የገባውን ቃል የሚጠብቅ አምላክ
ወደ አምላክ ቅረብ
የገባውን ቃል የሚጠብቅ አምላክ
ሰዎችን ማመን ይከብድሃል? የሚያሳዝነው የምንኖረው እምነት በጠፋበት ዓለም ውስጥ ነው። የምታምነው ሰው ምናልባት በመዋሸት ወይም የገባውን ቃል በማፍረስ ጎድቶህ ከሆነ ሌሎችን ማመን ይከብድህ ይሆናል። ይሁንና የገባውን ቃል የሚፈጽምና የማያሳፍርህ ልትተማመንበት የምትችል አንድ አካል አለ። ምሳሌ 3:5 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን” በማለት ምክር ይሰጠናል። በይሖዋ ላይ ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ይታመን የነበረው ኢያሱ የተናገራቸውን ቃላት እንመርምር፤ እነዚህ ቃላት በኢያሱ 23:14 ላይ ይገኛሉ።
እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። በሙሴ እግር ተተክቶ እስራኤልን ይመራ የነበረው ኢያሱ ወደ 110 ዓመት ገደማ ሆኖታል። ኢያሱ በዚህ ረጅም ዕድሜው ከ60 ዓመታት ገደማ በፊት ይሖዋ እስራኤላውያንን ለማዳን በተአምራዊ ሁኔታ ቀይ ባሕርን ያሻገራቸውን ጨምሮ ሌሎች ያከናወናቸውን በርካታ ታላላቅ ሥራዎች ተመልክቷል። ኢያሱ ሕይወቱን መለስ ብሎ አስቦ የእስራኤልን ‘አለቆች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምንት በሙሉ’ ጠራ። (ኢያሱ 23:2) ኢያሱ በዚህ ጊዜ በዕድሜው ባገኘው ተሞክሮ ብቻ ሳይሆን በእምነት ተሞልቶ በማሰላሰሉ ጥበብ ያዘለ ሐሳብ ሊናገር ችሏል።
ኢያሱ “አሁን የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው” በማለት ተናገረ። “የምድርን ሁሉ መንገድ” የሚለው ሐረግ ሞትን ለማመልከት የገባ ዘይቤያዊ አነጋገር ነው። “ከዚህ በኋላ ብዙ ዕድሜ የለኝም” ብሎ የተናገረ ያህል ነበር። ኢያሱ እንደሚሞት ስለሚያውቅ ስላሳለፈው ሕይወት መለስ ብሎ ለማሰላሰል ረጅም ሰዓታት ብቻውን እንዳሳለፈ ምንም ጥርጥር የለውም። የእምነት ባልንጀሮቹን ሲሰናበት ምን ይናገር ይሆን?
ኢያሱ በመቀጠል “እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ [አላስቀረባችሁም] . . . አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል” በማለት ተናገረ። እነዚህን ቃላት ሊናገር የሚችለው በአምላክ ላይ ሙሉ እምነት ያለው ሰው ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢያሱ የተመለከታቸውን ነገሮች መለስ ብሎ ሲያስብ ይሖዋ ምንጊዜም የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ተገንዝቦ ነበር። * ኢያሱ የተናገራቸው ቃላት ዓላማ አንድ ነው፤ ይኸውም እስራኤላውያን ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋ እንደሚፈጽም በእሱ ላይ ሙሉ እምነት እንዲያሳድሩ ፈልጎ ነው።
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ ኢያሱ 23:14ን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ሳይፈጽም የቀረው ወይም የረሳው አንድ ተስፋ እንኳ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ተስፋዎችን ሁሉ ማምጣት፣ የዓለምን ታሪኮች መመርመር እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖሩትን ፍጥረታት ሁሉ መጠየቅ ትችላላችሁ።” እንዲህ ዓይነት ምርምር ማድረግ ቢቻል እኛም ‘ይሖዋ የገባቸው ተስፋዎች አንዳቸውም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽመዋል’ በማለት ኢያሱ የደረሰበት መደምደሚያ ላይ እንደርስ ነበር።—1 ነገሥት 8:56፤ ኢሳይያስ 55:10, 11
መጽሐፍ ቅዱስ በዓይናችን የተመለከትናቸውን ጨምሮ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ተስፋዎችን ይዟል። በተጨማሪም የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ አምላክ የገባቸውን ግሩም ተስፋዎች ይዟል። * በአምላክ ቃል ላይ የሚገኙትን እነዚህን ተስፋዎች አንተ ራስህ ለምን አትመረምርም? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ቃሉን በሚጠብቀው አምላክ ላይ እንድትተማመን ያደርግሃል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 ኢያሱ ሲፈጸሙ በዓይኑ ከተመለከታቸው ተስፋዎች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የራሳቸው የሆነ ምድር እንደሚሰጣቸው የገባው ቃል (ዘፍጥረት 12:7ን ከኢያሱ 11:23 ጋር አወዳድር)፣ ከግብፅ ነፃ እንደሚያወጣቸው የሰጠው ተስፋ (ዘፀአት 3:8ን ከ12:29-32 ጋር አወዳድር) እንዲሁም ሕዝቡን እንደሚንከባከብ የገባው ቃል ናቸው።—ዘፀአት 16:4, 13-15ን ከዘዳግም 8:3, 4 ጋር አወዳድር።
^ አን.6 አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ስለ ሰጠው ተስፋ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3, 7 እና 8ን ተመልከት።