መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
“ይሖዋ አልረሳኝም”
የትውልድ ዘመን፦ 1922
የትውልድ አገር፦ ስፔን
የኋላ ታሪክ፦ ሃይማኖታዊ ትምህርት አስተማሪ
የቀድሞ ሕይወቴ፦
የተወለድኩት በሰሜናዊ ስፔን በቢልባኦ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ነው። በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት አራት ልጆች መካከል ሁለተኛ ልጅ ነኝ። ቤተሰባችን አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆን እኔ ደግሞ በየዕለቱ በቤተ ክርስቲያን በሚካሄደው ሥርዓተ ቁርባን ላይ እገኝ ነበር። በ23 ዓመቴ አስተማሪ ሆንኩ፤ ይህን ሙያ በጣም እወደው የነበረ ሲሆን ለ40 ዓመት በመምህርነት አገልግያለሁ። አስተምራቸው ከነበሩ ትምህርቶች መካከል ይበልጥ የሚያስደስተኝ ስለ ካቶሊክ ሃይማኖት ማስተማር ነበር፤ ስለሆነም ማታ ማታ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርት አስተምር የነበረ ሲሆን ልጃገረዶች ሥርዓተ ቁርባን ለመፈጸም እንዲበቁ የሚያስችላቸውን ትምህርት እሰጥ ነበር።
አሥራ ሁለት ዓመት አስደሳች የትዳር ሕይወት ካሳለፍኩ በኋላ ባለቤቴን በሞት ስላጣሁ አራት ሴት ልጆቼን ብቻዬን ለማሳደግ ተገደድኩ። በዚህ ወቅት ዕድሜዬ ገና 33 ዓመት ነበር! ከምከተለው የካቶሊክ እምነት ማጽናኛ ለማግኘት ሞከርኩ፤ ሆኖም በአእምሮዬ ውስጥ የሚጉላሉ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩ። እንዲህ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር፦ ‘ክርስቶስ ቤዛ ሆኖ ከዋጀን ለምን እንሞታለን? ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱ ከሆነ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጸልየው ለምንድን ነው?’ ከሁሉም በላይ ያስጨንቀኝ የነበረው ደግሞ ‘አምላክ በምንሞትበት ጊዜ ፍርድ የሚሰጠን ከሆነ ከሰማይ፣ ከመንጽሔ ወይም ከሲኦል ወጥተን ለመጨረሻው ፍርድ ዳግም ፊቱ የምንቀርበው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ነበር።
አንዳንድ ቄሶችን ይህን ጥያቄ ጠይቄያቸው ነበር። አንድ ቄስ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠኝ፦ “እኔ የማውቀው ነገር የለም። ጳጳሱን ጠይቂው። ደግሞስ ስለዚህ ጉዳይ አወቅሽ አላወቅሽ ምን ለውጥ ያመጣል? በአምላክ ታምኛለሽ አይደል? በቃ የፈለገው ይሁን!” እኔ ግን ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት ጥረት ማድረጌን ቀጠልኩ። ከጊዜ በኋላ ጀስዊቶች፣ ጴንጤቆስጤዎችና ግኖስቲኮች በሚሰጧቸው የሃይማኖት ትምህርቶች ላይ ተገኝቻለሁ። ይሁን እንጂ ለጥያቄዎቼ አጥጋቢ መልስ የሰጠኝ የለም።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ አንዲት የሰባት ዓመት ተማሪ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዘችኝ። እዚያ ያየሁትና የሰማሁት ነገር ያስደሰተኝ ቢሆንም ሕይወቴ በውጥረት የተሞላ ስለነበር በወቅቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበረኝ ግንኙነት ተቋረጠ። ከሁለት ዓመት በኋላ ጁዋንና ማይታ የተባሉ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ባልና ሚስት በሬን አንኳኩ። ለሦስት ወራት ያህል ከእነሱ ጋር በጥያቄዎቼ ላይ ሰፊ ውይይት ሳደርግ ከቆየሁ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።
እያንዳንዱን የጥናት ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት እጠብቅ ነበር! የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንደሚያስተምሩ ለማረጋገጥ የምማረውን እያንዳንዱን ነገር ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በመጠቀም በጥልቀት እመረምር ነበር። ብዙም ሳይቆይ ለብዙ አሥርተ ዓመታት በሃይማኖት ትምህርቶች ግራ ተጋብቼ እንደነበር ተረዳሁ። ቀደም ሲል አምንበት በነበረውና ከመጽሐፍ ቅዱስ በተማርኩት ነገር መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ስገነዘብ በጣም ተረበሽኩ። በጥልቅ ሥር እንደሰደደ ዛፍ የነበረው የቀድሞ እምነቴ ተነቅሎ ሲጣል ሳይ ውስጤ ታወከ።
ውድ ሀብት እንዳገኘሁ አውቄ ነበር
