ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
በተለያዩ አገሮች ውስጥ፣ ሰዎች ፍትሐዊ አይደሉም ብለው የሚያስቧቸውን የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለመታገል አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ያሰማሉ። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ደግሞ ሁኔታውን ስላባባሰው ይበልጥ ውጥረት እንዲፈጠር አድርጓል፤ ወረርሽኙን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደቦች መጣላቸው፣ የሸቀጦች እጥረት መኖሩ እንዲሁም በሕክምናው ዘርፍ ክፍተት መፈጠሩ በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ገሃድ እንዲወጣ አድርጓል።
ዓለምን ቀስፈው የያዙት የኢኮኖሚ ችግሮች የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ዛሬ ላሉብን ችግሮች እልባት ለመስጠት ምን እንደሚያደርግ ይናገራል።
አምላክ እልባት የሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ችግሮች
ችግሩ፦ የሰው ልጆች የሁሉንም ሰው ፍላጎት የሚያሟላ የኢኮኖሚ ሥርዓት መዘርጋት አልቻሉም።
መፍትሔው፦ አምላክ በሰብዓዊ መንግሥታት ምትክ የራሱን መንግሥት ያቋቁማል፤ ይህ መንግሥት የአምላክ መንግሥት ተብሎ ይጠራል። ይህ መንግሥት ከሰማይ ሆኖ መላዋን ምድር ያስተዳድራል።—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10
ውጤቱ፦ የአምላክ መንግሥት ዓለም አቀፍ መንግሥት ስለሆነ የምድርን ጉዳዮች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስተዳደር ይችላል። ያን ጊዜ ሰዎች በድህነት አይቆራመዱም፤ ወይም የኑሮ ጉዳይ ስጋት አይሆንባቸውም። (መዝሙር 9:7-9, 18) የልፋታቸውን ፍሬ ያገኛሉ፤ እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሥራቸው እየተደሰቱ ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ተስፋ ይሰጣል፦ “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤ እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22
ችግሩ፦ ሰዎች ለመከራና ለእጦት የሚዳርጉ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።
መፍትሔው፦ በመንግሥቱ አማካኝነት አምላክ እንድንፈራና እንድንሰጋ የሚያደርጉንን ነገሮች ሁሉ ያስወግዳል።
ውጤቱ፦ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር፣ ሰዎች እነሱንም ሆነ ቤተሰባቸውን ለእጦት የሚዳርግ ነገር አያጋጥማቸውም። ለምሳሌ ያህል ጦርነት፣ ረሃብና ወረርሽኝ ታሪክ ይሆናሉ። (መዝሙር 46:9፤ 72:16፤ ኢሳይያስ 33:24) አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ የመኖሪያ ስፍራ፣ አስተማማኝ በሆነ መኖሪያና ጸጥታ በሰፈነበት የማረፊያ ቦታ ይኖራል።”—ኢሳይያስ 32:18
ችግሩ፦ ራስ ወዳድና ስግብግብ የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሌሎችን መጠቀሚያ ያደርጋሉ።
መፍትሔው፦ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ከራሳቸው ይልቅ ሌሎችን መውደድን ይማራሉ።—ማቴዎስ 22:37-39
ውጤቱ፦ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር፣ ሁሉም ሰው እንደ አምላክ ለሌሎች ፍቅር ያሳያል፤ ፍቅር ደግሞ “የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ምክንያቱም ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድርም በይሖዋ a እውቀት ትሞላለች።”—ኢሳይያስ 11:9
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የምንኖረው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች እንደሆነ ይናገራል፤ እንዲሁም አምላክ ለሁሉም የኢኮኖሚ ችግሮቻችን መፍትሔ ለመስጠት የገባውን ቃል በቅርቡ እንደሚፈጽም ይገልጻል። b (መዝሙር 12:5) እስከዚያው ግን፣ ዛሬ የሚያጋጥሙህን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታት የሚረዱ መመሪያዎች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ “በአነስተኛ ገቢ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?” እና “ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።
a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።—መዝሙር 83:18
b በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል የምትችለው ለምን እንደሆነ ለማወቅ “መጽሐፍ ቅዱስ—አስተማማኝ የእውነት ምንጭ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።