በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትንቢትን መተርጎም የሚችለው ማን ነው?

ትንቢትን መተርጎም የሚችለው ማን ነው?

ትንቢትን መተርጎም የሚችለው ማን ነው?

በታላቁ እስክንድር ዘመን ከባድ የሚባለው እንቆቅልሽ የጎርዲያን ቋጠሮ እንደነበረ ይነገራል። ይህን ውስብስብ ቋጠሮ መፍታት የቻለ ሰው ጠቢብና ድል አድራጊ እንደሚሆን ይታመን ነበር። * በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ከሆነ እስክንድር አንድ ጊዜ ሰይፉን ሰንዝሮ ውስብስቡን ቋጠሮ በመበጠስ እንቆቅልሹን ፈቶታል።

ባለፉት ዘመናት በሙሉ ጠቢባን፣ አስቸጋሪ የሆኑ ቋጠሮዎችን ብቻ ሳይሆን እንቆቅልሾችን ለመፍታትና ትንቢቶችን ለመተርጎም አልፎ ተርፎም ስለ መጪው ጊዜ ለመተንበይ ይሞክሩ ነበር።

ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ከአቅማቸው በላይ ነበር። ለምሳሌ የባቢሎን ጠቢባን፣ ንጉሥ ቤልሻዛር ባዘጋጀው ድል ያለ ድግስ ላይ በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ የታየውን ተአምራዊ ጽሑፍ ፍቺ ማወቅ አልቻሉም ነበር። ትንቢታዊውን መልእክት መተርጎም የቻለው ‘የተቋጠረውን በመፍታት’ ችሎታው የታወቀው አረጋዊው የይሖዋ አምላክ ነቢይ ዳንኤል ብቻ ነበር። (ዳንኤል 5:12 የ1954 ትርጉም) በባቢሎን ግዛት ላይ የሚመጣውን ጥፋት የሚገልጸው ይህ ትንቢት በዚያኑ ሌሊት ተፈጽሟል!​—ዳንኤል 5:1, 4-8, 25-30

ትንቢት ምንድን ነው?

ትንቢት የሚለው ቃል ወደፊት ስለሚፈጸም ነገር በቅድሚያ የተነገረ ሐሳብ እንዲሁም ከመፈጸሙ በፊት የተመዘገበ ክስተት የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። እውነተኛ ትንቢት፣ በመንፈስ መሪነት የተነገረ ወይም የተጻፈ መልእክት እንዲሁም መለኮታዊውን ፈቃድና ዓላማ የሚያስታውቅ መግለጫ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መሲሑ መገለጥና ስለ ማንነቱ፣ ስለዚህ “ሥርዓት መደምደሚያ” እንዲሁም ስለ አምላክ የፍርድ መልእክቶች የሚገልጹ ትንቢቶች ተመዝግበዋል።​—ማቴዎስ 24:3፤ ዳንኤል 9:25

በዛሬው ጊዜ ያሉት “ጠቢባን” ማለትም በሳይንስ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በጤና፣ በፖለቲካ፣ በአካባቢ ጥበቃና በሌሎችም በርካታ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎች ስለ መጪው ጊዜ ለመተንበይ ይሞክራሉ። እነዚህ ሰዎች ከሚናገሯቸው ትንቢቶች አብዛኞቹ በመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን የሚሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡም ሳያንገራግር ይቀበላቸዋል፤ ይሁንና እነዚህ ትንቢቶች የምሁራን ግምቶችና የግል አስተያየቶች ከመሆን አይዘሉም። በተጨማሪም ምሁራኑ ለሚያቀርቡት ለእያንዳንዱ አስተያየት የዚያኑ ያህል በርካታ የተቃውሞ ሐሳቦችና የመከራከሪያ ነጥቦች መነሳታቸው አይቀርም። በእርግጥም ስለ ወደፊቱ ጊዜ መተንበይ ከባድ ነገር ነው።

