በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 25, 2022 ኮፐንሃገን ካትረፕ አየር ማረፊያ ውስጥ ዴኒስ ክሪስተንሰን በአባቱና በእህቱ አቀባበል ሲደረግለት

ግንቦት 25, 2022
ሩሲያ

ዴኒስ ክሪስተንሰን ተለቀቀ፤ ከአገር እንዲወጣም ተደረገ

ዴኒስ ክሪስተንሰን ተለቀቀ፤ ከአገር እንዲወጣም ተደረገ

ግንቦት 24, 2022 ዴኒስ በሚለቀቅበት ቀን አይሪና ክሪስተንሰን ከእስር ቤቱ ውጭ ስትጠብቀው፣ እስር ቤት ቁ. 3፣ ለጎቭ፣ ሩሲያ

ዴኒስ ክሪስተንሰን ግንቦት 25, 2022 በሰላም ዴንማርክ ደርሷል። ከእስር የተፈታው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሲሆን ወዲያውኑ ከሩሲያ እንዲወጣ ተወስኗል። በተለያዩ ወህኒ ቤቶች በድምሩ አምስት ዓመታት ቆይቷል።

ዴኒስ እንዲህ ብሏል፦ “ከእስር በመፈታቴና ከውዷ ባለቤቴ ከአይሪና ጋር በመገናኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል። ከዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ያገኘሁት ድጋፍና ማበረታቻ የይሖዋ ስጦታ እንደሆነ ይሰማኛል። በእምነታቸው ምክንያት እየተሰደዱና እየታሰሩ ላሉ ደፋር ወንድሞቼና እህቶቼ መጸለዬን እቀጥላለሁ።”

ዴኒስ እና አይሪና በሞስኮ ዶሞዴዶቮ አየር ማረፊያ ውስጥ

ዴኒስ እና አይሪና ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ እያገኙ ነው። ባልና ሚስቱ እንዲህ ብለዋል፦ “በዴንማርክ ከሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ይሖዋን በነፃነት ለማምለክ እንጓጓለን።”

ዴኒስ የታሰረው ግንቦት 25, 2017 ነው፤ ይህ የሆነው ጭምብል የለበሱና የታጠቁ የሩሲያ ወታደሮች ኦርዮል ውስጥ ዴኒስ የተገኘበትን የጉባኤ ስብሰባ ሰብረው በመግባት በበረበሩበት ወቅት ነው። በኋላም ጽንፈኛ ተብሎ የተፈረጀን ሃይማኖታዊ ድርጅት እንቅስቃሴዎች አስተባብረሃል በሚል ብይን ተላለፈበት፤ ሆኖም ዴኒስ በተያዘበት ወቅት የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን ድርጅት ጽንፈኛ ብሎ በመፈረጅ እገዳ ከጣለ ገና አንድ ወሩ ነበር።

የሩሲያ ባለሥልጣናት፣ የ2017ቱ እገዳ የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ ማኅበራት የሚገድብ እንጂ የግለሰቦችን የማምለክ ነፃነት የሚጋፋ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ማረጋገጫ እንደሰጡ ይታወቃል። ይሁንና የዴኒስን መያዝ ተከትሎ በመላው ሩሲያና ክራይሚያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የእስራት ዘመቻ ጀመረ።

ዴኒስ እና አይሪና ወደ ዴንማርክ ሲያቀኑ አውሮፕላኑ ለጊዜው ባረፈበት በኢስታንቡል አየር ማረፊያ ውስጥ ሁለት የቱርክ ወንድሞች አቆያይተዋቸዋል

በአሁኑ ወቅት 91 ወንድሞችና እህቶች እስር ቤት ይገኛሉ። ይሖዋ ታማኞቹን እንዲደግፋቸውና “ልዩ በሆነ መንገድ” እንዲይዛቸው መጸለያችንን እንቀጥላለን።—መዝሙር 4:3