የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ ከሚገባው በላይ አድርጎልኛል
የ17 ዓመት ወጣት ነበርኩ፤ እንደ አብዛኞቹ እኩዮቼ ሁሉ የሚያሳስቡኝና የሚያጓጉኝ ነገሮች ነበሩ። ከጓደኞቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ መዋኘትና እግር ኳስ መጫወት ያስደስተኝ ነበር። ሆኖም አንድ ምሽት ላይ የተፈጠረው ነገር ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለወጠው። በደረሰብኝ አሰቃቂ የሞተር ብስክሌት አደጋ የተነሳ ከአንገቴ በታች ያለው ሰውነቴ በሙሉ ሽባ ሆነ። ይህ ከሆነ 30 ዓመት ገደማ ያለፈ ቢሆንም ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአልጋ ቁራኛ ሆኛለሁ።
ያደግኩት በምሥራቃዊ ስፔን የባሕር ዳርቻ በምትገኝ አሊካንቴ የተባለች ከተማ ውስጥ ነው። የቤተሰብ ሕይወታችን የተመሰቃቀለ ስለነበር አብዛኛውን የወጣትነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት ጎዳና ላይ ነበር። ቤታችን አቅራቢያ አንድ ጎሚስታ ነበር። እዚያ ይሠራ ከነበረ ሆሴ ማሪያ ከተባለ አንድ ሰው ጋር ጓደኛ ሆንኩ። ይህ ሰው አፍቃሪ ሲሆን በገዛ ቤተሰቤ ያላገኘሁትን ትኩረት ይሰጠኝ ነበር። የ20 ዓመት ታላቄ ቢሆንም በአስቸጋሪ ጊዜያት እንደ ወንድሜ የማየው እውነተኛ ጓደኛዬ ነበር።
በወቅቱ ሆሴ ማሪያ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምሮ ነበር። የአምላክን ቃል እንደሚወድ ግልጽ ነው፤ ብዙ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ይነግረኝ ነበር። በአክብሮት አዳምጠው የነበረ ቢሆንም ለሚናገረው ነገር ያን ያህል ትኩረት አልሰጠሁም። ወጣት ስለነበርኩ ልቤ በተለያዩ ነገሮች ተከፋፍሎ ነበር። ነገር ግን ሁኔታዎች በዚያው አልቀጠሉም።
ሕይወቴን የለወጠ አደጋ
ስለደረሰብኝ አደጋ ብዙ ማውራት አልፈልግም። በአጭሩ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር የሞኝነትና የግዴለሽነት ድርጊት ፈጽሜአለሁ። በአንድ ጀምበር ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። በአንድ ወቅት ሮጬ የማልጠግብ ወጣት የነበርኩ ቢሆንም ሁኔታዬ በአንዴ ተቀይሮ ከሆስፒታል አልጋ የማልወርድ ሽባ ሰው ሆንኩ። ይህን አምኖ መቀበል በጣም ከበደኝ። ‘አሁን የእኔ መኖር ምን ትርጉም አለው?’ ብዬ ራሴን እጠይቅ ነበር።
ሆሴ ማሪያ መጥቶ የጠየቀኝ ሲሆን በአቅራቢያዬ በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሆስፒታል መጥተው እንዲጠይቁኝ ወዲያው ዝግጅት አደረገ። ወንድሞች ዘወትር ይጠይቁኝ ስለነበር ልቤ በጣም ተነካ። ልዩ የሕክምና ክትትል ከሚደረግበት ክፍል እንደወጣሁ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። የሰው ልጆች ለምን እንደሚሠቃዩና እንደሚሞቱ እንዲሁም አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ ለምን እንደፈቀደ እውነቱን አወቅኩ። በተጨማሪም አምላክ ወደፊት መላዋ ምድር ፍጹም በሆኑ የሰው ልጆች እንደምትሞላና ማንም “ታምሜአለሁ” የማይልበት ጊዜ እንደሚመጣ ስለገባው ቃል ተማርኩ። (ኢሳይያስ 33:24) በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሩህ ተስፋ ታየኝ።
ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ፈጣን እድገት አደረግኩ። ለአካል ጉዳተኞች በተዘጋጀ ልዩ ተሽከርካሪ ወንበር በመጠቀም የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው አንዳንድ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ከእነሱ ጋር በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመርኩ። ኅዳር 5, 1988 በ20 ዓመቴ ልዩ በሆነ የመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ተጠመቅኩ። ይሖዋ አምላክ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ታዲያ አድናቆቴን እንዴት ላሳይ እችላለሁ?
