በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 2, 2019
ታጂኪስታን

የታጂክ ባለሥልጣናት በ68 ዓመቱ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ ላይ ፍትሐዊ ያልሆነ የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ፈረዱ

የታጂክ ባለሥልጣናት በ68 ዓመቱ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ ላይ ፍትሐዊ ያልሆነ የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ፈረዱ

መስከረም 10, 2019 ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ ሃይማኖታዊ እምነቱን ለሌሎች በመናገሩ ብቻ በሰባት ዓመት ተኩል እስራት እንዲቀጣ በታጂኪስታን የሚገኘው የኩጃንድ ከተማ ፍርድ ቤት ብይን አስተላልፏል። የይሖዋ ምሥክሮች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ይግባኝ ጠይቀዋል።

ወንድም ካኪሞቭን ለዚህ ፍርድ የዳረገው ነገር የተከሰተው በ2019 መጀመሪያ ላይ ነው። የካቲት 26 ባለሥልጣናት “ሃይማኖታዊ ጥላቻን መቀስቀስ” በሚል ክስ የ68 ዓመቱን ሻሚልን ያዙት። በኋላም ፍርድ ቤቱ፣ ሻሚል ችሎት ፊት ከመቅረቡ በፊት ባለው ጊዜ ታስሮ እንዲቆይ የወሰነ ሲሆን ይህ ጊዜ ለስድስት ወር እንዲራዘም ተደረገ። ወንድም ካኪሞቭ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ መታሰሩ እንዳይበቃ የደም ግፊት ሕመምተኛ ነው፤ ለዚህ ሕመሙ ካደረገው ሕክምናም ገና አላገገመም።

በ2017 የ18 ዓመቱ ዳኒል ኢስላሞቭ ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለመልበስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የስድስት ወር እስራት ከተፈረደበት ወዲህ በታጂኪስታን የታሰረው የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር ይህ ወንድም ነው። በዚህ የተነሳ ታጂኪስታን፣ ቢያንስ አንድ የይሖዋ ምሥክር ከታሰረባቸው አምስት አገሮች ተርታ ተሰልፋለች። የቀሩት አራት አገሮች ሩሲያ፣ ሲንጋፖር፣ ቱርክሜኒስታን እና ኤርትራ ናቸው።

ይሖዋ ለወንድም ካኪሞቭ ይህን መከራ በጽናት እንዲወጣ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ መስጠቱን እንዲቀጥል ጸሎታችን ነው።—ሮም 15:5