ሕይወት እንዴት ጀመረ?
የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር አሟላ፦
ሕይወት የተገኘው በ . . . ነው።
ሀ. ዝግመተ ለውጥ
ለ. ፍጥረት
አንዳንዶች፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ከላይ ለቀረበው ጥያቄ “ዝግመተ ለውጥ” የሚለውን እንደሚመርጥ፣ ሃይማኖተኛ የሆነ ሰው ደግሞ “ፍጥረት” ብሎ እንደሚመልስ ያስቡ ይሆናል።
ይህ ግን ሁልጊዜ ትክክል አይደለም።
እንደ እውነቱ ከሆነ በርካታ ሳይንቲስቶችን ጨምሮ ብዙ የተማሩ ሰዎች የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ትክክለኛነት ይጠራጠራሉ።
ኮሌጅ ሳሉ ስለ ዝግመተ ለውጥ የተማሩትንና የነፍሳት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑትን ዠራርድን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። “ፈተና በምፈተንበት ጊዜ ፕሮፌሰሮቹ የሚፈልጉትን መልስ እሰጥ ነበር፤ እኔ ግን አላምንበትም” ብለዋል።
ለመሆኑ ሳይንሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎችም ሳይቀር ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው ብሎ መቀበል የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? የዚህን መልስ ለማግኘት ብዙ ተመራማሪዎችን ግራ ያጋቡ ሁለት ጥያቄዎችን እንመልከት፦ (1) ሕይወት የጀመረው እንዴት ነው? (2) ሕይወት ያላቸው ነገሮች ዛሬ ያላቸውን መልክ ሊይዙ የቻሉት እንዴት ነው?
ሕይወት የጀመረው እንዴት ነው?
አንዳንዶች ምን ይላሉ? ሕይወት የተገኘው ሕይወት ከሌለው ነገርና በአጋጣሚ ነው።
ሌሎች ሰዎች ይህ መልስ የማያረካቸው ለምንድን ነው? የሳይንስ ሊቃውንት ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ስለሚገኘው ኬሚካላዊና ሞለኪውላዊ አሠራር ያላቸው እውቀት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጨምሯል፤ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የሕይወትን ምንነት በእርግጠኝነት መናገር አልቻሉም። ሕይወት በሌላቸው ነገሮችና ውስብስብ ባልሆነ ሴል መካከል እንኳ የገደል ያህል ትልቅ ልዩነት አለ።
የሳይንስ ሊቃውንት በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በምድር ላይ ስለነበረው ሁኔታ ግምታዊ ሐሳብ ከመናገር ውጭ የሚያውቁት ነገር የለም። ሕይወት ስለጀመረበት ቦታ ያላቸው አመለካከትም የተለያየ ነው፤ ለምሳሌ አንዳንዶቹ በእሳተ ገሞራ ውስጥ ሌሎቹ ደግሞ ጥልቅ በሆነ የውቅያኖስ ወለል ላይ እንደጀመረ ያምናሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሕይወትን ለማስገኘት ምክንያት የሆኑት ነገሮች መጀመሪያ በሕዋ ውስጥ ከተሠሩ በኋላ ከጠፈር ከሚወረወሩ አካላት ጋር አብረው እንደመጡ የሚያምኑም አሉ። ይህም ቢሆን ‘ሕይወት የጀመረው እንዴት ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ አይሆንም፤ እንዲያውም ቦታው መራቁ መልሱን ማግኘት የዚያኑ ያህል ከባድ እንዲሆን ያደርገዋል።
የሳይንስ ሊቃውንት ዛሬ ለምናውቀው ጄኔቲካዊ ቁስ መገኛ የሆኑ ሞለኪውሎች እንደነበሩ ይገምታሉ። እነዚህ ሞለኪውሎች ሕይወት ከሌላቸው ነገሮች በአጋጣሚ እንደተገኙና ራሳቸውን በራሳቸው እንደሚያባዙ ይታሰባል። ይሁን እንጂ የሳይንስ ሊቃውንት እንደነዚህ ያሉ ሞለኪውሎች ኖረው ያውቁ እንደሆነ ማስረጃ ማቅረብም ሆነ ሞለኪውሎቹን በቤተ ሙከራ መሥራት አልቻሉም።
ሕያዋን ነገሮች መረጃዎችን የሚይዙበትና ጥቅም ላይ የሚያውሉበት መንገድ ፈጽሞ የተለየ ነው። ሴሎች በጄኔቲክ ኮዳቸው ውስጥ ያሉትን መመሪያዎች ያስተላልፋሉ፣ ይተረጉማሉ እንዲሁም ይተገብራሉ። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ጄኔቲክ ኮዶችን ከኮምፒውተር ሶፍትዌር (ፕሮግራም) ጋር ሲያመሳስሏቸው፣ የሴሎችን ኬሚካላዊ መዋቅር ደግሞ ከኮምፒውተር ሃርድዌር (የሚታየው የኮምፒውተሩ አካል) ጋር ያመሳስሉታል። ሆኖም ዝግመተ ለውጥ በጄኔቲክ ኮድ ላይ ያለው መረጃ ከየት እንደተገኘ ማብራራት አይችልም።
አንድ ሴል ተግባሩን እንዲያከናውን የፕሮቲን ሞለኪውሎች የግድ አስፈላጊ ናቸው። አንድ የፕሮቲን ሞለኪውል ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አሚኖ አሲዶች አሉት። በተጨማሪም የፕሮቲን ሞለኪውሉ ተፈላጊውን ጥቅም የሚሰጠው የተወሰነ ቅርጽ ይዞ ከተጣጠፈ በኋላ ነው። አንድ የፕሮቲን ሞለኪውል ብቻ እንኳ በራሱ ሊገኝ ይችላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል እንደሆነ አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ተናግረዋል። ፖል ዴቪስ የተባሉ የፊዚክስ ሊቅ “አንድ ሕይወት ያለው ሴል በሺህ የሚቆጠሩ የተለያዩ ዓይነት ፕሮቲኖች ስለሚያስፈልጉት በአጋጣሚ እንደተገኙ ማሰብ ሊታመን የማይችል ነገር ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
መደምደሚያ፦ በሁሉም የሳይንስ ዘርፎች ለበርካታ ዓመታት የተደረገው ምርምር እንዳሳየው ሕይወት የሚገኘው ሕይወት ካለው ነገር ብቻ ነው።
ሕይወት ያላቸው ነገሮች ዛሬ ያላቸውን መልክ ሊይዙ የቻሉት እንዴት ነው?
አንዳንዶች ምን ይላሉ? በጂን ላይ በአጋጣሚ በሚከሰት ለውጥ (ሚውቴሽን) እና በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት የመጀመሪያው ሕይወት ያለው አካል ቀስ በቀስ ተሻሽሎ ሰውን ጨምሮ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ አስገኘ።
ሌሎች ሰዎች ይህ መልስ የማያረካቸው ለምንድን ነው? አንዳንድ ሴሎች ከሌሎች ይበልጥ ውስብስብ ናቸው። አንድ ጽሑፍ እንደሚናገረው ‘አንድ ውስብስብ ያልሆነ ሴል ይበልጥ ውስብስብ ወደሆነ ሴል ሊሻሻል የሚችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ጥያቄ “‘ሕይወት እንዴት ተገኘ?’ ከሚለው ጥያቄ ቀጥሎ ዝግመተ ለውጥ ያልፈታው ሁለተኛው ሚስጥር ነው።”
የሳይንስ ሊቃውንት በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ የተለያየ ተግባር የሚያከናውኑ ከፕሮቲን የተሠሩ ማሽኖች እንዳሉና እርስ በርስ በመተባበር ውስብስብ የሆነ ተግባር እንደሚያከናውኑ ደርሰውበታል። ከእነዚህ ተግባራት መካከል ምግብ ማጓጓዝና ምግቡን ወደ ኃይል መለወጥ፣ የሴል ክፍሎችን መጠገን፣ መልእክቶችን በሴሉ ውስጥ ማድረስ ይገኙበታል። በጂን ላይ በአጋጣሚ የሚከሰት ለውጥና ተፈጥሯዊ ምርጦሽ በሴል ውስጥ የሚገኙትን የተራቀቁ ክፍሎች በማገጣጠም እንዲህ ያለ የተወሳሰበ ተግባር እንዲፈጽሙ ማድረግ ይችላሉ? ብዙዎች እንዲህ ብሎ ማመን ይከብዳቸዋል።
የእንስሳትም ሆነ የሰዎች እድገት መነሻ አንድ የዳበረ እንቁላል ነው። በጽንሱ ውስጥ ያሉ ሴሎች እየተባዙ በመሄድ ቀስ በቀስ ሚናቸውን ይለያሉ፤ የተለያየ ቅርጽና ተግባር በመያዝ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ያስገኛሉ። እያንዳንዱ ሴል ወደፊት ምን እንደሚሆን ብሎም በአካሉ ውስጥ ቦታው የት እንደሆነ “የሚያውቀው” እንዴት እንደሆነ ዝግመተ ለውጥ ማስረዳት አይችልም።
በአሁኑ ጊዜ የሳይንስ ሊቃውንት አንድ የእንስሳ ዓይነት ወደ ሌላ የእንስሳ ዓይነት እንዲቀየር ከተፈለገ ለውጡ መከናወን ያለበት በሞለኪውል ደረጃ፣ በሴል ውስጥ እንደሆነ ተገንዝበዋል። የሳይንስ ሊቃውንት፣ አንድ ውስብስብ አይደለም የሚባል ሴል እንኳ እንዴት በዝግመተ ለውጥ ሊገኝ እንደቻለ ማስረዳት ካልቻሉ በጂን ላይ በአጋጣሚ የሚከሰት ለውጥና ተፈጥሯዊ ምርጦሽ በፕላኔታችን ላይ የሚገኙትን የተለያዩ ዓይነት እንስሳት እንዳስገኙ ማመን ምክንያታዊ ነው? የባዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ቢሂ ስለ እንስሳት አካል አወቃቀር ሲናገሩ “ያልተጠበቀና እጅግ አስደናቂ የሆነ ውስብስብነት መኖሩ [በምርምር] ቢታወቅም እንዲህ ያለው ውስብስብ ንድፍ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ሳይኖር እንዲሁ በአጋጣሚ ሊገኝ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማስረዳት” አለመቻሉን ገልጸዋል።
የሰው ልጆች የማስተዋልና ማንነታቸውን የማወቅ፣ የማሰብና የማገናዘብ ችሎታ አላቸው፤ እንዲሁም እንደ ልግስና፣ ራስን መሥዋዕት እንደ ማድረግ ብሎም ትክክልና ስህተት የሆነውን እንደ መለየት ያሉ የሥነ ምግባር እሴቶችን ያንጸባርቃሉ። በጂን ላይ በአጋጣሚ የሚከሰት ለውጥና ተፈጥሯዊ ምርጦሽ እንደነዚህ ያሉትን ልዩ የሆኑ ባሕርያት ሊያስገኙ አይችሉም።
መደምደሚያ፦ ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ መሆኑ የማይታበል ሐቅ እንደሆነ የሚከራከሩ ሰዎች ብዙ ቢሆኑም ሌሎች ግን ዝግመተ ለውጥ፣ ሕይወት ስለተገኘበትና አሁን ያሉት ዝርያዎች ስለተገኙበት መንገድ የሚሰጠው ማብራሪያ አያረካቸውም።
ሊመረመር የሚገባው መልስ
ብዙ ሰዎች ማስረጃዎቹን ከመረመሩ በኋላ ሕይወት የላቀ የማሰብ ችሎታ ካለው አካል እንደተገኘ ደምድመዋል። በአንድ ወቅት አምላክ የለሽነትን በጥብቅ ይደግፉ የነበሩትና የፍልስፍና ፕሮፌሰር የሆኑት አንተኒ ፍሉ ለዚህ ምሳሌ ይሆኑናል። እኚህ ምሁር ሕይወት እጅግ ውስብስብ መሆኑን ሲገነዘቡና አጽናፈ ዓለም ስለሚመራበት ሕግ ሲያውቁ አመለካከታቸውን ለውጠዋል። የጥንት ፈላስፎችን አመለካከት በመጥቀስ “የትም ያድርሰን የት ማስረጃው ወደሚመራን መሄድ አለብን” በማለት ጽፈዋል። በመሆኑም ፕሮፌሰር ፍሉ ማስረጃው የመራቸው፣ ‘ፈጣሪ አለ’ ወደሚለው መደምደሚያ ነው።
በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ዠራርድም ተመሳሳይ ወደሆነ ድምዳሜ ደርሰዋል። ከፍተኛ ትምህርት የተከታተሉና በነፍሳት ጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ቢሆንም እንዲህ ብለዋል፦ “ሕይወት የተገኘው ሕይወት ከሌለው ነገር በአጋጣሚ እንደሆነ የሚያሳይ አንድም ማስረጃ አላገኘሁም። ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚታየው ሥርዓታማነትና ውስብስብነት አንድ አደራጅና ንድፍ አውጪ ሊኖር እንደሚገባ አሳምኖኛል።”
አንድ ሰው የአንድን ሠዓሊ ሥራዎች በመመርመር ስለ ሠዓሊው ሊያውቅ እንደሚችል ሁሉ ዠራርድም ተፈጥሮን በመመርመር የፈጣሪን ባሕርያት ሊያስተውሉ ችለዋል። በተጨማሪም ዠራርድ ፈጣሪ ያስጻፈው መጽሐፍ እንደሆነ የሚታመነውን መጽሐፍ ቅዱስን ጊዜ ወስደው መርምረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህን በማድረጋቸውም ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች የሚያረኩ መልሶችን አግኝተዋል፤ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ በሰው ልጆች ፊት ለተደቀኑ ችግሮች መፍትሔው ምን እንደሆነ ተረድተዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ያስጻፈው መጽሐፍ መሆኑን ሊያምኑ ችለዋል።
በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ መልሶች ሊመረመሩ የሚገባቸው ናቸው፤ ዠራርድም ይህን ተገንዝበዋል። አንተም መልሶቹን እንድትመረምር እናበረታታሃለን።