በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገንዘብ እውነተኛ ደስታ ሊያስገኝ ይችላል?

ገንዘብ እውነተኛ ደስታ ሊያስገኝ ይችላል?

ገንዘብ እውነተኛ ደስታ ሊያስገኝ ይችላል?

ሶንያ የተወለደችው በስፔን ነው። ልጅ ሳለች ከእናቷ ጋር በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ትገኝ ነበር። ይሁንና ካደገች በኋላ ወደ ለንደን፣ እንግሊዝ ተዛውራ በአንድ ትልቅ የንግድ ድርጅት ውስጥ መሥራት ጀመረች።

ሶንያ ሥራዋን በጣም ትወደው ነበር። በሥራዋ ብዙ ገንዘብ ያገኘች ሲሆን ለደንበኞቿም ብዙ ትርፍ አስገኝታለች። በሥራዋ የምትደሰት ከመሆኑም በላይ ውጤታማ ነበረች። ሶንያ አብዛኛውን ጊዜ በቀን ውስጥ 18 ሰዓት የምትሠራ ሲሆን አንዳንዴ የምትተኛው ለሁለት ወይም ለሦስት ሰዓታት ያህል ብቻ ነበር። ሕይወቷ ያተኮረው በሥራዋ ላይ ብቻ ነበር። ይሁንና በድንገት ሁሉ ነገር እንዳልነበር ሆነ። ሶንያ ጭንቅላቷ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ከፍተኛ የጤና እክል አጋጠማት፤ ምናልባትም ይህ ሁኔታ የተከሰተው ውጥረት የተሞላ የአኗኗር ዘይቤ በመከተሏ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማት ገና 30 ዓመቷ ነበር።

ሶንያ ግማሽ አካሏ ሽባ የሆነ ሲሆን ዶክተሮቹ የመናገር ችሎታዋን እንደገና ማግኘት አለማግኘቷን እርግጠኞች አልነበሩም። በዚህ ወቅት እናቷ ለሶንያ እንክብካቤ ለማድረግ ስትል በፍጥነት ወደ እንግሊዝ ሄደች። ሶንያ መራመድ ስትጀምር እናቷ እንዲህ አለቻት፦ “እኔ ወደ ጉባኤ ስብሰባ ልሄድ ነው። ብቻሽን ትቼሽ መሄድ ስለማልችል አብረሽኝ መሄድ አለብሽ።” ሶንያም ከእናቷ ጋር አብራ ለመሄድ ተስማማች። ታዲያ ጉባኤ መሄዷ ምን ውጤት አስገኘ?

ሶንያ የነበረውን ሁኔታ አስታውሳ እንዲህ ብላለች፦ “የምሰማው ነገር ሁሉ እውነት ነበር። በጣም አስገራሚ ነው። ወደ መንግሥት አዳራሽ በሄድኩበት በመጀመሪያው ዕለት ሰላምታ ከሰጡኝ በርካታ ሰዎች መካከል ከአንዷ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ በደስታ ተቀበልኩ። የቀድሞ ጓደኞቼ መጥተው እኔን መጠየቃቸውን ቢያቆሙም አዲስ ያገኘኋቸው ጓደኞቼ ግን ያስቡልኝና ይንከባከቡኝ ነበር።”

ሶንያ ቀስ በቀስ የመናገር ችሎታዋን መልሳ ያገኘች ሲሆን ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አደረገች። አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠመቀች። አዲስ ካፈራቻቸው ጓደኞቿ መካከል አብዛኞቹ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ስለነበሩ እነዚህ ጓደኞቿ ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ ማስተዋል ቻለች። ሶንያ “እኔም እንደነሱ መሆን እፈልጋለሁ፤ የምችለውን ሁሉ ለይሖዋ አምላክ መስጠት ይኖርብኛል!” ብላ አሰበች። በአሁኑ ወቅት ሶንያ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ላይ ትገኛለች።

ሶንያ ከራሷ ሕይወት ምን ትምህርት አገኘች? እንዲህ ብላለች፦ “በርካታ ገንዘብ ባገኝም ሥራው የፈጠረብኝ ውጥረትና ስጋት ለጭንቀት የዳረገኝ ከመሆኑም በላይ ደስታ አሳጥቶኝ ነበር። በሰማይ ከሚኖረው አባቴ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ከመመሥረት የበለጠ ምንም ነገር እንደሌለ ተገንዝቤያለሁ። በአሁኑ ጊዜ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተጠምደው ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:10) ሶንያ ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ማረጋገጥ ችላለች።