ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ማርያም የተጠቀመችው ሽቱ በጣም ውድ የነበረው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት የአልዓዛር እህት ማርያም “ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ” በመምጣት ሽቱውን በኢየሱስ ላይ አፍስሳ ነበር። (ማርቆስ 14:3-5፤ ማቴዎስ 26:6, 7፤ ዮሐንስ 12:3-5) የማርቆስና የዮሐንስ ዘገባዎች፣ ይህ ሽቱ 300 ዲናር እንደሚያወጣ የተናገሩ ሲሆን ይህም አንድ የቀን ሠራተኛ ያገኝ የነበረውን የዓመት ደሞዝ ያህላል።
ይህ ውድ ሽቱ የሚቀመመው ከምን ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የናርዶስ ሽቱ የሚቀመመው በሂማሊያ ተራሮች ከሚገኝ ጥሩ መዓዛ ካለው አንድ ትንሽ ተክል (ናርዶስታኪስ ጃታማንሲ) እንደሆነ ይታመናል። ሰዎች ውድ ዋጋ ያለውን ይህን የናርዶስ ሽቱ ርካሽ ከሆነ ንጥረ ነገር ጋር የሚቀላቅሉት ከመሆኑም በላይ አስመስለው ይሠሩት ነበር። ሆኖም ማርቆስና ዮሐንስ “ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ” የሚለውን አገላለጽ ተጠቅመዋል። ሽቱው በጣም ውድ መሆኑ ከሕንድ የመጣ ሳይሆን እንደማይቀር ይጠቁማል።
የማርቆስ ዘገባ ማርያም ‘ቢልቃጡን እንደሰበረች’ የገለጸው ለምንድን ነው? የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አብዛኛውን ጊዜ ቀጠን ያለ አንገት እንዲኖረው ተደርጎ የሚሠራ ሲሆን ይህም ውድ የሆነው ሽቱ እንዳይተን ግጥም አድርጎ ለማሸግ ያስችላል። አለን ሚላርድ ዲስከቨሪስ ፍሮም ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ በተባለ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በደስታ ስሜት የተዋጠችው ይህች ሴት እሽጉን እንኳ ለማንሳት ጊዜ ሳትሰጥ ሽቱውን በሙሉ በአንድ ጊዜ ለማፍሰስ እንዴት [የቢልቃጡን አንገት] ልትሰብረው እንደምትችል ለመረዳት አያዳግትም።” ይህም፣ ‘የሽቱው መዓዛ ቤቱን የሞላው’ ለምን እንደሆነ ግልጽ ያደርገዋል። (ዮሐንስ 12:3) በእርግጥም ይህች አድናቂ ሴት በጣም ውድ ሆኖም ተገቢ የሆነ ስጦታ አቅርባለች። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ የምትወደውን ወንድሟን አልዓዛርን ከጥቂት ጊዜ በፊት ከሞት አስነስቶላታል።—ዮሐንስ 11:32-45
ኢያሪኮ የሚባል ከተማ አንድ ብቻ ነበር ወይስ ሁለት?
ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ በኢያሪኮ አጠገብ ስለተከናወነ ተአምራዊ ፈውስ ዘግበዋል። (ማቴዎስ 20:29-34፤ ማርቆስ 10:46-52፤ ሉቃስ 18:35-43) ኢየሱስ ይህን ተአምር የፈጸመው ከኢያሪኮ ‘ወጥቶ ሲሄድ’ እንደሆነ ማቴዎስና ማርቆስ ተናግረዋል። ሉቃስ ግን ሁኔታው የተከናወነው ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ “በቀረበ ጊዜ” እንደሆነ ተናግሯል።
በኢየሱስ ዘመን፣ ኢያሪኮ የሚባል ከተማ አንድ ብቻ ነበር ወይስ ሁለት? ባይብል ዜን ኤንድ ናው የተባለው መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “በአዲስ ኪዳን ዘመን የድሮዋ ከተማ ትገኝበት ከነበረው ቦታ በስተ ደቡብ አንድ ማይል (1.6 ኪሎ ሜትር) ርቀት ላይ ኢያሪኮ የምትባል ሌላ ከተማ ተገንብታ ነበር። ታላቁ ሄሮድስ ክረምቱን የሚያሳልፍበት ቤተ መንግሥት በዚያ ሠርቶ ነበር።” አርኪኦሎጂ ኤንድ ባይብል ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ ይህ እውነት መሆኑን ሲያረጋግጥ እንዲህ ብሏል:- “በኢየሱስ ዘመን ኢያሪኮ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ከተሞች ነበሩ። . . . የጥንቶቹ የአይሁዳውያን ከተማ ከሮማውያኑ ከተማ 1.6 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ ይገኝ ነበር።”
በመሆኑም ኢየሱስ ፈውሱን ያከናወነው ከአይሁዳውያኑ ከተማ ወጥቶ ወደ ሮማውያኑ ከተማ በቀረበበት ጊዜ አሊያም ከሮማውያኑ ከተማ ወጥቶ ወደ አይሁዳውያኑ ከተማ በቀረበበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ታሪኩ በተጻፈበት ዘመን ስለነበሩት ሁኔታዎች ማወቅ የሚጋጩ የሚመስሉ ሐሳቦችን ለማስታረቅ ይረዳል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአልባስጥሮስ ሽቱ ቢልቃጥ
[ምንጭ]
© Réunion des Musées Nationaux/Art Resource, NY