያኖች ‘ሊያስወግዱት’ ይገባል። ቀልድ ጨዋታን ሊያጣፍጥ ቢችልም ሌሎችን በነገር በመውጋትና ስሜታቸውን የሚጎዳ ወይም እነሱን የሚያንቋሽሽ አሽሙር በመናገር ለማሳቅ ከመሞከር መቆጠብ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል፦ “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል ብቻ እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።”—ኤፌ. 4:29, 31

11. ተገቢ ቃላትን ለመምረጥ ምን ሊረዳን ይችላል?

11 ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” በማለት አስተምሯል። (ማቴ. 12:34) በመሆኑም ተገቢ ቃላት ለመናገር መጀመሪያ በልባችን ውስጥ ላለው ሐሳብ ትኩረት መስጠት አለብን። ስለ ሌሎች ያለን ስሜት ብዙውን ጊዜ በንግግራችን ላይ ይንጸባረቃል። ልባችን በፍቅርና በርኅራኄ ከተሞላ ንግግራችን አዎንታዊና የሚያንጽ ይሆናል።

12. ተገቢ ቃላትን የመምረጥ ችሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

12 በተጨማሪም ተገቢ ቃላትን ለመምረጥ ስለምንናገረው ነገር ማሰብና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ያስፈልገናል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞንም እንኳ “ደስ የሚያሰኙ ቃላትን ለማግኘትና የእውነትን ቃል በትክክል ለመመዝገብ” ሲል ‘አሰላስሏል እንዲሁም ሰፊ ምርምር አድርጓል።’ (መክ. 12:9, 10) “ደስ የሚያሰኙ ቃላትን” መናገር አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ይሆንብሃል? ከሆነ የምታውቃቸውን ቃላት ብዛት ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ቃላት እንዴት እንደሚሠራባቸው ማስተዋል ነው። የማታውቃቸውን አገላለጾች ትርጉም ለማወቅ ሞክር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ቃላትን ሌሎችን በሚያንጽ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ተማር። በይሖዋና በበኩር ልጁ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘[ኢየሱስ] ለደከመው ትክክለኛውን ቃል በመናገር እንዴት መልስ መስጠት እንደሚችል ያውቅ ዘንድ ይሖዋ የተማሩ ሰዎችን አንደበት ሰጥቶታል።’ (ኢሳ. 50:4) ከመናገራችን በፊት፣ ምን እንደምንል ቆም ብለን ማሰላሰላችን ተገቢ ቃላት ለመጠቀም ያስችለናል። (ያዕ. 1:19) ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘እነዚህ ቃላት ሐሳቤን በትክክል ያስተላልፋሉ? የምጠቀምባቸው ቃላት በሚያዳምጡኝ ሰዎች ላይ ምን ስሜት ይፈጥራሉ?’

13. ንግግራችን ለመረዳት ቀላል መሆኑ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 በጥንቷ እስራኤል ሕዝቡን ለመሰብሰብና ከሰፈረባቸው ቦታዎች ተነስቶ እንዲሄድ ምልክት ለመስጠት እንዲሁም ጦርነት እንዲወጣ ለማነሳሳት መለከት ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለመረዳት ቀላል የሆነ ንግግር አስፈላጊ መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት የመለከትን ድምፅ መጥቀሱ ተስማሚ ነው። ግልጽ ያልሆነ የመለከት ድምፅ በዘመቻ ላይ ያለን ሠራዊት ለአደጋ ሊያጋልጠው ይችላል። በተመሳሳይም የምንናገረው ነገር የተድበሰበሰ ወይም ዙሪያ ጥምጥም ከሆነ ሰሚዎቹን ግራ ሊያጋባና ሊያሳስት ይችላል። እርግጥ ነው፣ ንግግራችን ግልጽ ይሁን ሲባል አክብሮትና ዘዴኛነት የጎደለው ይሆናል ማለት አይደለም።1 ቆሮንቶስ 14:8, 9ን አንብብ።

14. የኢየሱስ ንግግር ለመረዳት የማይከብድ እንደነበር የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።

14 ኢየሱስ ተገቢ ቃላትን መርጦ በመጠቀም ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን አጭር ሆኖም ኃይለኛ መልእክት የያዘ ንግግሩን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ የተራቀቁ ወይም አሻሚ ቃላትን አልተጠቀመም፤ ንግግሩ ኃይለ ቃል ያዘለ ወይም ጎጂ አልነበረም። የአድማጮቹን ልብ ለመንካት ሲል ግልጽና ቀላል የሆኑ አገላለጾችን ተጠቅሟል። ለአብነት ያህል፣ ሕዝቡ ስለ ዕለታዊ ምግባቸው እንዳይጨነቁ ለመርዳት ሲል ይሖዋ የሰማይ ወፎችን የሚመግብበትን መንገድ እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። ከዚያም አድማጮቹን ከወፎች ጋር በማወዳደር “ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?” ብሎ ጠየቃቸው። (ማቴ. 6:26) ቀላል፣ ለመረዳት የማይከብዱና ልብ የሚነኩ ቃላትን በመጠቀም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ የቀረበ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! እስቲ አሁን ደግሞ ከንግግራችን ጋር በተያያዘ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባውን ሦስተኛ ነጥብ እንመልከት።

እንዴት እንናገር?

