መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
ራስተፈሪያን የነበረ ሰው የተድጎለገለ ረጅም ፀጉሩን እንዲስተካከል እንዲሁም ለነጮች የነበረውን ጥላቻ እንዲያስወግድ ያነሳሳው ምንድን ነው? በተጨማሪም ለዕፅ አዘዋዋሪዎች ገንዘብ ይሰበስብ የነበረ አንድ ዓመፀኛ ወጣት ሕይወቱን እንዲለውጥ ያስቻለው ምንድን ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።
‘የነበረኝን ጭፍን ጥላቻ አስወገድኩ።’—ሃፈኒ ዳማ
ዕድሜ፦ 34
የትውልድ አገር፦ ዛምቢያ
የኋላ ታሪክ፦ ራስተፈሪያን
የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት ዛምቢያ በሚገኝ በአንድ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው። እናቴ በጦርነት ወቅት ከናሚቢያ ሸሽታ የደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ሕዝቦች ድርጅት (ስዋፖ) አባል ሆነች። ይህ ድርጅት በዚያ ወቅት ናሚቢያን ይገዛ ከነበረው ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር ይዋጋ ነበር።
አሥራ አምስት ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ በተለያዩ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ኖሬያለሁ። በስዋፖ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ግንባር ቀደም ሆነው የነፃነት ትግሉን እንዲያቀጣጥሉ ይማሩ ነበር። ከፍተኛ የፖለቲካ ትምህርት ይሰጠን የነበረ ከመሆኑም ሌላ ነጮችን እንድንጠላ የሚያደርግ ትምህርት እንማር ነበር።
የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ በካምፑ ውስጥ ከሮም ካቶሊክ፣ ከሉተራን፣ ከአንግሊካንና ከሌሎች ሃይማኖቶች ተውጣጥቶ የተቋቋመ ቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን ፈለግኩ። ይሁንና ያነጋገርኩት ፓስተር ይህን እርምጃ እንዳልወስድ አበረታታኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አምላክ የለሽ ሆንኩ። አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ለሬጌ ሙዚቃ የነበረኝ ፍቅር እንዲሁም በጥቁር አፍሪካውያን ላይ ይደርስ የነበረውን ኢፍትሐዊ ድርጊት ለማስቀረት የነበረኝ ፍላጎት የራስተፈሪያንን እንቅስቃሴ እንድቀላቀል አደረገኝ። በመሆኑም ከዚያን ጊዜ አንስቶ ፀጉሬን ማስረዘም፣ ማሪዋና ማጨስ፣ ሥጋ ከመብላት መቆጠብና ስለ ጥቁሮች ነፃነት መስበክ ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ሕይወት መምራትም ሆነ ዓመፅ የሞላባቸውን ፊልሞች መመልከት አላቆምኩም ነበር። ከዚህም በላይ የብልግና ንግግር እናገር ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ1995 ዕድሜዬ 20 ዓመት ገደማ ሲሆን ወደፊት ልከተለው ስለሚገባ የሕይወት አቅጣጫ በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ። በመሆኑም የማገኛቸውን የራስተፈሪያን መጻሕፍት ሁሉ ማጥናቴን ተያያዝኩት። አንዳንዶቹ ጽሑፎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚጠቅሱ ቢሆንም የሚሰጡት ማብራሪያ አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም። በመሆኑም በግሌ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ወሰንኩ።
ከጊዜ በኋላ ራስታ የሆነ አንድ ጓደኛዬ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ አንድ መጽሐፍ ሰጠኝ። እኔም በግሌ ይህን መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያመሳከርኩ ማጥናት ጀመርኩ። በኋላም ከይሖዋ
ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁ ሲሆን ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ቀጠልኩ።ከብዙ ትግል በኋላ ማጨስም ሆነ ብዙ መጠጣት አቆምኩ። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ንጽሕናዬን መጠበቅ የጀመርኩ ከመሆኑም ሌላ ረጅም የነበረውን ፀጉሬን ተቆረጥኩ። እንዲሁም ወሲባዊና ዓመፅ የሞላባቸውን ፊልሞች ማየት እርግፍ አድርጌ ተውኩ፤ የብልግና ንግግሮችን መናገሬንም አቆምኩ። (ኤፌሶን 5:3, 4) ሌላው ቀርቶ ለነጮች የነበረኝን ጭፍን ጥላቻ አስወገድኩ። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) እነዚህን ለውጦች ለማድረግ ዘረኝነትን የሚያበረታታ ሙዚቃ መስማት ማቆምና ወደ ቀድሞ አኗኗሬ እንድመለስ ከሚገፋፉኝ ጓደኞቼ መራቅ ጠይቆብኛል።
እነዚህን ሁሉ ለውጦች ካደረግኩ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ የሚገኝበትን ቦታ ፈልጌ በማግኘት የሃይማኖቱ አባል መሆን እንዲፈቀድልኝ ጠየቅኩ። ይሁንና ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ያደረግኩት ውሳኔ ቤተሰቤን አላስደሰተም። እናቴ፣ የይሖዋ ምሥክር ከመሆን ይልቅ ሌላ “የክርስትና” ሃይማኖት እንድመርጥ ነገረችኝ። ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ያለው አንድ አጎቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመቀራረቤ ሁልጊዜ ይተቸኝ ነበር።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰዎችን እንዴት እንደያዘ መማሬና እሱ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጌ የሚደርስብኝን ተቃውሞና ፌዝ እንድቋቋም አስችሎኛል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩትን ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሳስተያየው እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች ሰዎች ስለ መስበክ የሚናገረውን ትእዛዝ ይፈጽማሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ የሐዋርያት ሥራ 15:14) በተጨማሪም በፖለቲካ ውስጥ አይገቡም።—መዝሙር 146:3, 4፤ ዮሐንስ 15:17, 18
ያገኘሁት ጥቅም፦ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራቴ በጣም ጠቅሞኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ማሪዋና ማጨስ ማቆሜ በየወሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ከማባከን አድኖኛል። በቅዠት ዓለም ውስጥ ገብቼ ከመዋዥቅ የተገላገልኩ ሲሆን አካላዊና አእምሯዊ ጤንነቴ በእጅጉ ተሻሽሏል።
በአሁኑ ጊዜ ሕይወቴን የምመራበት ዓላማና ግብ አለኝ፤ ይህ ደግሞ ከወጣትነቴ ጀምሮ ስመኘው የነበረ ነገር ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይበልጥ ወደ አምላክ እንደቀረብኩ ይሰማኛል።—ያዕቆብ 4:8
“ንዴቴን መቆጣጠር ተምሬያለሁ።”—ማርቲኖ ፔድሬቲ
ዕድሜ፦ 43
የትውልድ አገር፦ አውስትራሊያ
የኋላ ታሪክ፦ ዕፅ አዘዋዋሪ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ልጅ እያለሁ ብዙ ጊዜ ቤተሰቦቼ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይዘዋወሩ ነበር። በትናንሽ ከተሞችም ሆነ በትልቅ ከተማ ውስጥ የኖርኩ ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ በገጠራማ አካባቢ በሚገኝ የፕሮቴስታንቶች ሚሽን ውስጥ ኖሬያለሁ። በዚያን ጊዜ በገጠር ከአጎቶቼና ከሌሎች ዘመዶቼ ጋር ሆነን ዓሣ በማጥመድ፣ በማደን፣ መጫዎቻዎችንና ሌሎች ነገሮችን በመሥራት ያሳለፍኩት ግሩም ጊዜ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል።
አባቴ ቦክሰኛ ስለነበር መደባደብ ያስተማረኝ ገና ልጅ እያለሁ ነው። በዚህ ምክንያት ተደባዳቢ ሆንኩ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ ብዙውን ጊዜዬን የማሳልፈው በየመጠጥ ቤቱ ነበር። እኔና ጓደኞቼ ነገር ፈልገን ከሰዎች ጋር እንደባደብ ነበር። ጩቤዎችንና የቤዝ ቦል መጫወቻ ዱላዎችን ይዘን 20 ወይም ከዚያ በላይ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር እንደባደባለን።
