አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .
ኃይለኞች ምስኪኖችን እንዲጨቁኑ አምላክ የፈቀደው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምስኪን ሰዎች በኃይለኞች እንደተጨቆኑ የሚገልጹ አንዳንድ የሚያሳዝኑ ዘገባዎችን ይዟል። ምናልባትም ስለ ናቡቴ የሚናገረው ታሪክ ትዝ ይልህ ይሆናል። * በአሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ነበር፤ ሚስቱ ኤልዛቤል፣ አክዓብ የናቡቴን የወይን እርሻ ቦታ እንዲወርስ ለማድረግ ብላ ናቡቴንና ወንዶች ልጆቹን አስገደለቻቸው፤ ይህን ስታደርግ ንጉሡ በዝምታ ተመልክቷታል። (1 ነገሥት 21:1-16፤ 2 ነገሥት 9:26) አምላክ ሰዎች ይህን ያህል ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ሲጠቀሙበት ዝም ያለው ለምንድን ነው?
‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም።’—ቲቶ 1:2
እስቲ አንድ ወሳኝ ነጥብ እንመልከት፦ አምላክ ሊዋሽ አይችልም። (ቲቶ 1:2) ‘ታዲያ ይህ ሐሳብ፣ ክፉዎች ከሚፈጽሙት የጭቆና ድርጊት ጋር ምን የሚያያይዘው ነገር አለ?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አምላክ በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ፣ በእሱ ላይ ማመፅ አስከፊ ውጤት ይኸውም ሞት እንደሚያስከትል አስጠንቅቆ ነበር። ልክ አምላክ እንደተናገረው በኤደን ገነት ዓመፅ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ሞት የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታ ሆኗል። ደግሞም የሰው ልጅ የመጀመሪያውን የሞት ጽዋ የተጎነጨው፣ ቃየን አቤልን ሲገድል በፈጸመው ዓመፅ ምክንያት ነው።—ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 4:8
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ያለውን የሰው ልጆች ታሪክ የአምላክ ቃል ጠቅለል አድርጎ ሲገልጸው እንዲህ ይላል፦ “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።” (መክብብ 8:9) እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸው ተረጋግጧል? ይሖዋ ሕዝቡ የሆኑትን የእስራኤልን ብሔር፣ ነገሥታቶቻቸው ጨቋኝ እንደሚሆኑና እነሱም ከዚህ የተነሳ ወደ አምላክ እንደሚጮኹ አስጠንቅቋቸው ነበር። (1 ሳሙኤል 8:11-18) ጠቢብ የነበረው ንጉሥ ሰለሞን እንኳ በሕዝቡ ላይ ከባድ ግብር ጭኖባቸው ነበር። (1 ነገሥት 11:42, 43፤ 12:3, 4) እንደ ክፉው ንጉሥ እንደ አክዓብ ያሉ ነገሥታት ደግሞ ከዚህ የከፋ ጭቆና ፈጽመዋል። እስቲ ይህን አስብ፦ አምላክ እነዚህ የጭቆና ድርጊቶች እንዳይደርሱ ቢከላከል ኖሮ በተዘዋዋሪም ቢሆን ቃል አባይ አይሆንም ነበር?
“ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።”—መክብብ 8:9
በተጨማሪም ሰይጣን፣ ‘ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ጥቅማቸው እስካልተነካ ድረስ ብቻ ነው’ የሚል ክስ መሰንዘሩን አስታውስ። (ኢዮብ 1:9, 10፤ 2:4) አምላክ፣ ሌሎች በአገልጋዮቹ ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንዳይኖራቸው ቢያደርግ ሰይጣን ያቀረበው ክስ ትክክል እንደሆነ የሚያረጋግጥ አይሆንም ነበር? አምላክ በማንም ሰው ላይ ጭቆና እንዳይደርስ ቢከላከል ኖሮ ከአሁኑ የከፋ ውሸት እንዲስፋፋ ምክንያት አይሆንም ነበር? አምላክ እንዲህ ያለ ጥበቃ የሚያደርግ ከሆነ ብዙዎች፣ የሰው ልጅ ያለ አምላክ እርዳታ ራሱን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር ይችላል ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል የሚናገረው የዚህን ተቃራኒ ማለትም የሰው ልጅ ፈጽሞ ራሱን ማስተዳደር እንደማይችል ነው። (ኤርምያስ 10:23) በእርግጥም የአምላክ መንግሥት መምጣቱ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ግፍ የሚያከትመው ያን ጊዜ ብቻ ነው።
ታዲያ ይህ ሲባል አምላክ ጭቆናን አስመልክቶ ምንም ዓይነት እርምጃ አይወስድም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። እስቲ አምላክ ያደረጋቸውን ሁለት ነገሮች ተመልከት፦ አንደኛ፣ ጭቆና ምን እንደሆነ በደንብ ገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤልዛቤል በናቡቴ ላይ ያደረገችው እያንዳንዱ ነገር በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍር አድርጓል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ እንዲህ ያሉ ክፉ ድርጊቶችን የሚያስፋፋው ማንነቱን ለመደበቅ የሚፈልግ አንድ ኃይለኛ ገዥ እንደሆነ ይናገራል። (ዮሐንስ 14:30፤ 2 ቆሮንቶስ 11:14) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አካል ሰይጣን ዲያብሎስ በማለት ይጠራዋል። አምላክ ክፋትንና ጭቆናን እንዲሁም የእነዚህን ነገሮች እውነተኛ መንስኤ ግልጽ በማድረግ በክፋት ድርጊቶች ከመካፈል እንድንርቅ ይረዳናል። በዚህ መንገድ፣ ከፊታችን የተዘረጋውን ዘላለማዊ በረከት እንዳናጣ ይጠብቀናል።
ሁለተኛ፣ አምላክ ጭቆና እንደሚያበቃ አስተማማኝ ተስፋ ሰጥቶናል። አምላክ፣ አክዓብንና ኤልዛቤልን ጨምሮ እነሱን የመሳሰሉ ሌሎች ብዙ ሰዎች ያደረጉትን ማጋለጡ፣ በእነሱ ላይ መፍረዱና እነሱን መቅጣቱ ክፉ አድራጊዎችን በሙሉ የሚቀጣበት ቀን እንደሚመጣ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት እንዲኖረን ያደርጋል። (መዝሙር 52:1-5) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ክፋት እሱን በሚወዱ ሰዎች ላይ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ በቅርቡ መልሶ እንደሚያስተካክል የሚገልጽ አስተማማኝ ተስፋ ሰጥቶናል። * በዚያ ወቅት ታማኙ ናቡቴና ልጆቹ ግፍ በማይኖርባት ገነት የሆነች ምድር ላይ ይኖራሉ።—መዝሙር 37:34
^ አን.3 “በእምነታቸው ምሰሏቸው” የሚለውን በዚህ እትም ውስጥ ያለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.8 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።