ቅድመ ዝግጅት ማድረግና አደጋው ያስከተለውን ሁኔታ መቋቋም
የተፈጥሮ አደጋዎች ቁጥርና የሚያደርሱት ውድመት እየጨመረ ከመሆኑ አንጻር ቅድመ ዝግጅት ማድረግና አደጋው የሚያስከትለውን ሁኔታ መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው? ልንወስዳቸው የምንችላቸውን አንዳንድ እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።
ለአደጋ ከተጋለጡ አካባቢዎች ራቅ።
መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ይህ ጥበብ ያዘለ ምክር ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር በተያያዘም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። እሳተ ገሞራ እንደሚፈነዳ እንዲሁም ጎርፍ ወይም አውሎ ነፋስ እንደሚመጣ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከአደጋ ነፃ ወደሆነ ቦታ መሄዳቸው የጥበብ እርምጃ ነው። ከቤት ወይም ከሌሎች ቁሳዊ ንብረቶች ሁሉ ይበልጥ ሕይወት ውድ ነው።
አንዳንዶች ለአደጋ ከተጋለጡ አካባቢዎች ርቀው መኖር ይችሉ ይሆናል። አንድ ባለሥልጣን እንዲህ ብለዋል፦ “በምድራችን ላይ ለአደጋ የተጋለጡ አካባቢዎች የሚገኙት በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ሲሆን ወደፊትም ከባድ የሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚደርሱት በእነዚህ አካባቢዎች ነው።” ለምሳሌ፣ በጣም ዝቅ ብለው ከሚገኙ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ወይም የመሬት ገጽ ከተሰነጠቀባቸውና ለመሬት መናወጥ ከተጋለጡ ስፍራዎች ጋር በተያያዘ ይህ እውነት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ካሉ አካባቢዎች ርቀህ መኖር አሊያም ከአደጋ ነፃ ወደሆኑ ቦታዎች መዛወር የምትችል ከሆነ እንዲህ ማድረግህ ለአደጋ የመጋለጥ አጋጣሚህን በእጅጉ ሊቀንሰው ይችላል።
አስቀድመህ ተዘጋጅ።
አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ብታደርግም ያልተጠበቀ አደጋ ያጋጥምህ ይሆናል። አስቀድመህ ከተዘጋጀህ አደጋው ያስከተለውን ሁኔታ መቋቋም ቀላል ይሆንልሃል። ይህ ሐሳብ፣ በምሳሌ 22:3 ላይ ከሚገኘው ቀደም ሲል ካየነው ምክር ጋርም ይስማማል። ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር ብድግ አድርገኸው ልትወጣ የምትችል መሠረታዊ ነገሮችን የያዘ ቦርሳ አዘጋጅተሃል? በዚህ ረገድ 1-2-3 ኦቭ ዲዛስተር ኤዱኬሽን የሚለው ጽሑፍ የሚሰጠው ሐሳብ ጠቃሚ ነው፤ ጽሑፉ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ቁሳቁሶችን፣ በቀላሉ የማይበላሹ ምግቦችንና ውኃ እንዲሁም አስፈላጊ ሰነዶችን መያዝ ጠቃሚ እንደሆነ ይጠቁማል። ከዚህም በላይ በአካባቢያችሁ ምን ዓይነት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችልና በእያንዳንዱ ሁኔታ ምን ማድረግ እንደምትችሉ ከቤተሰብህ አባላት ጋር መወያየቱ ጥበብ ነው።
ከአምላክ ጋር የቀረበ ወዳጅነት ይኑርህ።
እንዲህ ማድረግህ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው . . . እሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል” ይላል። በሌላ ጥቅስ ላይ ደግሞ አምላክ “ሐዘንተኞችን የሚያጽናና” እንደሆነ ተገልጿል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ 7:6
አዎ፣ አምላክ በእሱ የሚታመኑ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች ሁሉ ያውቃል። የፍቅር አምላክ ከመሆኑም ሌላ የሚታመኑበትን ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ያበረታታል። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ ተአምር እንዲፈጽምልን ሳይሆን ኃያል የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን በጸሎት ከጠየቅነው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ይረዳናል። መንፈስ ቅዱስ፣ መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች የሚያጽናኑና መንፈሳቸውን የሚያረጋጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ወደ አእምሯቸው እንዲመጡ ይረዳቸዋል። በእርግጥም የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ እንደነበረው እንደ ዳዊት ሊሰማቸው ይችላል፤ ዳዊት “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል” ብሏል።—መዝሙር 23:4
አምላክ ተአምር እንዲፈጽምልን ሳይሆን ኃያል የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ከጸለይን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ይረዳናል
ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ይረዳዳሉ።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ አጋቦስ የተባለ አንድ ክርስቲያን ነቢይ “በምድሪቱ ሁሉ ታላቅ ረሃብ እንደሚከሰት . . . [ተናግሮ ነበር]፤ ይህም በቀላውዴዎስ ዘመን ተፈጸመ።” በወቅቱ በይሁዳ የሚገኙ በርካታ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በረሃቡ ክፉኛ ተጎድተው ነበር። በሌላ ቦታ የሚገኙት ደቀ መዛሙርት፣ ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ሲሰሙ ምን አደረጉ? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በመላክ በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች የእርዳታ አገልግሎት ለመስጠት ወሰኑ።” (የሐዋርያት ሥራ 11:28, 29) በፍቅር ተነሳስተው የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ አደረጉላቸው።
በዛሬው ጊዜም ከባድ አደጋ ሲከሰት የአምላክ አገልጋዮች ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የእምነት አጋሮቻቸውን በመርዳት ይታወቃሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የካቲት 27 ቀን 2010 ቺሊ በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ በተመታች ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ የደረሰባቸውን ለመርዳት ፈጣን እርምጃ ወስደዋል። በሱናሚ ቤቷ የወደመባት ካርላ እንዲህ ብላለች፦ “ልክ በነጋታው [የእምነት ባልንጀሮቻችን] እኛን ለመርዳት ከሌሎች አካባቢዎች መምጣታቸው በጣም የሚያበረታታና የሚያጽናና ነበር። ይሖዋ እኛን ለማበረታታት ራሳቸውን በፈቃደኝነት ባቀረቡት በእነዚህ የእምነት ባልንጀሮቻችን እንደተጠቀመ ምንም ጥርጥር የለውም። እኔም ይሖዋ እንደሚወደኝና እንክብካቤ እንደሚያደርግልኝ ተሰማኝ።” የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑት የካርላ አያት የተደረገላትን እርዳታ ከተመለከቱ በኋላ “ይህ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ለዓመታት ካየሁት ነገር ፈጽሞ የተለየ ነው” ብለዋል። እኚህ ሰው ያስተዋሉት ነገር፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኗቸው ለመጠየቅ አነሳስቷቸዋል።
ክርስቲያኖች አደጋዎች በሚደርሱበት ጊዜ እርስ በርሳቸው ይረዳዳሉ
በእርግጥም አምላክን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ያለን ወዳጅነት በአስቸጋሪ ጊዜያት በጣም ይጠቅመናል። ይሁን እንጂ በምድር ላይ የተፈጥሮ አደጋ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት።