በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

መጸለይ እንዳለብህ ይሰማሃል?

መጸለይ እንዳለብህ ይሰማሃል?

‘አምላክ የማስበውንና የሚያስፈልገኝን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የሚያውቅ ከሆነ ለምን እጸልያለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በእርግጥ ይህን መጠየቅህ ተገቢ ነው። ደግሞም ኢየሱስ “አምላክ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:8) የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊትም ቢሆን ይህን ስለተገነዘበ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣ እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 139:4) ታዲያ ወደ አምላክ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎትን አስመልክቶ ምን እንደሚናገር እንመልከት። *

“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕቆብ 4:8

 ጸሎት ከአምላክ ጋር ያቀራርበናል

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ * አምላክ ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ ቢናገርም ትኩረት የሚያደርገው ስለ አገልጋዮቹ መረጃ በመሰብሰብ ላይ ብቻ አለመሆኑንም ይገልጻል። (መዝሙር 139:6፤ ሮም 11:33) ገደብ የለሽ የማስታወስ ችሎታ ያለው አምላክ ከኮምፒውተር ፈጽሞ የተለየ ነው፤ ኮምፒውተር የግለሰቦችን መረጃ ቢሰበስብም ስለ ግለሰቦቹ ምንም ዓይነት ስሜት የለውም። አምላክ ግን ከእሱ ጋር እንድንቀራረብ ስለሚፈልግ ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበው የውስጥ ሐሳባችንን ማወቅ ነው። (መዝሙር 139:23, 24፤ ያዕቆብ 4:8) ይሖዋ የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች በደንብ የሚያውቅ ቢሆንም ኢየሱስ ወደ አባቱ እንዲጸልዩ ተከታዮቹን ያበረታታቸው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 6:6-8) ሐሳባችንን ለፈጣሪያችን ባካፈልነው መጠን ይበልጥ ከእሱ ጋር እንቀራረባለን።

አንዳንድ ጊዜ በጸሎት መጠየቅ የምንፈልገውን ነገር በትክክል መግለጽ ይቸግረን ይሆናል። በዚህ ጊዜ አምላክ መግለጽ ያቃተንን ስሜት ይረዳል፤ እንዲሁም ስላለንበት ሁኔታ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ አስፈላጊውን እርዳታ ይሰጠናል። (ሮም 8:26, 27፤ ኤፌሶን 3:20) አምላክ ይህን የሚያደርገው ለእኛ ቶሎ ግልጽ በማይሆንልን መንገድ ቢሆንም እንኳ የእኛ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ስለምንረዳ ከእሱ ጋር እንደተቀራረብን ይሰማናል።

አምላክ ለሁሉም ጸሎቶች መልስ ይሰጣል?

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት እንደሚመልስ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጠናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ጸሎቶችን የማይሰማው ለምን እንደሆነ ይነግረናል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንቷ እስራኤል ዓመፅ በጣም ተስፋፍቶ በነበረበት ዘመን አምላክ ነቢዩ ኢሳይያስን ለሕዝቡ የሚከተለውን መልእክት እንዲናገር አዝዞት ነበር፦ “አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል።” (ኢሳይያስ 1:15) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ለአምላክ ሕግ ንቀት የሚያሳዩ ወይም ተገቢ ያልሆነ ዓላማ በውስጣቸው ይዘው የሚጸልዩ ሰዎች በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት እናገኛለን ብለው መጠበቅ አይችሉም።—ምሳሌ 28:9፤ ያዕቆብ 4:3

በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:14) ታዲያ እንዲህ ሲባል አምላክ፣ አገልጋዮቹ ያቀረቡትን ልመና ሁሉ ወዲያውኑ ይፈጽምላቸዋል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። አምላክ ‘ሥጋውን የሚወጋውን እሾህ’ እንዲያስወግድለት ሦስት ጊዜ ጸልዮ የነበረውን የሐዋርያው ጳውሎስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። (2 ቆሮንቶስ 12:7, 8) ጳውሎስ የጠቀሰው የሥጋ መውጊያ ሥር የሰደደ የዓይን ሕመም ሊሆን ይችላል። ይህ ሕመም ምን ያህል ሥቃይ አስከትሎበት እንደሚሆን መገመት ይቻላል! ጳውሎስ የመፈወስ ስጦታ የተሰጠው ከመሆኑም ሌላ የሞተ ሰው ጭምር አስነስቶ ነበር፤ ያም ሆኖ የራሱን ሕመም ችሎ መኖር ግድ ሆኖበታል። (የሐዋርያት ሥራ 19:11, 12፤ 20:9, 10) ጳውሎስ ላቀረበው ልመና መልስ የተሰጠው እሱ በፈለገው መንገድ ባይሆንም እንኳ አምላክ የሰጠውን ምላሽ በአመስጋኝነት ተቀብሏል።—2 ቆሮንቶስ 12:9, 10

“በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”—1 ዮሐንስ 5:14

እውነት ነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ አንዳንድ ግለሰቦች ጸሎታቸው ተአምራዊ በሆነ መንገድ መልስ አግኝቷል። (2 ነገሥት 20:1-7) ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት መልስ በዚያ ዘመንም እንኳ ሁልጊዜ የሚያጋጥም አይደለም። አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች አምላክ ለጸሎታቸው መልስ እንዳልሰጣቸው ሆኖ ሲሰማቸው ተጨንቀው ነበር። ንጉሥ ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከ መቼ ድረስ ለዘላለሙ ትረሳኛለህ?” በማለት ጠይቆ ነበር። (መዝሙር 13:1) ይሁን እንጂ ታማኙ ዳዊት፣ ይሖዋ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ እንደደረሰለት ሲገነዘብ በአምላክ ላይ የነበረው የመተማመን ስሜት እንደገና ተጠናክሯል። ዳዊት በዚያው ጸሎት ላይ “እኔ ግን በጸናች ፍቅርህ እታመናለሁ” በማለት አክሎ ተናግሯል። (መዝሙር 13:5) ልክ እንደ ዳዊት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም አምላክ ለልመናቸው መልስ እንደሰጣቸው እስኪያስተውሉ ድረስ በጸሎት መጽናት ሊኖርባቸው ይችላል።—ሮም 12:12

 አምላክ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጥባቸው መንገዶች

አምላክ በእርግጥ የሚያስፈልገንን ነገር ስንጠይቀው መልስ ይሰጠናል።

ምክንያታዊና አፍቃሪ የሆነ አንድ ወላጅ ልጆቹ የጠየቁትን ነገር ሁሉ እነሱ በፈለጉበት ጊዜ አያደርግም። በተመሳሳይም አምላክ ለልመናችን መልስ የሚሰጠን እኛ ባሰብነው መንገድ ወይም በጠበቅነው ጊዜ ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት በእርግጥ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በትክክለኛው ጊዜና በተገቢው መንገድ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሉቃስ 11:11-13

አምላክ ለልመናችን መልስ የሚሰጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኝ ሐሳብ አማካኝነት ሊሆን ይችላል

አምላክ ለእኛ ግልጽ ባልሆነ መንገድ መልስ ሊሰጠን ይችላል።

ከአንድ ችግር ለመገላገል ከጸለይን በኋላ ችግሩ ለረጅም ጊዜ ቢቀጥልስ? ከችግሩ እንድንላቀቅ ስላላደረገን ብቻ ይሖዋ ጭራሽ መልስ አልሰጠንም ብለን መደምደም ይኖርብናል? በፍጹም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእኛ ግልጽ ባልሆኑ መንገዶች እየደገፈን ሊሆን ስለሚችል፣ እነዚህን መንገዶች ለማስተዋል ጥረት ማድረጋችን የተሻለ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ምናልባት አንድ አሳቢ ወዳጃችን ልክ በተገቢው ጊዜ ላይ እኛን ለመርዳት የቻለውን ሁሉ አድርጎ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 17:17) ይሖዋ ይህ አሳቢ ወዳጃችን በሰዓቱ እንዲደርስልን አነሳስቶት ይሆን? አምላክ ለልመናችን መልስ የሚሰጥበት ሌላው መንገድ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኝ ሐሳብ አማካኝነት ሊሆን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሐሳብ ያጋጠመንን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም የምንችልበትን መንገድ እንድናስተውል ሊረዳን ይችላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

አምላክ በተገቢው ጊዜ ላይ እኛን ለመርዳት አሳቢ በሆኑ ወዳጆቻችን ሊጠቀም ይችላል

ብዙውን ጊዜ አምላክ ችግሩን በማስወገድ ፋንታ ለመቋቋም የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ እንዳያመጣ በመፍራት መከራውን እንዲያስወግድለት አባቱን ለምኖት ነበር፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ መከራውን ከማስወገድ ይልቅ የሚያበረታታው መልአክ ልኮለታል። (ሉቃስ 22:42, 43) በተመሳሳይም አምላክ፣ በጣም በሚያስፈልገን ሰዓት ላይ አንድ የምንቀርበውን ወዳጃችንን ተጠቅሞ ሊያበረታታን ይችላል። (ምሳሌ 12:25) እንዲህ ዓይነቱ መልስ ቶሎ ግልጽ ላይሆንልን ስለሚችል አምላክ ለጸሎቶቻችን መልስ የሚሰጥበትን መንገድ በንቃት መከታተል ይኖርብናል።

አንዳንድ ጸሎቶች መልስ የሚያገኙት አምላክ በወሰነው ጊዜ ላይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ትሑት ለሆኑ ግለሰቦች “በተገቢው ጊዜ” ሞገሱን እንደሚያሳያቸው ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 5:6) በመሆኑም ከልብ ለመነጨ ልመናችን ቶሎ መልስ እንዳልሰጠን በሚሰማን ጊዜ ይሖዋ የእኛ ሁኔታ እንደማያሳስበው አድርገን መደምደም የለብንም። ከዚህ ይልቅ አፍቃሪው ፈጣሪያችን እጅግ የላቀ እውቀት ያለው በመሆኑ ለልመናችን መልስ የሚሰጠን ለእኛ በጣም የተሻለውን ጊዜ ግምት ውስጥ አስገብቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለው።

“በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።”—1 ጴጥሮስ 5:6

ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ልጅህ ብስክሌት እንድትገዛለት ለመነህ እንበል። ታዲያ ልመናውን ወዲያውኑ ትፈጽምለታለህ? ብስክሌት ለመንዳት ዕድሜው እንዳልደረሰ ከተሰማህ መግዛቱን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ልትወስን ትችላለህ። ውሎ አድሮ ግን ለልጅህ ብስክሌት ብትገዛ የተሻለ እንደሆነ ከተሰማህ ብስክሌቱን ትገዛለታለህ። በተመሳሳይም መጸለያችንን ከቀጠልን አምላክ ተገቢ የሆነውን ‘የልባችንን መሻት’ በተገቢው ጊዜ ይፈጽምልናል።—መዝሙር 37:4

ይሖዋ እንደሚሰማህ እርግጠኛ ሁን

እውነተኛ ክርስቲያኖችን ጸሎት ባለው ጥቅም ላይ ጥርጣሬ እንዳያድርባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳስባል። ምናልባት አንዳንዶች ‘ያልተነካ ግልግል ያውቃል’ ይሉ ይሆናል። እውነት ነው፣ ከአንድ ችግር መላቀቅ ሲያቅተን ወይም አንድ ዓይነት ግፍ ሲደርስብን አምላክ መልስ የሚሰጥበትን ጊዜ መጠበቅ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ይሁንና ኢየሱስ፣ በጸሎት ስለ መጽናት ያስተማረውን ነገር ማስታወሳችን ጥሩ ነው።

ኢየሱስ ክፉ ወደሆነ አንድ ዳኛ ፍትሕ ለማግኘት ትመላለስ ስለነበረች አንዲት ችግረኛ መበለት የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሮ  ነበር። (ሉቃስ 18:1-3) ዳኛው መጀመሪያ ላይ እሷን ለመርዳት ፈቃደኛ ባይሆንም በመጨረሻ ግን “ይህች መበለት ሁልጊዜ እየመጣች ስለምታስቸግረኝ እንደምንም ብዬ ፍትሕ እንድታገኝ ማድረግ አለብኝ፤ አለበለዚያ በየጊዜው እየመጣች አሳሬን ታበላኛለች” ብሎ አሰበ። (ሉቃስ 18:4, 5) ጥቅሱ በተጻፈበት የመጀመሪያ ቋንቋ መሠረት ዳኛው የመበለቷን አቤቱታ የሰማው በምሳሌያዊ አገላለጽ “ዓይኑ ሥር እንዳትመታው” ወይም “ስሙን እንዳታጠፋው” * ብሎ ነው። አንድ ክፉ ዳኛ እንኳ ስሙ እንዳይጠፋ በማሰብ ብቻ አንዲትን ድሃ መበለት የሚረዳት ከሆነ አፍቃሪው አምላካችን ‘ቀንና ሌሊት ወደ እሱ ለሚጮኹ’ ሰዎች ፍትሕን ምንኛ አብልጦ አይሰጣቸው! ኢየሱስ እንደተናገረው አምላክ “በፍጥነት ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል።”—ሉቃስ 18:6-8

“ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል።”—ሉቃስ 11:9

ምንም እንኳ አምላክ እንዲረዳን ወይም አንድ ነገር እንዲያደርግልን መለመን የሚታክተን ጊዜ ቢኖርም ተስፋ ቆርጠን ማቆም የለብንም። በጸሎት የምንጸና ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን እጅ ለማየት ያለን ፍላጎት ምን ያህል ከልብ የመነጨ እንደሆነ እናሳያለን። በተጨማሪም አምላክ ለልመናችን መልስ የሚሰጥባቸውን መንገዶች ማስተዋል እንጀምራለን፤ ይህ ደግሞ ይበልጥ ከእሱ ጋር እንድንቀራረብ ያደርገናል። አዎን፣ በእምነት መጸለያችንን ከቀጠልን ይሖዋ ተገቢ ለሆነው ጸሎታችን መልስ እንደሚሰጠን እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—ሉቃስ 11:9

^ አን.3 አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማልን ከፈለግን የእሱን መሥፈርቶች ለማሟላት ከልብ መጣር አለብን። እንዲህ ካደረግን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደተገለጸው የጸሎትን ኃይል በራሳችን ሕይወት ማየት እንችላለን። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ተመልከት፤ ወይም www.ps8318.com/am የተሰኘውን ድረ ገጻችንን ጎብኝ።

^ አን.5 የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።

^ አን.22 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በእስራኤል የነበሩ ዳኞች ለመበለቶችና አባት ለሌላቸው ልጆች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አምላክ ይጠብቅባቸው ነበር።—ዘዳግም 1:16, 17፤ 24:17፤ መዝሙር 68:5