በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኤርትራ

በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ኤርትራ

በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ኤርትራ

የኤርትራ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮችን በቁጥጥር ሥር ሲያውልና ሲያስር ቆይቷል። ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ የይሖዋ ምሥክሮች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ወይም ክስ ሳይመሠረትባቸው ይታሰራሉ፤ አንዳንዶቹ የታሰሩት በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በመካፈላቸው ምክንያት ሲሆን ሌሎቹ ግን የታሰሩበት ምክንያት አይገለጽም። ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ኣፈወርቂ ጥቅምት 25, 1994 ባወጡት ፕሬዚዳንታዊ አዋጅ አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮችን ዜግነት ነጥቀዋል፤ ለዚህም እንደ ምክንያት የቀረበው የይሖዋ ምሥክሮች በ1993 ኤርትራ ነፃነቷን ባወጀችበት ሕዝበ ውሳኔ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆናቸው እንዲሁም በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት የማይካፈሉ መሆኑ ነው። ኤርትራ ውስጥ የውትድርና ምልመላ ከመጀመሩ በፊት ባለሥልጣናቱ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት አማራጭ አዘጋጅተው ነበር። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ይህን አገልግሎት ሰጥተዋል። ባለሥልጣናቱም ይህን ብሔራዊ አገልግሎት ላጠናቀቁ ሰዎች የምሥክር ወረቀት የሰጡ ሲሆን ላከናወኑት ጥሩ ሥራም አመስግነዋቸው ነበር። ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንታዊው አዋጅ ከወጣ በኋላ የደህንነት ኃይሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ ለማስገደድ ሲሉ አስረዋቸዋል፣ አሠቃይተዋቸዋል እንዲሁም አንገላተዋቸዋል።

በአሁኑ ወቅት 39 የይሖዋ ምሥክሮች (27 ወንዶችና 12 ሴቶች) እስር ቤት ይገኛሉ። ታኅሣሥ 4, 2020 እስር ቤት የነበሩ 28 የይሖዋ ምሥክሮች (26 ወንዶች እና 2 ሴቶች) ተለቅቀዋል፤ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ከ5 እስከ 26 ለሚደርሱ ዓመታት እስር ቤት ቆይተዋል። ጥር 29, 2021 ደግሞ ከ12 ዓመት በላይ ታስሮ የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር ተፈትቷል፤ በተጨማሪም የካቲት 1, 2021 ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች (አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶች) ከእስር ተለቅቀዋል። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ከአራት እስከ ዘጠኝ ዓመት ድረስ ታስረዋል።

እስር ቤት በነበረው አስከፊ ሁኔታ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ የይሖዋ ምሥክሮች

ኤርትራ ውስጥ አራት የይሖዋ ምሥክሮች እስር ቤት ውስጥ እያሉ ሕይወታቸው አልፏል። ሦስት አረጋውያን የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ አርፈዋል፤ ለዚህ ምክንያት የሆነው እስር ቤት ውስጥ የነበረው አስከፊ ሁኔታ ነው።

በ2018 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ከተዛወሩ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል። ጥር 3 ሃብተሚካኤል ተስፋማርያም በ76 ዓመቱ አርፏል፤ ሃብተሚካኤል መኰነን ደግሞ መጋቢት 6 በ77 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል። የኤርትራ ባለሥልጣናት ሁለቱንም ሰዎች ከ2008 ጀምሮ ያለፍርድ አስረዋቸው ነበር።

በ2011 እና በ2012 ደግሞ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በምዕጢር እስር ቤት በደረሰባቸው ኢሰብዓዊ እንግልት ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ምስግና ገብረትንሳኤ፣ ምድር ቤት በሚገኝ ከፍተኛ ሙቀት ያለው የቅጣት ቦታ ውስጥ በመቆየቱ የተነሳ ሐምሌ 2011 በ62 ዓመቱ አርፏል። ዮሃንስ ሃይለ ደግሞ በዚያው ቦታ ለአራት ዓመታት ገደማ ከታሰረ በኋላ ነሐሴ 16, 2012 በ68 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል። ካሕሳይ መኰነን፣ ጐይትኦም ገብረክርስቶስ እና ጸሃየ ተስፋማርያም የተባሉ ሦስት አረጋውያን የይሖዋ ምሥክሮች ከእስር ከተፈቱ በኋላ አርፈዋል፤ ለሞታቸው ምክንያት የሆነው በምዕጢር እስር ቤት የነበረው አስከፊ ሁኔታ ነው።

ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት አላገኘም

ኤርትራ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መሥፈርቶችን ችላ ማለቷን ቀጥላለች። ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በኤርትራ የሚፈጸመውን የመሠረታዊ መብት ጥሰት ያወገዙ ከመሆኑም ሌላ ኤርትራ ሁኔታውን እንድታስተካክል አሳስበዋል።

በ2014 የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በተመለከተ የቀረበውን ልዩ ሪፖርት አዳምጦ ነበር፤ ሪፖርቱ የኤርትራ ባለሥልጣናት “ዓለም አቀፍ ደንቦችን ግምት ውስጥ በማስገባት” ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ሰዎች መብት እንዲያከብሩ አሳስቧል። በተጨማሪም “የሁሉም እስረኞች አካላዊ ደህንነት እንዲረጋገጥ፣ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው እስረኞች እርዳታ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች . . . እንዲሁም ከዓለም አቀፋዊ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መልኩ የእስር ቤቶቹ ሁኔታ እንዲሻሻል” ሐሳብ ቀርቧል። የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በ2015 ባሳለፈው ድምፀ ውሳኔ ላይ የኤርትራ መንግሥት “ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው ለማይፈቅድላቸው ሰዎች አማራጭ እንዲያዘጋጅ” ጥያቄ አቅርቧል።

በ2016 የሰብዓዊ መብቶች አጣሪ ኮሚሽን ስለ ኤርትራ ባወጣው ሪፖርት ላይ የኤርትራ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች እና በሌሎች ሰዎች ላይ ያደረሱት “ሃይማኖትን እንዲሁም ዘርን መሠረት ያደረገ ስደት” “በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ ወንጀል” መሆኑን ገልጿል።

በ2017 የአፍሪካ የሕፃናት መብትና ደህንነት ባለሙያዎች ኮሚቴ፣ የሕግ ማዕቀፎች ቢኖሩም ኤርትራ ውስጥ “የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች” መብታቸው ያልተከበረላቸው እንዲያውም እንግልት የሚደርስባቸው መሆኑ እንዳሳሰበው ገልጿል። ኮሚቴው ኤርትራ “ለሁሉም ሕፃናት የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት እውቅና እንድትሰጥ እንዲሁም መብታቸውን ሙሉ በሙሉ እንድታስከብር” ሐሳብ አቅርቧል።

በ2018 የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን፣ ኤርትራ “የይሖዋ ምሥክር እምነት ተከታዮችን ጨምሮ የሁሉንም እስረኞች መሠረታዊ መብት ጥሰት ለማስተካከል አፋጣኝ እርምጃ እንድትወስድ” እንዲሁም እስር ቤት ሳሉ የሞቱ የይሖዋ ምሥክሮችን ጉዳይ በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ ሐሳብ አቅርቧል። ኮሚሽኑ የኤርትራ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮች “የዜግነት መብታቸው” እንዳይነፈጋቸው ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቶ ገልጿል።

ግንቦት 2019 የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ ኤርትራ ለሕዝቦቿ የሃይማኖት እና የእምነት ነፃነትን እንድታረጋግጥ እንዲሁም “የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ የሃይማኖት ነፃነት መብታቸውን በመጠቀማቸው ምክንያት የተያዙ ወይም የታሰሩ ሰዎችን በሙሉ እንድትለቅ” አሳስቧል። በተጨማሪም ኮሚቴው ኤርትራ፣ “በሕሊና ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት አለመካፈል ሕጋዊ መብት መሆኑን እንድትቀበል እንዲሁም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው ለማይፈቅድላቸው ሰዎች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንድታዘጋጅ” ጥያቄ አቅርቧል።

ግንቦት 12, 2021 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ልዩ ሪፖርት ላይ የኤርትራ መንግሥት “20 የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ፣ ክስ ሳይመሠረትባቸው ወይም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩትን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቅ” ጥያቄ አቅርቧል። ሪፖርቱ አክሎም መንግሥት፣ “የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ዜግነታቸውን እንዲነጠቁ የተላለፈውን ውሳኔ እንደገና እንዲያጤነው፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን የይሖዋ ምሥክሮች የዜግነት መብታቸው እንዲከበርላቸው ያቀረበው ሐሳብ ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲሁም እስር ቤት ሳሉ እንደሞቱ የተገለጹ የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ምርመራ እንዲካሄድ” ሐሳብ አቅርቧል።

ማብቂያ የሌለው እስራት

ኤርትራ ውስጥ የታሰሩት አብዛኞቹ ወንድ የይሖዋ ምሥክሮች እስራታቸው ማብቂያ የለውም፤ እስኪሞቱ ወይም ሞት አፋፍ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የመፈታት ተስፋ የላቸውም። ይህን ሁኔታ የሚያስተካክል ሕጋዊ አሠራር ወይም አማራጭ በአገሪቱ ስለሌለ፣ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ሊቆጠር ይችላል።

የጊዜ ሰሌዳ

  1. ግንቦት 20, 2024

    በአጠቃላይ 39 የይሖዋ ምሥክሮች ታስረዋል።

  2. የካቲት 1, 2021

    ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ከእስር ቤት ተፈቱ።

  3. ጥር 29, 2021

    አንድ የይሖዋ ምሥክር ከእስር ቤት ተፈታ።

  4. ታኅሣሥ 4, 2020

    ሃያ ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች ከእስር ቤት ተፈቱ።

  5. መጋቢት 6, 2018

    ሃብተሚካኤል መኰነን ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ከተዛወረ በኋላ በ77 ዓመቱ አረፈ።

  6. ጥር 3, 2018

    ሃብተሚካኤል ተስፋማርያም ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ከተዛወረ በኋላ በ76 ዓመቱ አረፈ።

  7. ሐምሌ 2017

    በምዕጢር እስር ቤት የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ በአስመራ አቅራቢያ ወደሚገኘው ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ተዛወሩ።

  8. ሐምሌ 25, 2014

    ሚያዝያ 14 ከታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች አብዛኞቹ ተለቀቁ፤ ሚያዝያ 27 ከታሰሩት መካከል 20ዎቹ ግን አልተፈቱም።

  9. ሚያዝያ 27, 2014

    ሠላሳ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተሰብስበው እያለ ተያዙ።

  10. ሚያዝያ 14, 2014

    በዓመታዊው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ የተገኙ ከ90 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ተያዙ።

  11. ነሐሴ 16, 2012

    አስከፊ በሆነ እስር ቤት ውስጥ የነበረው ዮሃንስ ሃይለ በ68 ዓመቱ ሕይወቱ አለፈ።

  12. ሐምሌ 2011

    አስከፊ በሆነ እስር ቤት ውስጥ የነበረው ምስግና ገብረትንሳኤ በ62 ዓመቱ ሕይወቱ አለፈ።

  13. ሰኔ 28, 2009

    በአንድ የይሖዋ ምሥክር ቤት ሃይማኖታዊ ስብሰባ እየተካሄደ ሳለ ፖሊሶች በድንገት በመግባት በስብሰባው ላይ የተገኙትን 23ቱንም የይሖዋ ምሥክሮች በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው፤ የተያዙት ሰዎች ከ2 እስከ 80 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው።

  14. ሚያዝያ 28, 2009

    ባለሥልጣናቱ፣ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ ሲቀር ሌሎቹን በሙሉ ወደ ምዕጢር እስር ቤት ወሰዷቸው።

  15. ሐምሌ 8, 2008

    ፖሊሶች 24 የይሖዋ ምሥክሮችን ከመኖሪያ ቤታቸውና ከሥራ ቦታቸው ለቅመው አሰሯቸው፤ ከተያዙት አብዛኞቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸው።

  16. ግንቦት 2002

    መንግሥት ከፈቀደላቸው አራት ሃይማኖቶች ውጭ ያሉ ሌሎች ሃይማኖቶች በሙሉ ታገዱ።

  17. ጥቅምት 25, 1994

    በፕሬዚዳንታዊ አዋጅ አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮች ዜግነታቸውንና መሠረታዊ መብቶቻቸውን ተነጠቁ።

  18. መስከረም 17, 1994

    ጳውሎስ እያሱ፣ ይስሃቅ ሞገስ እና ነገደ ተኽለማርያም ያለክስ እና ያለፍርድ ታሰሩ።

  19. 1940ዎቹ

    ኤርትራ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ጀመሩ።