ከዚያም ሁለተኛው ባሌ በጠና ታሞ ሞተ። በዚሁ ወቅት አካባቢ ጡረታ የወጣሁ ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ ቢልባኦን ለቅቄ ሄድኩ። ጁዋንና ማይታም ወደ ሌላ አካባቢ ሄዱ። የሚያሳዝነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ተቋረጠ። ይሁንና ውድ ሀብት እንዳገኘሁ አውቄ ስለነበር ይህ እውነት ፈጽሞ ከአእምሮዬ አልጠፋም።
ከ20 ዓመት ገደማ በኋላ ይኸውም የ82 ዓመት አረጋዊ ሳለሁ ጁዋንና ማይታ ወደ ቢልባኦ ስለተመለሱ ሊጠይቁኝ መጡ። ከእነሱ ጋር ዳግም በመገናኘቴ በጣም ተደሰትኩ! ይሖዋ እንዳልረሳኝ ተገነዘኩ፤ ጥናቴንም ቀጠልኩ። ብዙውን ጊዜ አንድን ጥያቄ ደጋግሜ እጠይቃቸው ስለነበር ጁዋንና ማይታ እኔን በትዕግሥት መያዝ ጠይቆባቸዋል። ቀደም ሲል አምንባቸው የነበሩትን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ከውስጤ ለማስወጣት መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ መወያየት አስፈልጎኛል። እግረ መንገዴንም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለጓደኞቼና ለቤተሰቤ በሚገባ የማስረዳት ችሎታ ማዳበር እፈልግ ነበር።
በመጨረሻም በ87 ዓመቴ ተጠመቅኩ፤ ይህ ቀን በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩበት ዕለት ነው። የተጠመቅኩት በአንድ ትልቅ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ነበር። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ለመጠመቅ የተዘጋጀነውን ሰዎች በቀጥታ የሚመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር አቀረበ። ንግግሩን ስሰማ አለቀስኩ። ይሖዋ በቀጥታ እያነጋገረኝ እንዳለ ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር። ከተጠመቅኩ በኋላ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው ደስታቸውን ገለጹልኝ፤ የሚገርመው ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹን አላውቃቸውም ነበር!
ያገኘሁት ጥቅም፦
ከድሮ ጀምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ “መንገድ” መሆኑን አውቅ ነበር። (ዮሐንስ 14:6) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ይሖዋን አወቅኩ፤ ኢየሱስም መንገድ ሆኖ የሚያደርሰን ወደ እሱ ነው። አሁን አምላክን እንደ ውድ አባቴና ወዳጄ በመመልከት ወደ እሱ መጸለይ እችላለሁ። ወደ ይሖዋ ቅረብ * የተባለውን መጽሐፍ ማንበቤ በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። መጀመሪያ ላይ ይህን መጽሐፍ በአንድ ሌሊት አንብቤ ጨረስኩት! ይሖዋ ምን ያህል መሐሪ አምላክ እንደሆነ ስገነዘብ ልቤ በጥልቅ ተነካ።
ሃይማኖታዊ እውነትን ለማግኘት ለረጅም ጊዜ ያደረግኩትን ፍለጋ ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ኢየሱስ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ትዝ ይለኛል፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።” (ማቴዎስ 7:7) አሁን ለረጅም ጊዜ በአእምሮዬ ውስጥ ሲመላለሱ ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ ያገኘሁ ሲሆን ያገኘሁትንም እውቀት ለሌሎች ማካፈል እጅግ ያስደስተኛል።
ዕድሜዬ 90 ዓመት ቢሆንም በመንፈሳዊ ገና ልጅ እንደሆንኩ ይሰማኛል። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረገው በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ስገኝ ልዩ ስሜት ይፈጥርብኛል፤ ምክንያቱም በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ውድ የሆነ እውቀት የምገበይ ከመሆኑም ሌላ ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር የመጨዋወት አጋጣሚ አገኛለሁ። ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን በድጋሚ አስተማሪ መሆን እፈልጋለሁ። (ራእይ 21:3, 4) በተለይም ደግሞ በሞት ያጣኋቸው ዘመዶቼ ዳግም ሕያው ሆነው ማየትና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለእነሱ ማስተማር በጣም የምጓጓለት ነገር ነው። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ይሖዋ በስተእርጅናዬ ምን ውድ ስጦታ እንደሰጠኝ ልነግራቸው እናፍቃለሁ!
^ አን.15 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።