በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የሚያይ አምላክ

በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የሚያይ አምላክ

ወደ አምላክ ቅረብ

በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የሚያይ አምላክ

1 ነገሥት 14:13

ይሖዋ ‘ልብን ሁሉ ይመረምራል፤ ሐሳብንም ሁሉ ያውቃል።’ (1 ዜና መዋዕል 28:9) በመንፈስ መሪነት የተጻፉት እነዚህ ቃላት ይሖዋ ስለ እኛ በጥልቅ ለማወቅ የሚፈልግ መሆኑን እንድንገነዘብ ስለሚያደርጉን ልባችን በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል። ከፍጽምና እጅግ የራቅን ብንሆንም እንኳ ይሖዋ በልባችን ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ለማየት ይጥራል። ይሖዋ በ1 ነገሥት 14:13 ላይ አብያን አስመልክቶ የተናገረው ሐሳብ ለዚህ ግልጽ ማስረጃ ይሆናል።

አብያ ያደገው ክፉ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቱ ኢዮርብዓም ያቋቋመው ሥርወ መንግሥት የክህደትን ጎዳና የተከተለ ነበር። * ሰው “ፋንድያን እስኪጠፋ ድረስ እንደሚጠርግ” ሁሉ ይሖዋም የኢዮርብዓምን ቤት ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ አስቧል። (1 ነገሥት 14:10 የ1954 ትርጉም) ይሁንና አምላክ የኢዮርብዓም ቤተሰብ አባል የሆነውና በጠና ታሞ የነበረው አብያ ብቻ በወግ በማዕረግ እንዲቀበር ትእዛዝ ሰጠ። * ለምን? አምላክ ምክንያቱን ሲገልጽ “ከኢዮርብዓም ቤት ሁሉ መልካም ነገር ያገኘበት” እሱ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ነገሥት 14:1, 12, 13) ይህ ጥቅስ ስለ አብያ ማንነት ምን ይጠቁመናል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አብያ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ እንደነበር አይናገርም። ያም ቢሆን በልቡ ውስጥ አንድ መልካም ነገር ተገኝቶበት ነበር። ይህ መልካም ነገር ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። አብያ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ለአምልኮ ሄዶ አሊያም ደግሞ እስራኤላውያን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄዱ ለማገድ አባቱ ያቆማቸው ዘቦች ከቦታቸው እንዲነሱ አድርጎ ሊሆን እንደሚችል የአይሁድ ረቢዎች ጽፈዋል።

አብያ ያደረገው መልካም ነገር ምንም ይሁን ምን ሳይስተዋል አልቀረም። በአንደኛ ደረጃ ይህ መልካም ነገር እውነተኛና ከልብ የተደረገ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ በሌሎች ዘንድ ያልታየ ነበር። አብያ የወጣው “ከኢዮርብዓም ቤት” ቢሆንም በልቡ መልካም ነገር ተገኝቶበታል። አንድ ምሑር እንዲህ ብለዋል፦ “በመጥፎ አካባቢ ወይም ቤተሰብ ውስጥ ቢኖሩም መልካም ነገር ማድረጋቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች ታላቅ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።” ሌላ ምሑር ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “ሰማዩ ሲጠቁር ከዋክብት ፍንትው ብለው እንደሚታዩ እንዲሁም የሌሎች ዛፎች ቅጠል በሚረግፍበት ወቅት የጥድ ዛፍ ውበት ጎልቶ እንደሚታይ ሁሉ [የአብያ መልካምነትም] . . . በግልጽ የሚታይ ነበር።”

ከሁሉ በላይ ግን በ1 ነገሥት 14:13 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ይሖዋንና በልባችን ውስጥ የሚመለከተውን ነገር በተመለከተ አንድ ትልቅ ቁም ነገር ያስተምረናል። በአብያ ልብ ውስጥ መልካም ነገር ‘እንደተገኘበት’ አስታውስ። ይሖዋ አንድ መልካም ነገር እስኪያገኝበት ድረስ የአብያን ልብ የመረመረ ይመስላል። ከቤተሰቡ አንጻር ሲታይ አብያ “በተከመረ ጠጠር መካከል” ብቻዋን እንደተቀመጠች ዕንቁ ሊታይ እንደሚችል አንድ ምሑር ተናግረዋል። ይሖዋ የአብያን መልካምነት ከፍ አድርጎ የተመለከተው ከመሆኑም ሌላ ክፉ ከሆነ ቤተሰብ ለወጣው ለዚህ ሰው በተወሰነ መጠንም ቢሆን ምሕረት በማሳየት አክብሮታል።

ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ይሖዋ በልባችን ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ለማግኘት እንደሚጥርና ያገኘውንም መልካም ነገር ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ማወቃችን የመረጋጋት ስሜት አይፈጥርብንም? (መዝሙር 130:3) ይህን ማወቃችን፣ በጣም ትንሽም እንኳ ቢሆን በልባችን ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ለማግኘት ወደሚመረምረው ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊያነሳሳን ይገባል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ኢዮርብዓም አሥሩን ነገዶች ባቀፈው በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የጥጃ አምልኮ አቋቁሞ ነበር፤ ይህንንም ያደረገው ሕዝቡ ለይሖዋ አምልኮ ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ እንዳይሄድ ለማድረግ ሲል ነው።

^ አን.2 በጥንት ዘመን አንድ ሰው በወጉ እንዳይቀበር ከተደረገ የአምላክን ሞገስ እንዳጣ ተደርጎ ይታይ ነበር።—ኤርምያስ 25:32, 33