ገንዘብ የማገኘው ዕፆችንና የወደብ ሠራተኞች የሰረቋቸውን ዕቃዎች በመሸጥ ነበር። ለዕፅ አዘዋዋሪዎች ገንዘብ እሰበስብላቸው የነበረ ሲሆን ዕዳ ያለባቸውን ሰዎች በጠመንጃና በሽጉጥ እያስፈራራሁ ለዕፅ አዘዋዋሪዎቹ ገንዘብ እቀበልላቸው ነበር። ግቤ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ መሆን ነበር። ግደል አለዚያ ትገደላለህ የሚል መርሕ ነበረኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሰማሁት ልጅ እያለሁ ነበር። ወደ 20ዎቹ ዓመታት ገደማ እያለሁ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙበትን ቦታ ታውቅ እንደሆነ እናቴን ስጠይቃት አስታውሳለሁ። ከሁለት ቀናት በኋላ ዲክሰን የተባለ የይሖዋ ምሥክር ቤቴን አንኳኳ። ከዲክሰን ጋር ለተወሰኑ ሰዓታት ከተነጋገርን በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዘኝ። በዚያ ስብሰባ ላይ የተገኘሁ ሲሆን በእንዲህ ዓይነት ስብሰባ ላይ መገኘት ከጀመርኩ አሁን ከ20 ዓመት በላይ ሆኖኛል። የማነሳቸውን ጥያቄዎች በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይመልሱልኝ ነበር።
ይሖዋ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ሌላው ቀርቶ ክፉ ለሆኑ ሰዎች እንኳ እንደሚያስብ መማሬ አስደስቶኛል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ዞር ብሎ የሚያየኝ ማንም ሰው በማይኖርበት ጊዜም እንኳ አፍቃሪ አባት የሆነው ይሖዋ እንደሚፈልገኝ ተገነዘብኩ። በተጨማሪም አኗኗሬን ካስተካከልኩ ይሖዋ ኃጢአቴን ይቅር እንደሚልልኝ ማወቄ እፎይታ አስገኝቶልኛል። በኤፌሶን 4:22-24 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከፍተኛ ለውጥ እንዳደርግ ረድቶኛል። ይህ ጥቅስ ‘አሮጌውን ስብዕናዬን አውልቄ በመጣል እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን አዲሱን ስብዕና እንድለብስ’ አበረታቶኛል።
አኗኗሬን ማስተካከል ጊዜ ወስዶብኛል። ሳምንቱን ሙሉ ዕፅ የሚባል ነገር ሳልወስድ እቆይና ቅዳሜና እሁድ ከጓደኞቼ ጋር ስሆን እሸነፋለሁ። ሕይወቴን ማስተካከል ከፈለግኩ ከጓደኞቼ መራቅ እንዳለብኝ ስለተገነዘብኩ ከተማዋን ለቅቄ ለመሄድ ወሰንኩ። አንዳንድ ጓደኞቼ ሊሸኙኝ እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፤ እኔም በሐሳባቸው ተስማማሁ። በመንገድ ላይ ሳለን ጓደኞቼ ማሪዋና ማጨስ የጀመሩ ሲሆን እኔንም እንዳጨስ ጋበዙኝ። በዚህ ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹን ልማዶች እየተውኩ እንደሆነ ገለጽኩላቸው፤ ከዚያም ድንበር ላይ ስንደርስ ብቻዬን ጉዞ ቀጠልኩ። ብዙም ሳይቆይ ጓደኞቼ በጠመንጃ በማስፈራራት ባንክ እንደዘረፉ ሰማሁ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ ከጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ካቋረጥኩ በኋላ በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ማድረግ ቀላል ሆነልኝ። በ1989 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ከተጠመቅኩ በኋላ እህቴ፣ እናቴና አባቴም ይሖዋን ማገልገል ጀመሩ።
አሁን ካገባሁ 17 ዓመት ሆኖኛል፤ ሦስት የሚያማምሩ ልጆችም አሉኝ። የሚያበሳጭ ነገር በሚያጋጥመኝ ጊዜም እንኳ ንዴቴን መቆጣጠር ተምሬያለሁ። እንዲሁም ሰዎች ‘ዘራቸው፣ ጎሣቸው ወይም ቋንቋቸው’ ምንም ይሁን ምን እነሱን መውደድ ተምሬያለሁ። (ራእይ 7:9) ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን በራሴ ሕይወት አረጋግጫለሁ፦ “በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”—ዮሐንስ 8:31, 32
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ለውጥ ለማድረግ ዘረኝነትን የሚያበረታታ ሙዚቃ መስማት ማቆም ጠይቆብኛል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
እኔና ጓደኞቼ ነገር ፈልገን ከሰዎች ጋር እንደባደብ ነበር። ጩቤዎችንና የቤዝ ቦል መጫወቻ ዱላዎችን ይዘን 20 ወይም ከዚያ በላይ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር እንደባደባለን