ነቅታችሁ ጠብቁ!
ዓለማችን በከፍተኛ ሙቀት እየነደደች ነው—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በሐምሌ ወር 2022 በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ የሙቀት ወጀብ ክብረ ወሰን ተመዝግቧል፦
“ቻይና በዚህ ወር ለሁለተኛ ጊዜ ወደ 70 የሚጠጉ ከተሞች ከፍተኛ የሙቀት ወጀብ እንደሚያጋጥማቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።”—ሐምሌ 25, 2022 ሲ ኤን ኤን ዋየር ሰርቪስ
“አውሮፓን እያንገበገባት ያለው የሙቀት ወጀብ በብዙ አገሮች ሰደድ እሳት እንዲስፋፋ አድርጓል።”—ሐምሌ 17, 2022 ዘ ጋርዲያን
“እሁድ ዕለት በበርካታ የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ኃይለኛ ሙቀት ተመዝግቧል፤ ሙቀቱ ወደ ምሥራቃዊው ዳርቻ እንዲሁም ወደ አንዳንድ የደቡባዊና የመካከለኛ ምዕራብ ክፍሎች እየተዛመተ ነው።”—ሐምሌ 24, 2022 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ
እነዚህ ክስተቶች የሚጠቁሙት ነገር ይኖር ይሆን? ምድራችን ሰው አልባ የምትሆንበት ጊዜ እየመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ የሙቀት ወጀብ እንደሚመጣ ተንብዮአል?
አዎ። በዓለም ዙሪያ የሚታየው የሙቀት ወጀብ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመናችን ከሚናገረው ትንቢት ጋር የሚስማማ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ “የሚያስፈሩ [ወይም “የሚያስደነግጡ፣” ሕያው ቃል] ነገሮች” እንደሚታዩ ትንቢት ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ዓለም አቀፍ የሙቀት መጠን መጨመር ብዙዎችን ‘የሰው ልጅ ምድርን ያጠፋት ይሆን?’ የሚል ስጋት ውስጥ ከትቷቸዋል።
ምድራችን ሰው አልባ ትሆን ይሆን?
አትሆንም። አምላክ ምድርን የፈጠራት የሰው ልጆች ለዘላለም እንዲኖሩባት ነው። (መዝሙር 115:16፤ መክብብ 1:4) ስለዚህ የሰው ልጆች ምድርን እንዲያጠፏት አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ቃል በገባው መሠረት “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ያጠፋቸዋል]።”—ራእይ 11:18
አምላክ የገባውን ቃል የያዙ ሌሎች ሁለት ትንቢቶችንም እስቲ እንመልከት፦
“ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ሐሴት ያደርጋል፤ በረሃማው ቦታም ደስ ይለዋል፤ እንደ ሳሮን አበባም ያብባል።” (ኢሳይያስ 35:1) አምላክ ምድራችን ሰው አልባ ምድረ በዳ እንድትሆን አይፈቅድም፤ እንዲያውም ጉዳት የደረሰባቸው የምድር ክፍሎች እንዲታደሱ ያደርጋል።
“ምድርን እጅግ ፍሬያማ በማድረግና በማበልጸግ ትንከባከባታለህ።” (መዝሙር 65:9) አምላክ ምድርን ገነት ያደርጋታል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ትንቢት ተናግሯል? መልሱን ለማግኘት “የአየር ንብረት ለውጥ ያጠፋን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምድራችን እንደምትታደስ ስለሰጠው ተስፋ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? “ምድርን የሚታደጋት ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።