በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ አሌክሲ ቡደንቹክ፣ ኮንስታንቲን ባዤኖቭ፣ ፊሊክስ ማኻመዲዬቭ፣ አሌክሲ ሚሬትስኪ፣ ሮማን ግሪዳሶቭ እና ጌናዲ ጊርማን ከመታሰራቸው በፊት

መስከረም 23, 2019
ሩሲያ

በሩሲያ ተጨማሪ ስድስት ወንድሞች እስራት ተፈረደባቸው

በሩሲያ ተጨማሪ ስድስት ወንድሞች እስራት ተፈረደባቸው

ሐሙስ፣ መስከረም 19, 2019 ሩሲያ ውስጥ በምትገኘው የሳራቶቭ ከተማ የሚኖሩ ስድስት ወንድሞች የይሖዋ ምሥክር በመሆናቸው ብቻ በእስር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

በሳራቶቭ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ዲሚትሪ ላሪን በወንድም ኮንስታንቲን ባዤኖቭ እና በወንድም አሌክሲ ቡደንቹክ ላይ የሦስት ዓመት ተኩል እስራት፣ በወንድም ፊሊክስ ማኻመዲዬቭ ላይ የሦስት ዓመት እስራት እንዲሁም በወንድም ሮማን ግሪዳሶቭ፣ በወንድም ጌናዲ ጊርማን እና በወንድም አሌክሲ ሚሬትስኪ ላይ የሁለት ዓመት እስራት በይነዋል። በዚህ ብይን መሠረት እነዚህ ወንድሞች የእስር ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለአምስት ዓመታት በሕዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ በአመራር ቦታ ላይ እንዳያገለግሉ ታግደዋል። ተከሳሾቹ ጉዳዩን ይግባኝ ለማለት አስበዋል።

በእነዚህ ስድስት ወንድሞች ላይ ክስ የተመሠረተው ሰኔ 12, 2018 የሩሲያ ባለሥልጣናት በሳራቶቭ በሚገኙ ሰባት የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ፍተሻ ካደረጉ በኋላ ነው። ሁሉም ወንድሞች ቤተሰብ ያላቸው ሲሆን ወንድም ቡደንቹክ ትምህርት ያልጨረሱ ሁለት ልጆች አሉት። ወንድም ቡደንቹክ፣ ወንድም ባዤኖቭ እና ወንድም ማኻመዲዬቭ በባለሥልጣናቱ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ ችሎት ፊት ሳይቀርቡ ወደ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ታስረው ቆይተዋል።

ስድስቱ ወንድሞች ለፍርድ ቤቱ በሰጡት የመደምደሚያ ሐሳብ ላይ አንዳንድ የሚያበረታቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የጠቀሱ ከመሆኑም ሌላ ክሱን ለመሠረቱት ሰዎች ምንም ዓይነት ጥላቻ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ሩሲያ ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው በእስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ወንድሞች ሰባት ደርሰዋል። በሩሲያ የሚገኙ ከ250 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ክስ የተመሠረተባቸው ሲሆን 41 የሚሆኑት በእስር ላይ (ችሎት ፊት ሳይቀርቡ ወይም ተፈርዶባቸው) ናቸው፤ በተጨማሪም 23 የሚሆኑት በቁም እስር ላይ ይገኛሉ።

በሩሲያ የሚገኙት ታማኝና ደፋር ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ‘በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት እንዲቋቋሙ የአምላክ ታላቅ ኃይል የሚያስፈልጋቸውን ብርታት ሁሉ እንዲሰጣቸው’ እንጸልያለን።—ቆላስይስ 1:11