የእውነተኛ ትንቢት ምንጭ

ታዲያ እውነተኛ ትንቢቶች የሚመነጩት ከየት ነው? ሊተረጉማቸው የሚችለውስ ማን ነው? ሐዋርያው ጴጥሮስ “በመጽሐፍ ያለው የትንቢት ቃል ሁሉ ማንም ሰው በገዛ ራሱ መንገድ የሚተረጉመው አይደለም” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 1:20 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) እዚህ ላይ ‘መተርጎም’ ተብሎ የተቀመጠው የግሪክኛ ቃል “መፍታት፣ መግለጥ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን “ታስሮ የነበረ ነገር እንደተለቀቀ ወይም እንደተፈታ” የሚገልጽ ሐሳብ ያስተላልፋል። በመሆኑም ዚ አምፕሊፋይድ ኒው ቴስታመንት ጴጥሮስ የተናገረውን ሐሳብ “የትኛውንም የቅዱሳን መጻሕፍት ትንቢት ማንም በግሉ . . . ሊፈታው አይችልም” በማለት ተርጉሞታል።

ብልሃት በተሞላበት መንገድ ውስብስብ የሆነ ቋጠሮ የሚሠራ አንድ መርከበኛ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። መርከበኛው ሥራውን ሲጨርስ፣ ስለ ቋጠሮ ብዙም የማያውቅ አንድ ሰው ገመዱ እንዴት እንደተቋጠረ ማየት ቢችልም እንዴት እንደሚፈታ ግን ሊያውቅ አይችልም። በተመሳሳይም ሰዎች ውስብስብ ወደሆኑ ችግሮች የሚመሩ አንዳንድ ሁኔታዎችን ማየት ቢችሉም እነዚህ ሁኔታዎች ምን እንደሚያስከትሉ እርግጠኞች መሆን አይችሉም።

እንደ ዳንኤል ያሉት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ትንቢት የተናገሩ የጥንት ነቢያት በዘመናቸው የነበረውን ሁኔታ በግላቸው ካጤኑ በኋላ ወደፊት የሚከሰቱትን ውስብስብ ነገሮች በተመለከተ ትንቢት ለመናገር ሙከራ አላደረጉም። የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ የተናገሩት ነገር ፍጻሜውን እንዲያገኝ ለማድረግ ቢሞክሩ ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ ትንቢት በምናባቸው የፈጠሩት ይሆን ነበር። ይህ ከሆነ ደግሞ የተናገሩት ትንቢት ከሰው አእምሮ የፈለቀ ስለሚሆን ምንጩ ፍጽምና የጎደለው ይሆናል። ከዚህ በተቃራኒ ጴጥሮስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ።”​—2 ጴጥሮስ 1:21

‘የሕልም ትርጓሜ ከአምላክ ይገኛል’

ከ3,700 ዓመታት በፊት በግብፅ አገር ሁለት ሰዎች በወህኒ ተጥለው ነበር። ሁለቱም ሰዎች ትኩረት የሚስብ ሕልም አዩ። በአገሩ ከነበሩት ጠቢባን ጋር መገናኘት ስለማይችሉ አብሯቸው ለታሠረው ለዮሴፍ “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጕምልን ሰው አጣን” በማለት ጭንቀታቸውን አካፈሉት። የአምላክ አገልጋይ የነበረው ዮሴፍም “የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር የሚገኝ አይደለምን?” በማለት ሕልማቸውን እንዲነግሩት ጠየቃቸው። (ዘፍጥረት 40:8) ውስብስብ የሆነ ቋጠሮን መፍታት የሚችለው ተሞክሮ ያለው መርከበኛ እንደሆነ ሁሉ ትንቢትን መተርጎም የሚችለውም ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ቀድሞውኑም ቢሆን የእነዚህ ትንቢቶች ምንጭ አምላክ ነው፤ በሌላ አባባል ትንቢቶቹን የቋጠራቸው እሱ ራሱ ነው። በመሆኑም የትንቢቶቹን ትርጉም ሊያሳውቀን ወይም ቋጠሮውን ሊፈታልን የሚችለው እሱ ብቻ ነው። በእርግጥም፣ ዮሴፍ “የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር የሚገኝ” እንደሆነ መናገሩ ትክክል ነበር።

ታዲያ “የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር” ይገኛል የምንለው ለምንድን ነው? እንዲህ እንድንል የሚያደርጉን በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትንቢቶችን ብቻ ሳይሆን ፍጻሜያቸውንም ተመዝግቦ እናገኛለን። አንድ መርከበኛ ቋጠሮው እንዴት እንደሚፈታ ካብራራልን ቋጠሮውን መፍታት ቀላል እንደሚሆን ሁሉ የዚህ ዓይነት ትንቢቶችን ፍጻሜ መረዳትም ቀላል ነው።​—ዘፍጥረት 18:14፤ 21:2

ሌሎች ትንቢቶችን ደግሞ በዙሪያቸው ያለውን ሐሳብ በመመርመር ትርጉማቸውን መረዳትና ማወቅ ይቻላል። ለምሳሌ፣ ነቢዩ ዳንኤል “ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ . . . በዐይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ [ባለው] አውራ ፍየል” ተወግቶ ሲወድቅ የሚያሳይ ትንቢታዊ ራእይ ተመልክቶ ነበር። በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው አውራው በግ “የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት” የሚያመለክት ሲሆን ፍየሉ ደግሞ ‘የግሪክን ንጉሥ’ ያመለክታል። (ዳንኤል 8:3-8, 20-22) ይህ ትንቢት ከተነገረ ከ200 ዓመት በላይ ካለፈ በኋላ በትንቢቱ ላይ “ትልቁ ቀንድ” የተባለው ታላቁ እስክንድር ፋርስን ወረረ። እስክንድር በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወታደራዊ ዘመቻውን እያካሄደ ሳለ ይህን ትንቢት እንደተመለከተና ትንቢቱ ስለ እሱ የሚናገር መሆኑን እንደተቀበለ አይሁዳዊው የታሪክ ምሁር ጆሴፈስ ጽፏል።

“የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር” ይገኛል የምንልበት ሌላም ምክንያት አለ። የይሖዋ አምላክ ታማኝ አገልጋይ የነበረው ዮሴፍ አብረውት የታሰሩት ሰዎች ያዩትን ግራ የሚያጋባ ሕልም ትርጉም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ማስተዋል ችሎ ነበር። (ዘፍጥረት 41:38) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች የአንድን ትንቢት ትርጉም በተመለከተ እርግጠኛ ካልሆኑ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ከጸለዩ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክን ቃል በትጋት ያጠናሉ እንዲሁም ይመረምራሉ። በዚህ መንገድ ከአምላክ በሚያገኙት ድጋፍ አማካኝነት የአንዳንድ ትንቢቶችን ትርጉም ለመረዳት የሚያስችሏቸውን ጥቅሶች ማግኘት ይችላሉ። የትንቢቶቹ ትርጉሞች ልዩ ችሎታ ባላቸው ሰዎች አማካኝነት የሚገኙ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የትንቢቶቹ ትርጉም ግልጽ የሚሆነው በአምላክ መንፈስና በቃሉ አማካኝነት ስለሆነ ትርጓሜው የተገኘው ከአምላክ ነው ማለት ይችላል። ትርጓሜው፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በሆነ ሐሳብ ላይ የተመሠረተም ሆነ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከሚናገሩ ሰዎች የተገኘ አይደለም።​—የሐዋርያት ሥራ 15:12-21

በምድር ላይ ያሉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች አንድን ትንቢት መቼ ሊረዱት እንደሚገባ የሚወስነውና የሚመራቸው አምላክ መሆኑም “የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር” ይገኛል እንድንል ያደርገናል። የአንድን ትንቢት ትርጉም ትንቢቱ ከመፈጸሙ በፊት፣ እየተፈጸመ ባለበት ወቅት ወይም ከተፈጸመ በኋላ መረዳት ይቻላል። ትንቢቶቹን ያስነገራቸው ወይም የቋጠራቸው አምላክ ስለሆነ በትክክለኛው ጊዜ ማለትም በራሱ ጊዜ ይፈታቸዋል።

ስለ ዮሴፍና ስለ ሁለቱ እስረኞች በሚገልጸው ታሪክ ላይ ዮሴፍ ሕልማቸውን የፈታላቸው ሕልሙ ከመፈጸሙ ከሦስት ቀናት በፊት ነበር። (ዘፍጥረት 40:13, 19) ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ፣ የኃያሉን ፈርዖንን ሕልም ለመፍታት በፊቱ በቀረበበት ጊዜ ምግብ የሚትረፈረፍባቸው ሰባት ዓመታት ሊጀምሩ ተቃርበው ነበር። ዮሴፍ በአምላክ መንፈስ እርዳታ የፈርዖንን ሕልሞች በመፍታቱ በትንቢት የተነገረውን የተትረፈረፈ ምርት ለመሰብሰብ ዝግጅት ሊደረግ ችሏል።​—ዘፍጥረት 41:29, 39, 40

ሌሎች ትንቢቶችን ደግሞ የአምላክ አገልጋዮች ሙሉ በሙሉ ሊረዷቸው የሚችሉት ከተፈጸሙ በኋላ ብቻ ነው። በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተፈጸሙ በርካታ ክንውኖች እሱ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት በትንቢት ተነግረው የነበረ ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱ ትንቢቶቹን ሙሉ በሙሉ የተረዱት ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ነበር። (መዝሙር 22:18፤ 34:20፤ ዮሐንስ 19:24, 36) በሌላ በኩል ደግሞ በ⁠ዳንኤል 12:4 መሠረት አንዳንድ ትንቢቶች ‘ዕውቀት እስከሚበዛበት እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የታተሙ’ ሆነው ይቆያሉ። አሁን የምንኖረው እነዚያ ትንቢቶች እየተፈጸሙ ባሉበት ዘመን ነው። *

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና አንተ

ዮሴፍና ዳንኤል በዘመናቸው በነበሩት ነገሥታት ፊት ቀርበው ብሔራትንና መንግሥታትን የሚመለከቱ ትንቢታዊ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ክርስቲያኖችም የትንቢት አምላክ የሆነው የይሖዋ ቃል አቀባዮች በመሆን በዘመናቸው ለነበሩ ሕዝቦች መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ለዚህ መልእክት ቀና ምላሽ የሰጡ ሰዎች ታላቅ ጥቅም አግኝተዋል።

በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች የሚገልጸውን ትንቢታዊ መልእክት በመላው ዓለም እያወጁ እንዲሁም ኢየሱስ የዚህን “ሥርዓት መደምደሚያ” በተመለከተ የተናገረው ትንቢት በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ መሆኑን ለሕዝቦች ሁሉ እየተናገሩ ነው። (ማቴዎስ 24:3, 14) ይህ ትንቢት ምን እንደሆነና አንተን እንዴት እንደሚነካህ ታውቃለህ? ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንዱ የሆነውን ይህን ትንቢት መረዳትና ከእሱም ጥቅም ማግኘት እንድትችል የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 የግሪክ አፈ ታሪክ እንደሚገልጸው ከሆነ ጎርድየም የምትባለው የፍርግያ ዋና ከተማ መሥራች የነበረው ጎርዲየስ፣ ሠረገላውን ከአንድ ግንድ ጋር ካሰረው በኋላ ገመዱን ውስብስብ በሆነ መንገድ ቋጥሮት ነበር፤ ይህን ቋጠሮ መፍታት የቻለ ሰው እስያን ድል አድርጎ እንደሚቆጣጠር ይታመን ነበር።

^ አን.19 በግንቦት 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣው “ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ እያየህ ነው” በሚለው ርዕስ ሥር ያሉትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዮሴፍና ዳንኤል ትንቢቶችን ባብራሩበት ጊዜ ትርጓሜውን የገለጠላቸው አምላክ መሆኑን ተናግረዋል