በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

አንዲት ወጣት ከዚህ ቀደም እርግፍ አድርጋ ትታው የነበረውን በልጅነቷ የቀሰመችውን ሃይማኖታዊ ትምህርት እንደገና እንድትከተል ያደረጋት ምንድን ነው? እስቲ የምትለውን እንስማ።

“አሁን ትክክለኛ ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ጀምሬያለሁ።”​ሊሳ አንድሬ

የትውልድ ዘመን፦ 1986

የትውልድ አገር፦ ሉክሰምበርግ

የኋላ ታሪክ፦ “አባካኝ ልጅ” የነበረች

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት ሉክሰምበርግ አጠገብ በምትገኝ ቤርትሮሽ በምትባል ንጹሕ የሆነች፣ ሰላም የሰፈነባትና የበለጸገች ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። ከአምስት ልጆች መካከል እኔ የመጨረሻዋ ነኝ። ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ በእኔ እንዲሁም በወንድሞቼና በእህቶቼ አእምሮ ውስጥ ክርስቲያናዊ ትምህርቶችን ለመቅረጽ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በአሥራዎቹ ዕድሜዬ መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሯቸውን ትምህርቶች በጣም መጠራጠር ጀመርኩ። ይሁንና የተሰማኝን ጥርጣሬ በቸልታ ለማለፍ ሞከርኩ፤ ቀስ በቀስ ግን እምነቴ እየተዳከመ ሄደ። ወላጆቼ ከትክክለኛው መንገድ እንዳልወጣ የቻሉትን ሁሉ ጥረት ቢያደርጉም እኔ ግን እርዳታቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳልሆን ቀረሁ። እነሱ ሳያውቁ ለሥልጣን ምንም አክብሮት ከሌላቸው ልጆች ጋር መዋል ጀመርኩ። እነዚህ ልጆች በነፃነት እንደሚኖሩ ስለተሰማኝ አኗኗራቸው አስቀናኝ። ብዙ ጊዜ ወደ ጭፈራ ቦታ እንሄድ፣ ከማንም ጋር እንተኛ፣ ዕፅ እንወስድ እንዲሁም ከልክ በላይ እንጠጣ ነበር። መጀመሪያ ላይ፣ ዓለማቸውን እየቀጩ ነው ብዬ ካሰብኳቸው ልጆች ጋር አብሬ መሆኔ አስደስቶኝ ነበር።

ሐቁን ለመናገር ግን እውነተኛ ደስታ አልነበረኝም። ከእነሱ ጋር የማሳልፈው ሕይወት ትርጉም የለሽ ነበር፤ ከመካከላችን ስለ ምንም ጉዳይ ግድ የሚሰጠው ሰው አልነበረም። እኔ ግን በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ እንደሚታየው የፍትሕ መጓደል ያሉ ነገሮች ይረብሹኝ ነበር። ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር ይበልጥ ደስታ እየራቀኝ መጣ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው፦ የ17 ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ ቀን ከፍተኛ የከንቱነት ስሜት አደረብኝ። እናቴ በሐዘን መዋጤን አስተውላ መጽሐፍ ቅዱስን እንደገና እንዳጠና ጠየቀችኝ። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች እንድመረምርና ከተማርኩት ነገር ጋር ተስማምቼ መኖር እፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ የራሴን ውሳኔ እንዳደርግ አበረታታችኝ። እንዲህ ልብ ለልብ መነጋገራችን የሕይወት አቅጣጫዬ እንዲቀየር ምክንያት ሆነ። ታላቅ እህቴ ካሮሊን እና ባሏ አኪፍ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑኝ ተስማማሁ። አኪፍ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ካደገ በኋላ ነበር፤ በልጅነቱ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚያውቀው ነገር አልነበረም። እሱ ያሳለፈውን ሕይወት ስለማውቅ በግልጽ ላነጋግረው እንደምችል ተሰማኝ፤ ይህ ደግሞ በጣም ጠቅሞኛል።

አኗኗሬ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እንደማያበቃኝ ቢገባኝም መጀመሪያ ላይ፣ በሕይወቴ የማደርገው ነገር የግል ምርጫዬ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ድርጊቴ ይሖዋን ሊያስደስተው ወይም ሊያሳዝነው እንደሚችል ተገነዘብኩ። (መዝሙር 78:40, 41፤ ምሳሌ 27:11) ሌሎች ሰዎችም በእኔ ድርጊት ስሜታቸው ሊነካ እንደሚችል ተረዳሁ።

መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እየመረመርኩ ስሄድ የአምላክ ቃል መሆኑን እንዳምን የሚያደርጉ አጥጋቢና አሳማኝ ማስረጃዎች አገኘሁ። ለምሳሌ ያህል፣ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ በትክክል ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መኖራቸውን ተረዳሁ። ይህ ያገኘሁት እውቀት በውስጤ የነበሩትን ጥርጣሬዎች እንዳስወግድ ረዳኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመርኩ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ እኔና ወላጆቼ በጀርመን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ፈቃደኛ ሠራተኛ የሆነውን ታላቅ ወንድሜን ለመጠየቅ ሄድን። ወንድሜ ምን ያህል ደስተኛ እንደሆነ ስመለከት ስሜቴ በጥልቅ ተነካ። እኔም ስመኘው የነበረው እሱ ያገኘው ዓይነት ደስታ ማግኘት ነበር! በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው የሚያገለግሉ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያየሁት ነገርም ከአእምሮዬ አይጠፋም። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ በፊት እቀርባቸው ከነበሩት አስመሳይና ፈንጠዝያ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በቀሪው ሕይወቴ ይሖዋን እንደማገለግል ቃል በመግባት ለእሱ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረብኩ። በ19 ዓመቴ በውኃ በመጠመቅ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ገለጽኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ አሁን ትክክለኛ ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ጀምሬያለሁ። ሌሎች ሰዎች ይሖዋንና እሱ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ የሰጠውን ተስፋ እንዲያውቁ መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማር ያስደስተኛል። ቤተሰቦቼም ቢሆን ተጠቅመዋል ሊባል ይችላል፤ በአሁኑ ጊዜ ስለ እኔ መጨነቅ አቁመዋል።

እርግጥ ነው፣ ከዚህ በፊት የፈጸምኳቸው ስህተቶች ከአእምሮዬ አልጠፉም፤ ይሁንና በእነሱ ላይ ላለማተኮር ጥረት አደርጋለሁ። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ይቅር ባይነትና ለእኔ ባሳየኝ ፍቅራዊ አሳቢነት ላይ ትኩረት አደርጋለሁ። ምሳሌ 10:22 ላይ በሚገኘው በሚከተለው ሐሳብ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፦ “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም።”

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ብዙ ጊዜ ወደ ጭፈራ ቦታ እንሄድ፣ ከማንም ጋር እንተኛ፣ ዕፅ እንወስድ እንዲሁም ከልክ በላይ እንጠጣ ነበር”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከዚህ በፊት የፈጸምኳቸው ስህተቶች ከአእምሮዬ አልጠፉም፤ ይሁንና በእነሱ ላይ ላለማተኮር ጥረት አደርጋለሁ”