በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

ከአምላክ ቃል ተማር

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች በመልሶቹ ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።

1. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር ነው። ሌሎች ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ አጥፍቶ የአምላክ ፈቃድ በሰማይና በምድር ላይ እንዲሆን ያደርጋል። በመሆኑም ጥሩ አገዛዝ ለማግኘት ያለንን ፍላጎት የሚያሟላልን የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።​—ዳንኤል 2:44ን እና ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።

የትኛውም መንግሥት ንጉሥ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው። ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን የመንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል።​—ሉቃስ 1:30-33ን አንብብ።

2. ኢየሱስ ብቃት ያለው መሪ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

የአምላክ ልጅ ብቃት ያለው መሪ ነው፤ ምክንያቱም እሱ ደግ ብሎም ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይል ነው፤ እንዲሁም ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም አለው። (ማቴዎስ 11:28-30) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ በመሄድ ሥልጣኑን እስኪያገኝ ድረስ በይሖዋ ቀኝ ሆኖ ይጠባበቅ ጀመር። (ዕብራውያን 10:12, 13) በመጨረሻም አምላክ በሰማይ ሆኖ መግዛት እንዲጀምር ሥልጣን ሰጠው።​—ዳንኤል 7:13, 14ን አንብብ።

3. ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙ አሉ?

አምላክ፣ ከኢየሱስ ጋር በመሆን በሰማይ የሚገዛ “ቅዱሳን” ተብሎ የሚጠራ አንድ ቡድን መርጧል። (ዳንኤል 7:27) ቅዱሳን በተባለው ቡድን ውስጥ እንዲታቀፉ በመጀመሪያ የተመረጡት የኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያት ነበሩ። ይሖዋ ቅዱሳን በተባለው ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን አሁንም መምረጡን ቀጥሏል። እነዚህ ሰዎች ልክ እንደ ኢየሱስ መንፈሳዊ አካል ይዘው ከሞት ይነሳሉ።​—ዮሐንስ 14:1-3ን እና 1 ቆሮንቶስ 15:42-45ን አንብብ።

ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ምን ያህል ናቸው? ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች “ትንሽ መንጋ” በማለት ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 12:32) አጠቃላይ ቁጥራቸው 144,000 ሲሆን ከኢየሱስ ጋር በመሆን ምድርን ይገዛሉ።​—ራእይ 5:9, 10⁠ን እና 14:1ን አንብብ።

4. የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው?

ኢየሱስ በ1914 መግዛት ጀምሯል። * ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ምድር ወርውሯቸዋል። (ራእይ 12:7-10, 12) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሄዷል። ጦርነት፣ የምድር ነውጥ፣ ረሃብ፣ ወረርሽኝና ዓመፅ አሁን ያለው ሥርዓት በመጨረሻዎቹ ቀኖች ላይ እንደሚገኝ የሚጠቁመው ምልክት ክፍል ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የአምላክ መንግሥት ከሚያመጣው በረከት ጥቅም ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ የንጉሡ የኢየሱስ ተከታዮች መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ይኖርባቸዋል።​—ሉቃስ 21:7, 10, 11, 31, 34, 35ን አንብብ።

5. የአምላክ መንግሥት ምን ያከናውናል?

የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው የስብከት ሥራ አማካኝነት ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክ እንዲማሩ እየረዳ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይህ መንግሥት በምድር ላይ ያለውን ክፉ ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ የኢየሱስ ታማኝ ተገዢ የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ያድናቸዋል።​—ራእይ 7:9, 10, 13-17ን አንብብ።

ይህ መንግሥት በ1,000 ዓመት ውስጥ ምድርን ቀስ በቀስ ወደ ገነትነት ይለውጣል። በመጨረሻም ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ ያስረክባል። (1 ቆሮንቶስ 15:24-26) ታዲያ አንተ ስለ አምላክ መንግሥት ልትነግረው የምትችለው ሰው አለ?​—መዝሙር 37:10, 11, 29ን አንብብ።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 እና 9 ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ኢየሱስ በ1914 መግዛት መጀመሩን የሚጠቁሙት እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 215-218 ተመልከት።