በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአውሮፓ የደህንነትና የትብብር ድርጅት (OSCE) ቋሚ ምክር ቤት መቀመጫ የሆነው በቪየና የሚገኘው የሆፍበርግ ቤተ መንግሥት

ነሐሴ 11, 2020
ሩሲያ

የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ባለሥልጣናት ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እያደረሰች ያለችውን ስደት አወገዙ

የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ባለሥልጣናት ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እያደረሰች ያለችውን ስደት አወገዙ

ዩናይትድ ስቴትስና 30 ገደማ የሚሆኑ የአውሮፓ አገሮች ሩሲያ በወንድሞቻችን ላይ እያደረሰች ያለችውን የተቀነባበረ ስደትና እንግልት በጥብቅ አወገዙ። ይህን አቋማቸውን የገለጹት የአውሮፓ የደህንነትና የትብብር ድርጅት (OSCE) ቋሚ ምክር ቤት a ሐምሌ 23, 2020 ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው።

የምክር ቤቱ የዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ አማካሪ የሆኑት ሌን ዳርነል ለተሰበሰቡት ባለሥልጣናት እንዲህ ብለዋል፦ “ዩናይትድ ስቴትስና እዚህ የተሰበሰቡት ሰዎች የወከሏቸው በርካታ አገሮች የሩሲያ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን ያለምንም መሠረት በማሰር፣ ቤታቸውን በመፈተሽ፣ እስከ ስድስት ዓመት የሚደርስ እስራት በመበየንና በማንገላታት ያደረሱትን በደል ያወግዛሉ፤ ደግሞም በዚህ አቋማቸው ይቀጥላሉ።”

ተወካዮቹን ይበልጥ ያሳሰባቸው በቅርቡ የሩሲያ ባለሥልጣናት በቮሮኒሽ ክልል የሚገኙ ከ100 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶችን እንደፈተሹ የሚገልጸው ሪፖርት ነው። የፖለቲካ አማካሪዋ ሌን “አነስተኛ ቁጥር ባለው አንድ ሰላማዊ የሃይማኖት ቡድን ላይ በዚህ መጠን ጭቆና መድረሱ በጣም አስደንጋጭ ነው” በማለት ገልጸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ልዑካን ምክትል ኃላፊ የሆኑት ኒኮላ መሬም በበኩላቸው “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የቤቶች ፍተሻና መጠነ ሰፊ ብርበራ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተቀነባበረ የስደት ዘመቻ መከፈቱን የሚጠቁም ይመስላል” በማለት ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። አክለውም “ምርመራ በሚካሄድባቸውና በወንጀል በሚጠየቁት ላይ ማስረጃ ተብሎ የሚቀርበው ነገር መደበኛ የሆነ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴን የሚያካትት ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም የቮሮኒሽ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮቹን “ሕገ ወጥ ድርጊት ለመፈጸም አሲረዋል” በሚል እስር ቤት አስገብተዋቸው የነበረ ሲሆን ሌን ዳርነል ይህ ሐሰት መሆኑን አጋልጠዋል። የይሖዋ ምሥክሮቹን በዚህ ወንጀል ካስጠየቋቸው ነገሮች መካከል ሪፖርቶችንና ሌሎች ሰነዶችን በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ማስቀመጣቸው፣ ቡድኖችን ማደራጀታቸው እንዲሁም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ስብሰባዎችን ማድረጋቸው ይገኙበታል። ሌን የሩሲያ ባለሥልጣናት የሰነዘሩትን ይህን ክስ “የማይመስልና አሳፋሪ” በማለት ጠርተውታል። “በዚህ ዓይነት እኔም በየዕለቱ ‘ሕገ ወጥ ድርጊት ለመፈጸም አሴራለሁ’ ማለት ነው” ብለዋል። በተጨማሪም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ እየተካፈሉ ያሉት የሩሲያ ልዑካንም “እንዲህ ባሉ የወንጀል እንቅስቃሴዎች ተካፍለዋል” ሊባል እንደሚችል ገልጸዋል።

የአውሮፓ ኅብረት 27 አባል አገራት፣ የኅብረቱ አባላት ካልሆኑ ሌሎች ስምንት አገራት ጋር ሆነው ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የሩሲያ ልዑካን በቋሚ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት ሃይማኖታቸውን እያራመዱ እንዳሉና ወደፊትም በዚህ ሁኔታ እንደሚቀጥሉ እንዲሁም የሩሲያ ፌዴሬሽን የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት እንደሚሰጥ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምተናል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች እየታሰሩ፣ ቤቶቻቸው እየተፈተሹና ሕግ ፊት እየቀረቡ እንዳሉ የሚገልጹ በርካታ ሪፖርቶች እየደረሱን ነው። ይህን ሁኔታ የሩሲያ ልዑካን እየተናገሩ ካሉት ነገር ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል።”

የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች ያለምንም አድልዎ ሰብዓዊ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፤ ይህም የሃይማኖትና የእምነት ነፃነትን፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመሰብሰብ መብትንና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ያካትታል። የሩሲያ ፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት [እንዲሁም] ሩሲያ በዓለም አቀፍ ሕግ ሥር ለምክር ቤቱ (OSCE) የገባችው ቃል ይህ መብት እንዲከበር ያዛል።”

ኒኮላ መሬ፣ ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የምታደርሰውን ስደት እንድታቆም በመጠየቅ የዩናይትድ ኪንግደምን መግለጫ ደምድመዋል።

ሌን ዳርነል፣ ሩሲያ (1) የይሖዋ ምሥክሮችን ሕግ ፊት ማቅረቧን እንድታቆም፣ (2) በቁጥጥር ሥር ያዋለችውን በሩሲያ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት እንድትመልስ እና (3) ያሰረቻቸውን የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ በአስቸኳይ እንድትፈታ ጠይቀዋል።

ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሩሲያ በወንድሞቻችን ላይ እያደረሰች ያለችውን በደል አውግዘው ሲናገሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የጭካኔ ድርጊት ጠንቅቆ ያውቃል፤ ሩሲያም ይህን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል። ከሁሉ በላይ ግን ይሖዋ በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያሉበትን ሁኔታ እንደሚያውቅ እርግጠኞች ነን። (መዝሙር 37:18) በሰማይ ያለው አፍቃሪ አባታችን ወንድሞቻችንን ላሳዩት ታማኝነት፣ ድፍረትና ጽናት ምንጊዜም እንደሚባርካቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 37:5, 28, 34

a የአውሮፓ የደህንነትና የትብብር ድርጅት (OSCE) ከተሰጡት ተልእኮዎች መካከል ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ማድረግ ይገኝበታል። ቋሚ ምክር ቤቱ የዚህ ድርጅት (OSCE) ውሳኔ ሰጪ አካል ነው።