ተአምራት ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው?
ተአምራት ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው?
“ተአምር የሚለው ቃል ፍቺ በራሱ ከሳይንስ ጋር ይጋጫል።”—ሪቻርድ ዶከንዝ፣ ፐብሊክ ኣንደርስታንዲንግ ኦቭ ሳይንስ የተባለው መስክ የቀድሞ ፕሮፌሰር
“ተአምራት እንደሚፈጸሙ ማመን ምክንያታዊ ነው። በተአምራት ማመን አንድ ሃይማኖት ሊያፍርበት የሚገባ ነገር አይደለም፤ እንዲያውም ተአምራት፣ አምላክ ፍጥረታቱን እንደሚወድና ከእነሱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳላቆመ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።”—ሮበርት ላርመር፣ የፍልስፍና ፕሮፌሰር
“ተአምራት እንደሚፈጸሙ ታምናለህ?” ከላይ ያሉት ሐሳቦች እንደሚያሳዩት ሰዎች በዚህ ረገድ ያላቸው አመለካከት በጣም የተለያየ ነው። አንተስ ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ?
“አዎ፣ አምናለሁ” ብለህ በልበ ሙሉነት ለመናገር አትደፍር ይሆናል። ምክንያቱም እንዲህ ማለትህ በአጉል እምነት እንደተተበተብክ ወይም መሃይም እንደሆንክ አድርጎ እንደሚያስቆጥርህ ይሰማህ ይሆናል። እንደ አንተ የሚሰማቸው ብዙዎች ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ተአምራት እንደሚፈጸሙ ሙሉ እምነት ይኖርህ ይሆናል። ሙሴ ቀይ ባሕርን ለሁለት እንደከፈለው የሚገልጸውን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመዘገቡት ተአምራት ታምን ይሆናል። እንዲያውም ዛሬም ተአምራት እንደሚፈጸሙ ይሰማህ ይሆናል። በቅርቡ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደጠቆመው “በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ሰዎች (ለምሳሌ ያህል ከዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪዎች ሦስት አራተኛ የሚሆኑትና ከብሪታንያ ነዋሪዎች 38 በመቶ የሚሆኑት) ተአምራት እንደሚፈጸሙ አሁንም ያምናሉ።” (ዘ ካምብሪጅ ከምፓንየን ቱ ሚራክልስ፣ አርታኢ ግሬም ትዌልፍትሪ) ከዚህም ሌላ በተአምራት የሚያምኑት ክርስቲያኖች ብቻ አይደሉም። ብሪታኒካ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ዎርልድ ሪሊጅንስ እንደገለጸው “ሁሉም ሃይማኖቶች ማለት ይቻላል በተአምራዊ ክስተቶች ያምናሉ።”
አሊያም ደግሞ የሚከተለው ዓይነት አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ሐሳብ ትጋራ ይሆናል፦ “ተአምራት ሊፈጸሙም ላይፈጸሙም ይችላሉ፤ ደግሞም ይህ ጉዳይ ያን ያህል አያሳስበኝም! በእኔ ሕይወት ውስጥ ተአምራት እንደሚፈጸሙ አልጠብቅም!” ለመሆኑ ተአምራት ትኩረትህን ሊስቡት የሚገባው ለምንድን ነው?
እስቲ አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ መድኃኒት ያልተገኘለት በሽታ ይዞሃል እንበል። ከበሽታህ ሊያድንህ የሚችል አዲስ ዓይነት መድኃኒት እንደተገኘ የሚገልጽ ዘገባ ተአማኒ በሆነ አንድ የሕክምና መጽሔት ላይ አነበብክ፤ ታዲያ የተወሰነ ጊዜና ጉልበት መሥዋዕት ማድረግ ቢጠይቅብህም ይህ ነገር እውነት መሆኑን ማጣራቱ ተገቢ አይመስልህም? በተመሳሳይም በቅርቡ አስደናቂ የሆኑ ተአምራት እንደሚፈጸሙ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል። እነዚህ ተአምራት በምድር ላይ ያሉ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ የሚነኩ ናቸው። ታዲያ የተወሰነ ጊዜና ጉልበት መሥዋዕት በማድረግ ይህ ተስፋ እምነት የሚጣልበት መሆኑን ማረጋገጡ ተገቢ አይመስልህም?
መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት እንደሚፈጸሙ የሚገልጻቸው እነዚህ ተአምራት ምን እንደሆኑ ከመመርመራችን በፊት ግን ከተአምራት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ሦስት የተለመዱ የተቃውሞ ሐሳቦችን እንመልከት።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተአምር ምንድን ነው?
የታወቁት ሰብዓዊም ሆነ ተፈጥሯዊ ኃይሎች በሙሉ ሊያከናውኑት ከሚችሉት ነገር እጅግ የላቀ ክንውን ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከሰው በላይ በሆነ ኃይል እንደተፈጸመ ይነገራል።