የአካል ጉዳተኛ ብሆንም እድገት ማድረጌን ቀጠልኩ
የነበርኩበት ሁኔታ በይሖዋ አገልግሎት የቻልኩትን ሁሉ ከማድረግ እንዲያግደኝ አልፈቀድኩም። እድገት ማድረግ እፈልግ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) መጀመሪያ ላይ፣ ቤተሰቦቼ አዲስ እምነት በመያዜ ይቃወሙኝ ስለነበር እድገት ማድረግ ከብዶኝ ነበር። ሆኖም የእምነት ባልንጀሮቼ የሆኑት መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ምንጊዜም ከጎኔ ነበሩ። አንድም ስብሰባ እንዳያመልጠኝ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ንቁ ተሳትፎ እንዳደርግ ይጥሩ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ግን የ24 ሰዓት የባለሙያ ክትትል እንደሚያስፈልገኝ ግልጽ ሆነ። ከብዙ ፍለጋ በኋላ ከአሊካንቴ በስተ ሰሜን 160 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ቫሌንሲያ በተባለች ከተማ ውስጥ የምፈልገው ዓይነት የአካል ጉዳተኞች መንከባከቢያ ማዕከል አገኘሁ። ይህ ማዕከል ቋሚ መኖሪያዬ ሆነ።
የአልጋ ቁራኛ መሆኔ እምነቴን ለሌሎች ከማካፈል አላገደኝም
የአልጋ ቁራኛ ብሆንም ይሖዋን ማገልገሌን ለመቀጠል ቆርጬ ነበር። ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን የገንዘብ እርዳታና ሌሎች ድጎማዎችን በመጠቀም ኮምፒውተር ገዝቼ አልጋዬ አጠገብ እንዲገጠም አደረግኩ። ሞባይል ስልክም ገዛሁ። እንክብካቤ የሚያደርግልኝ ሰው ሁልጊዜ ጠዋት ላይ ኮምፒውተሬንና ስልኬን ይከፍትልኛል። ኮምፒውተር የምጠቀመው ጆይስቲክ በሚባል መሣሪያ እገዛ ሲሆን ይህን ደግሞ የማንቀሳቅሰው በአገጬ ነው። በተጨማሪም በአፌ የምይዘው ልዩ የሆነ ዘንግ አለኝ። ኮምፒውተር ላይ መጻፍም ሆነ ስልክ መደወል ስፈልግ በዚህ ዘንግ እጠቀማለሁ።
እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የጠቀሙኝ እንዴት ነው? አንደኛ ነገር፣ jw.org የተባለውን ድረ ገጽና የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትን መጠቀም አስችለውኛል። እነዚህን መሣሪያዎች በጣም ጠቃሚ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ! በየዕለቱ በርከት ያሉ ሰዓታትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማጥናትና ምርምር በማድረግ አሳልፋለሁ፤ ይህም ስለ አምላክና ግሩም ስለሆኑት ባሕርያቱ በቀጣይነት እውቀት እንድቀስም አስችሎኛል። እንዲሁም የብቸኝነት ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማኝ ሁልጊዜ ከድረ ገጹ ላይ የሚያበረታታ ሐሳብ አገኛለሁ።
ከዚህ ተጨማሪም ኮምፒውተሬ የጉባኤ ስብሰባዎችን ለመከታተልም ሆነ ተሳትፎ ለማድረግ አስችሎኛል። በመሆኑም ሐሳብ መስጠት፣ መጸለይ፣ ንግግር ማቅረብ ብሎም የጉባኤያችን የመጠበቂያ ግንብ አንባቢ ሆኜ ማገልገል እችላለሁ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በአካል መገኘት ባልችልም እንኳ ከጉባኤው ጋር አብሬ እንዳለሁ ይሰማኛል።
ስልክና ኮምፒውተር ያለኝ መሆኑ በስብከቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ እንዳደርግም ረድቶኛል። እርግጥ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት ከቤት ወደ ቤት መሄድ አልችልም። ሆኖም ይህ እንዳልሰብክ አላገደኝም። እነዚህን መሣሪያዎች በመጠቀም እምነቴን ለሌሎች ማካፈል ችያለሁ። እንዲያውም በስልክ የማደርጋቸው ውይይቶች በጣም ስለሚያስደስቱኝ የጉባኤያችን ሽማግሌዎች በስልክ ለመስበክ የሚደረጉትን ዘመቻዎች እንዳስተባብር ጠይቀውኛል። እነዚህ ዘመቻዎች በተለይ ከቤት መውጣት ለማይችሉ የጉባኤው አባላት ጠቃሚ ሆነዋል።
