በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

ሰዎች እንዳገለሉህ ተሰምቶህ ያውቃል?

ሰዎች እንዳገለሉህ ተሰምቶህ ያውቃል?

አንድን ሰው ሌሎች አግልለውታል ሲባል ግለሰቡ ከእነሱ ጋር እንዲሆን አይፈልጉም ማለት ነው። ምናልባትም ይህ ሰው የቆዳ ቀለሙ፣ ዜግነቱ፣ የሚናገረው ቋንቋ ወይም ደግሞ አንዳንድ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ ከእነሱ ለየት ያለ ይሆናል። አንተስ ሌሎች እንዳገለሉህ ተሰምቶህ ያውቃል?​ *

እስቲ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ስለነበረ ሰው ልንገርህ። ይህ ሰው ሜምፊቦስቴ ይባላል። ሜምፊቦስቴ ማን እንደሆነና ሌሎች እንዳገለሉት የተሰማው ለምን እንደሆነ እንመልከት። አንተም ሌሎች እንዳገለሉህ ተሰምቶህ የሚያውቅ ከሆነ ከሜምፊቦስቴ ብዙ ነገር መማር ትችላለህ።

ሜምፊቦስቴ የዳዊት የቅርብ ጓደኛ የነበረው የዮናታን ልጅ ነው። ዮናታን በጦርነት ላይ ከመሞቱ በፊት ዳዊትን ‘እባክህ ልጆቼን ተንከባከብልኝ’ ብሎት ነበር። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ንጉሥ ሆነ። የተወሰኑ ዓመታት ካለፉ በኋላም ዮናታን የነገረው ነገር ትዝ አለው። በዚህ ወቅት ሜምፊቦስቴ በሕይወት ነበረ። ሜምፊቦስቴ በልጅነቱ ከባድ አደጋ ደርሶበት ነበር። በዚህም ምክንያት ከልጅነቱ ጀምሮ በእግሩ መራመድ አይችልም። ሜምፊቦስቴ ሰዎች እንደሚያገሉት ሊሰማው የሚችለው ለምን እንደሆነ ገባህ?​

ዳዊት ለዮናታን ልጅ መልካም ነገር ለማድረግ ፈለገ። ስለዚህ ኢየሩሳሌም ውስጥ ከእሱ ቤት አጠገብ ለሜምፊቦስቴ የሚሆን መኖሪያ ቤት አዘጋጀለት፤ ደግሞም ከዳዊት ጋር እንዲበላ ቋሚ መቀመጫ ተሰጠው። ሲባ የተባለው ሰውና ልጆቹ እንዲሁም የእሱ አገልጋዮች የሜምፊቦስቴ አገልጋዮች እንዲሆኑ ተደረገ። በእርግጥም ዳዊት የዮናታንን ልጅ በአክብሮት ይዞታል! ከዚያ በኋላ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?​

ዳዊት በቤቱ ውስጥ ችግር ገጠመው። ከዳዊት ልጆች አንዱ የሆነው አቤሴሎም በዳዊት ላይ ዓምፆ ንጉሥ ለመሆን ፈለገ። ዳዊት ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ለመሸሽ ተገደደ። ሌሎች ብዙ ሰዎችም ከዳዊት ጋር አብረው ሄዱ፤ በዚህ ጊዜ ሜምፊቦስቴም አብሮት መሄድ ፈልጎ ነበር። ከዳዊት ጋር የሄዱት እነዚህ ሰዎች ንጉሥ መሆን ያለበት ዳዊት እንደሆነ ያውቁ ነበር። ሜምፊቦስቴ ይህን ቢያውቅም በእግሩ መራመድ ስለማይችል አብሮ መሄድ አልቻለም።

ከዚያም ሲባ፣ ‘ሜምፊቦስቴ እኮ ከእኛ ጋር ያልመጣ ንጉሥ ለመሆን ፈልጎ ነው’ በማለት ለዳዊት ነገረው። ዳዊት፣ ሲባ የነገረውን ውሸት አመነ! ስለዚህ የሜምፊቦስቴን ንብረት በሙሉ ለሲባ ሰጠው። ብዙም ሳይቆይ ዳዊት አቤሴሎምን አሸንፎ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። አሁን ደግሞ ዳዊት የተፈጠረውን ነገር በተመለከተ ሜምፊቦስቴ የሚለውን ሰማ። ከዚያም ዳዊት ንብረቱን ሜምፊቦስቴና ሲባ እንዲካፈሉ ወሰነ። በዚህ ጊዜ ሜምፊቦስቴ ምን ያደረገ ይመስልሃል?​

ሜምፊቦስቴ የዳዊት ውሳኔ ትክክል አይደለም በማለት ቅሬታ አላሰማም። ሜምፊቦስቴ ንጉሡ ሥራውን በደንብ ማከናወን እንዲችል ሰላም ማግኘት እንደሚያስፈልገው ያውቃል። ስለዚህ ‘ንብረቱን በሙሉ ሲባ ይውሰደው’ አለ። ሜምፊቦስቴን በዋነኝነት አሳስቦት የነበረው የይሖዋ አገልጋይ የሆነው ዳዊት ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም መመለሱ እንጂ የንብረቱ ጉዳይ አልነበረም።

ሜምፊቦስቴ ከፍተኛ በደል ደርሶበታል። በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ ሌሎች እንደሚያገሉት ይሰማው ነበር። ይሁንና ይሖዋ ይወደውና ይንከባከበው ነበር። እኛ ከዚህ ምን እንማራለን?​— ትክክል የሆነውን ነገር እያደረግን ብንሆንም እንኳ ሌሎች ስለ እኛ ውሸት ሊናገሩ ይችላሉ። ኢየሱስ “ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ” ሲል ተናግሯል። ደግሞም ሰዎች ኢየሱስን ከመጥላትም አልፈው ገድለውታል። ትክክል የሆነውን ነገር እስካደረግን ድረስ እውነተኛ አምላክ የሆነው ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ እንደሚወዱን ምንም ጥርጥር የለውም።

ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።