በመስጠት የሚገኘው ደስታ
“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35
አንዳንዶች ገናን የሚያከብሩበት ምክንያት
ኢየሱስ እንደተናገረው መስጠት ለሰጪውም ሆነ ለተቀባዩ ደስታ ያስገኛል። ብዙዎች በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም ሲሉ ገናን በሚያከብሩበት ወቅት ስጦታ መስጠትን ትልቅ ቦታ ይሰጡታል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ጥናት መሠረት ባለፈው ዓመት በነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ ወቅትም እንኳ በአየርላንድ እያንዳንዱ ቤተሰብ የገና ስጦታ ለመግዛት በአማካይ ከ660 የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚያወጣ ተገምቷል።
ይህን ማድረግ ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው?
ብዙዎች የገና ስጦታ መስጠት ደስታ ከማምጣት ይልቅ ውጥረት እንደሚጨምር ይሰማቸዋል። እንዲህ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ብዙ ሸማቾች ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ስጦታዎችን እንዲገዙ ጫና እንደሚደረግባቸው ይሰማቸዋል። ከዚህም ሌላ ሰዎች ስጦታዎችን የሚገዙት በተመሳሳይ ጊዜ ስለሆነ በገበያ ቦታዎች የሚኖረው ጭንቅንቅና ረጅም ሰልፍ ብዙዎችን ያበሳጫቸዋል።
ሊረዱን የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች
ኢየሱስ “ሰጪዎች ሁኑ” ብሏል። * (ሉቃስ 6:38) ኢየሱስ በዓመት ውስጥ በተወሰነ ጊዜ ላይ ስጦታ እንድንሰጥ ስለሚጠበቅብን ብቻ ይህን እንድናደርግ አላስተማረም። ኢየሱስ ተከታዮቹን በራሳቸው ተነሳሽነት መስጠትን ልማድ እንዲያደርጉ መክሯቸዋል።
“አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።” (2 ቆሮንቶስ 9:7) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንታኔ የሚሰጥ አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው ጳውሎስ የሰጠው ምክር ፍሬ ሐሳብ “አንድ ሰው ማንኛውንም ነገር ‘ተገዶ’ ማለትም የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ስለተሰማው ብቻ ሊሰጥ አይገባም” የሚል ነው። ‘በደስታ የሚሰጥ’ የሚለው ሐሳብ፣ በተወሰነ ወቅት ላይ አንድ ነገር የመስጠት ግዴታ እንዳለብን ተሰምቶን የምንሰጠው ስጦታ ተገቢ እንዳልሆነ ያሳያል፤ አብዛኛውን ጊዜ በገና ወቅት የሚሰጠው ስጦታ ግን የዚህ ዓይነት መንፈስ ይንጸባረቅበታል።
“ለመስጠት ፈቃደኝነቱ ካለ ስጦታው ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው አንድ ሰው ባለው መጠን ሲሰጥ እንጂ በሌለው መጠን ሲሰጥ አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 8:12) ክርስቲያኖች ውድ የሆኑ ስጦታዎችን ለመግዛት ሲሉ ዕዳ ውስጥ እንዲገቡ አምላክ አይጠብቅባቸውም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው የሚሰጠው “ባለው መጠን” በሚሆንበት ጊዜ ስጦታው “ይበልጥ ተቀባይነት” ያለው ይሆናል። ይህ በበዓላት ሰሞን ከሚታየው ተበድሮ የመግዛት ልማድ ምንኛ የተለየ ነው!
^ စာပိုဒ်၊ 8 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “ስጡ” ብለው ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ እንዲህ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ ቀጣይ የሆነ ድርጊትን ያመለክታል። በመሆኑም ኢየሱስ የተጠቀመበትን ቃል ሙሉ ትርጉም ለማስተላለፍ ሲባል አዲስ ዓለም ትርጉም “ሰጪዎች ሁኑ” በማለት ተርጉሞታል።