15. ንግግራችን ማራኪ እንዲሆን መጣር ያለብን ለምንድን ነው?

15 የምንናገርበትን መንገድ ከምንናገረው ነገር ባልተናነሰ ልናስብበት ይገባል። ኢየሱስ ባደገበት በናዝሬት በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ባስተማረበት ወቅት ሕዝቡ “ከአፉ በሚወጡት የሚማርኩ ቃላት” ተደንቀዋል። (ሉቃስ 4:22) የሚማርክ ወይም ለዛ ያለው ንግግር ልብን ደስ ያሰኛል፤ እንዲህ ያለው አነጋገር፣ የምንናገረውን ነገር ኃይል ያሳጣዋል ብለን መስጋት አይኖርብንም። እንዲያውም ማራኪ የሆኑ ቃላት ንግግራችን ይበልጥ አሳማኝ እንዲሆን ያደርጋሉ። (ምሳሌ 25:15) እኛም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል ንግግራችን ደግነት፣ አክብሮትና ለሌሎች ስሜት አሳቢነት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ ሕዝቡ እሱን ለማዳመጥ ሲሉ ያደረጉትን ጥረት ሲመለከት በጣም ስላዘነላቸው ‘ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል።’ (ማር. 6:34) ኢየሱስ ሌሎች ቢሰድቡትም እንኳ ኃይለ ቃል አልተናገረም።—1 ጴጥ. 2:23

16, 17. (ሀ) ከቤተሰባችን አባላትም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ካሉ የቅርብ ወዳጆቻችን ጋር ስንነጋገር ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) የለዘበ መልስ ያለውን ጥቅም የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።

16 በጣም የምንቀርበውን ሰው በለሰለሰ አንደበትና ዘዴኛነት በተሞላበት መንገድ ማነጋገር ሊከብደን ይችላል። እንዲያውም የፈለግነውን የመናገር ነፃነት እንዳለን ይሰማን ይሆናል። ለምሳሌ ከቤተሰባችን አባል ወይም በጉባኤ ውስጥ ከምንቀርበው ጓደኛችን ጋር ስናወራ እንዲህ እናደርግ ይሆናል። ይሁንና ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለሚቀርባቸው እነሱን በኃይለ ቃል ለመናገር ነፃነት እንዳለው ተሰምቶት ነበር? በፍጹም! የቅርብ ተከታዮቹ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲከራከሩ ኢየሱስ አንድን ትንሽ ልጅ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ደግነት በተሞላበት መንገድ እርማት ሰጥቷቸዋል። (ማር. 9:33-37) ሽማግሌዎች “በገርነት መንፈስ” ምክር በመስጠት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ።—ገላ. 6:1

17 አንድ ሰው ቅር የሚያሰኝ ነገር በሚናገርበት ጊዜም እንኳ የለዘበ መልስ መስጠት ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። (ምሳሌ 15:1) አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ የአንዲት ነጠላ እህት ልጅ ሁለት ዓይነት ሕይወት እየመራ ነበር። አንዲት ሌላ እህት ይህችን እናት “ልጅሽን በማሠልጠን ረገድ ሳይሳካልሽ መቅረቱ በጣም ያሳዝናል” አለቻት፤ ይህን ያለችው ስላዘነችላት ነው። እናትየው ቆም ብላ ካሰበች በኋላ እንዲህ በማለት መለሰችላት፦ “ነገሮች በትክክለኛው አቅጣጫ እየሄዱ እንዳልሆነ አልክድም፤ ሆኖም ልጄ ሥልጠናውን ገና አልጨረሰም። እርግጠኛ መሆን የምንችለው ከአርማጌዶን በኋላ ነው።” ይህች እናት የሰጠችው የለዘበ መልስ በሁለቱ እህቶች መካከል ያለው ሰላም እንዳይደፈርስ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ጭውውታቸውን ይሰማ የነበረውን የእህትን ልጅ አበረታቶታል። ልጁ፣ እናቱ በእሱ ተስፋ እንዳልቆረጠች ተገነዘበ። ይህም ከመጥፎ ጓደኞች እንዲርቅ አነሳሳው። ከጊዜ በኋላ የተጠመቀ ሲሆን ውሎ አድሮም ቤቴል ገባ። ከወንድሞቻችን፣ ከቤተሰባችን አባላት ወይም ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ስንሆን ንግግራችን ምንጊዜም “በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው” ሊሆን ይገባል።—ቆላ. 4:6

18. በንግግራችን የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን አንደበታችን ያለውን ኃይል ለመልካም ነገር ለመጠቀም የሚረዳን እንዴት ነው?

18 በእርግጥም ሐሳባችንንና ስሜታችንን በቃላት የመግለጽ ችሎታ ድንቅ ስጦታ ነው! እንግዲያው ለመናገር ተገቢውን ጊዜ በመምረጥ፣ ተስማሚ ቃላትን በመጠቀም እንዲሁም ማራኪ በሆነ መንገድ ለመናገር ጥረት በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተል። እንዲህ ካደረግን የአንደበታችንን ኃይል አድማጮችን በሚፈውስ ብሎም ውድ የሆነውን የመናገር ስጦታ የሰጠንን ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን።