በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የቃል ኪዳኑ ታቦት የት እንደደረሰ የሚታወቅ ነገር አለ?

የቃል ኪዳኑ ታቦት አምላክ በእስራኤላውያን መካከል እንዳለ የሚያሳይ መግለጫ ሆኖ ያገለግል ነበር። (ዘፀአት 25:22) ታቦቱ፣ ሙሴ ሕጉ የተጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ያስቀመጠበት ከእንጨት የተሠራና በወርቅ የተለበጠ ቅዱስ ሣጥን ነበር። እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚቀመጠው በመገናኛው ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ነበር። (ዘፀአት 26:33) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰለሞን በሠራው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ተቀምጧል።—1 ነገሥት 6:19

ታቦቱ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰው ንጉሥ ኢዮስያስ በ642 ዓ.ዓ. ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲመለስ ማድረጉን በሚናገረው ዘገባ ላይ ይኸውም በ⁠2 ዜና መዋዕል 35:3 ላይ ነው። ታቦቱን መመለስ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ከኢዮስያስ በፊት ንጉሥ የነበረው ከሃዲው ምናሴ የጣዖት አምልኮ ባስፋፋበት ጊዜ ከቤተ መቅደሱ አውጥቶት ስለነበር ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱ እንዲታደስ ባደረገበት ጊዜ ለጥንቃቄ ሲባል ሌላ ቦታ ተቀምጦ ስለነበር ሊሆን ይችላል። (2 ዜና መዋዕል 33:1, 2, 7፤ 34:1, 8-11) ታቦቱ ከዚያ በኋላ የት እንደደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም፤ ምክንያቱም ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በ607 ዓ.ዓ. ድል አድርገው ቤተ መቅደሱን በዘረፉ ጊዜ እንደወሰዷቸው ከተዘረዘሩት ንብረቶች መካከል አልተጠቀሰም።—2 ነገሥት 25:13-17

ታቦቱ፣ ዘሩባቤል እንደገና ወደገነባው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን እንደተመለሰ አሊያም በምትኩ ሌላ ታቦት እንደተሠራ ቅዱሳን መጻሕፍት አይናገሩም።—ዕዝራ 1:7-11

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያዕቆብ ተብለው የተጠሩት ሰዎች እነማን ናቸው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚህ ስም የተጠሩ በርከት ያሉ ሰዎች ነበሩ። ይሁንና አንዱን ከሌላው መለየት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል እስቲ አንድ በአንድ እንመልከታቸው። “አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ሲሆን ማቴዎስ 1:16 ደግሞ ‘የማርያምን ባል ዮሴፍን ስለወለደው’ ያዕቆብ ይናገራል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው ሌላው ያዕቆብ የሐዋርያው የይሁዳ አባት (የአስቆሮቱ ይሁዳ አባት አይደለም) የሆነው ያዕቆብ ሲሆን ስለ እሱ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም።—ሉቃስ 6:16፤ የሐዋርያት ሥራ 1:13

ከዚህም በተጨማሪ የዘብድዮስ ልጅ ያዕቆብ ተጠቅሷል። ይኼኛው ያዕቆብ የዮሐንስ ወንድም ሲሆን ሁለቱም የኢየሱስ ሐዋርያት ነበሩ። (ማቴዎስ 10:2) የዚህኛው ያዕቆብ እናት የኢየሱስ እናት እህት እንደሆነች ተደርጋ የምትታሰበው ሰሎሜ ሳትሆን አትቀርም። (ማቴዎስ 27:55, 56⁠ን ከ⁠ማርቆስ 15:40, 41 እና ከ⁠ዮሐንስ 19:25 ጋር አወዳድር) ይህ ከሆነ፣ ያዕቆብ የኢየሱስ የአክስት ልጅ ነው ማለት ነው። ያዕቆብና ወንድሙ ከጴጥሮስና ከእንድርያስ ጋር በመሆን ዓሣ በማጥመድ ሥራ ይተዳደሩ ነበር።—ማርቆስ 1:16-19፤ ሉቃስ 5:7-10

ሌላው ደግሞ ከኢየሱስ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ ነው። (ማርቆስ 3:16-18) ይኼኛው ያዕቆብ በ⁠ማርቆስ 15:40 ላይ “ትንሹ ያዕቆብ” ተብሎ ተጠርቷል። “ትንሹ” ተብሎ የተጠራው የዘብዴዎስ ልጅ ከሆነው ከያዕቆብ ጋር ሲተያይ በአካል ወይም በዕድሜ አነስ ስለሚል ሊሆን ይችላል።

የመጨረሻው ደግሞ የዮሴፍና የማርያም ልጅ እንዲሁም የይሁዳና የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ነው። (ማርቆስ 6:3፤ ገላትያ 1:19) ኢየሱስ በምድር ላይ ባገለገለባቸው ዓመታት ያዕቆብ የእሱ ደቀ መዝሙር አልነበረም። (ማቴዎስ 12:46-50፤ ዮሐንስ 7:5) ይሁን እንጂ በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል በፊት ሐዋርያት በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ደርብ ላይ በጸለዩ ጊዜ ያዕቆብ ከእናቱና ከወንድሞቹ ጋር በዚያ ተገኝቶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:13, 14) ያዕቆብ ከጊዜ በኋላ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረው ሲሆን በስሙ የተሰየመ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ጽፏል።—የሐዋርያት ሥራ 12:17፤ ያዕቆብ 1:1