የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ ነው?
የሞት መንደፊያ
ስለ ሞት ማውራት ደስ የሚያሰኝ ነገር አይደለም። ብዙ ሰዎች ይህን ርዕሰ ጉዳይ ማንሳት አይፈልጉም። ሆኖም ማናችንም ብንሆን ይዋል ይደር እንጂ ከሞት ጋር መፋጠጣችን አይቀርም። የሞት መንደፊያ ደግሞ ኃይለኛና የሚያሠቃይ ነው።
የወላጅን፣ የትዳር ጓደኛንና የልጅን ሞት መቼም ቢሆን ልንቀበለው የምንችለው ነገር አይደለም። የሰውን ሕይወት የሚቀጥፍ ነገር በድንገት ወይም በጊዜ ሂደት ሊከሰት ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሞት ከባድ ሥቃይ የሚያስከትልብን ሲሆን ሁኔታውን መለወጥ አለመቻላችን ደግሞ ሐዘናችንን ይበልጥ መራራ ያደርገዋል።
በመኪና አደጋ አባቱን ያጣው አንቶንዮ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው ቤትህን ቆልፎ ቁልፉን የወሰደብህ ያህል ነው። ላፍታም እንኳ ወደ ቤትህ መመለስ አትችልም። በሐዘን ከመብሰልሰል በቀር ምንም ምርጫ የለህም። ይህ ልትሸሸው የማትችለው እውነታ ነው። ‘ይሄማ በፍጹም መሆን የለበትም’ ብለህ ስለምታስብ ሁኔታውን መቀበል ይከብድሃል፤ ሆኖም ምንም ማድረግ አትችልም።”
በ47 ዓመቷ ባሏን በሞት በመነጠቋ ምክንያት ለሐዘን የተዳረገችው ዶርቲ በውስጧ ለተፈጠሩት አንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ወሰነች። የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪ እንደመሆኗ መጠን ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ ነው የሚል እምነት አልነበራትም። ሆኖም ከሞት በኋላ ስላለው ሁኔታ ግልጽ የሆነ መልስ የላትም። በመሆኑም በቤተ ክርስቲያኗ ያለን አንድ የአንግሊካን ቄስ “ስንሞት ምን እንሆናለን?” ስትል ጠየቀችው። እሱም “ይህን ማንም በእርግጠኝነት አያውቅም። ወደፊት የሚሆነውን ጊዜ ያሳየናል” ሲል መለሰላት።
በእርግጥ ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ነው? ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ መሆን አለመሆኑን በትክክል ማወቅ የምንችልበት መንገድ ይኖር ይሆን?