በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 3, 2023
ሞዛምቢክ

መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በቾፒ ቋንቋ ወጣ

መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በቾፒ ቋንቋ ወጣ

ጥቅምት 29, 2023 በኩዊሲኮ፣ ሞዛምቢክ በተካሄደ ልዩ ስብሰባ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በቾፒ ቋንቋ መውጣቱ ተበሰረ። የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ማርሴሎ ሳንቶስ የማቴዎስ መጽሐፍ መውጣቱን ያበሰረው 460 ተሰብሳቢዎች በተገኙበት ነው። የታተመው ቅጂ በስብሰባው ላይ ለተገኙት ደርሷቸዋል። የኤሌክትሮኒክና የድምፅ ቅጂዎቹንም ማውረድ ተችሏል።

በዋነኝነት በሞዛምቢክ ደቡባዊ አውራጃዎች የሚኖሩ 1.1 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የቾፒ ቋንቋን ይናገራሉ። በቾፒ ቋንቋ በሚካሄዱ ሰባት ጉባኤዎችና አምስት ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ332 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አሉ። በቾፒ ቋንቋ የሚገኙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቢኖሩም ይሖዋ የሚለውን ስም አይጠቀሙም። በተጨማሪም ውድ ከመሆናቸውም በላይ በአብዛኛው የሚጠቀሙት ጊዜ ያለፈባቸውን ቃላት ነው።

እኛም የቾፒ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ደስታ እንጋራለን፤ እንዲሁም ይህ አዲስ ትርጉም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የሚያረካ የእውነት ውኃ እየፈለጉ ያሉ ብዙ ሰዎችን እንዲረዳ እንጸልያለን።—ኢሳይያስ 55:1