ይሁንና ሕይወቴ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ላይ
ብቻ ያተኮረ አይደለም። ጓደኞቼ በየቀኑ እየመጡ የሚጠይቁኝ ከመሆኑም ሌላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ የሚፈልጉ ዘመዶቻቸውንና ሌሎች ሰዎችን ይዘው ይመጣሉ። እንዲያውም ብዙ ጊዜ እኔ እንዳወያያቸው ይጠይቁኛል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አንዳንድ ቤተሰቦች መጥተው የሚጠይቁኝ ከመሆኑም ሌላ በቤተሰብ አምልኳቸው እንድካፈል ይጋብዙኛል። በተለይ ትናንሽ ልጆች አልጋዬ አጠገብ ቁጭ ብለው ይሖዋን የሚወዱት ለምን እንደሆነ ሲናገሩ መስማት ያስደስተኛል።ብዙ ሰዎች መጥተው ስለሚጠይቁኝ ደስ ይለኛል። ቅርብም ሆነ ሩቅ ያሉ ጓደኞቼ እኔን ለማየት ስለሚመጡ ከክፍሌ ሰው አይጠፋም። ሰዎች የሚያሳዩኝ እንዲህ ያለው ፍቅራዊ አሳቢነት በማዕከሉ ውስጥ እንክብካቤ የሚሰጡትን ሰዎች እንደሚያስገርማቸው መገመት ይቻላል። ይሖዋ እንዲህ በመሰለ ግሩም የወንድማማች ማኅበር ውስጥ እንድታቀፍ ስላስቻለኝ በየዕለቱ አመሰግነዋለሁ።
እጅ አልሰጠሁም
ሰዎች ሰላምታ ከሰጡኝ በኋላ ስላለሁበት ሁኔታ ሲጠይቁኝ “እንደምታዩኝ ነው፤ አሁንም እጅ አልሰጠሁም!” እላቸዋለሁ። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለ ትግል ያለብኝ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ። ሁኔታቸው ወይም እንቅፋት የሚሆንባቸው ነገር ይለያይ እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች ትግል ማድረግ ይኸውም ‘መልካሙን የእምነት ገድል መጋደል’ አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 6:12) ይህን ሁሉ ዓመት በትግሉ እንድጸና የረዳኝ ምንድን ነው? ይሖዋ ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲኖረኝ ስለረዳኝ በየዕለቱ በጸሎት አመሰግነዋለሁ። እንዲሁም በተቻለኝ መጠን ራሴን በይሖዋ አገልግሎት ለማስጠመድና ዓይኔ ከፊቴ በሚጠብቀኝ ተስፋ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ እጥራለሁ።
ብዙ ጊዜ ስለ አዲሱ ዓለም እንዲሁም በድጋሚ እንደ ልቤ መሮጥና መዝለል ስለምችልበት ጊዜ አስባለሁ። የፖሊዮ ሰለባ ከሆነው ከቅርብ ጓደኛዬ ከሆሴ ማሪያ ጋር በማራቶን ሩጫ አብረን ስለመካፈል እያወራን የምንቀላለድባቸው ጊዜያት አሉ። “ማን የሚያሸንፍ ይመስልሃል?” ብዬ እጠይቀዋለሁ። እሱም “ገነት ገብተን በሩጫው ለመወዳደር ያብቃን እንጂ ማንም አሸነፈ ማን ለውጥ የለውም” ይለኛል።
የአካል ጉዳተኛ መሆኔን መቀበል በጣም ከብዶኝ ነበር። በወጣትነቴ የሞኝነት ሥራ እንደሠራሁና ያደረግኩት ነገር ከባድ ዋጋ እንዳስከፈለኝ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ሆኖም ይሖዋ ስላልጣለኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ይሖዋ ብዙ ነገር አድርጎልኛል፤ ሰፊ መንፈሳዊ ቤተሰብ፣ በሕይወት የመኖር ፍላጎት፣ ሌሎችን በመርዳት የሚገኝ ደስታና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ግሩም የሆነ ተስፋ ሰጥቶኛል። ስሜቴን ሁሉ በአንድ ዓረፍተ ነገር ግለጽ ብባል ይሖዋ በእርግጥም ከሚገባው በላይ አድርጎልኛል ብዬ መናገር እችላለሁ።