ኅዳር 12, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና
በምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል የሚካሄደው የተፋጠነ የስብሰባ አዳራሾች ግንባታ ሃያ አምስት ዓመታት አስቆጠረ
ወደ 1,000 የሚጠጉ የስብሰባ አዳራሾች ተገንብተዋል!
በምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የሚከናወነው የተፋጠነ የስብሰባ አዳራሾች ግንባታ በ2024 25ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፤ ይህ ቅርንጫፍ ቢሮ በአሁኑ ወቅት ሱዳንን፣ ታንዛንያን፣ ኬንያን እና ደቡብ ሱዳንን ያጠቃልላል።
የበላይ አካሉ የገንዘብ አቅማቸው ውስን ለሆነ አገሮች የሚሆን ፕሮግራም a በ1999 አጽድቆ ነበር፤ ይህ ፕሮግራም በ88 ታዳጊ አገሮች ውስጥ የስብሰባ አዳራሾችን ግንባታ ለማስፋፋት የወጠነ ነበር። ዝግጅቱ፣ የተሻለ የገንዘብ አቅም ያላቸው ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይህን ገንዘባቸውን አቅማቸው ውስን ለሆነ አገራት በልግስና እንዲሰጡ አስችሏል። (2 ቆሮንቶስ 8:13-15) በተጨማሪም የስብሰባ አዳራሾችን የመገንባት ልምድ ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ባሕር ተሻግረው በመጓዝ በየአካባቢው ያሉ ወንድሞችና እህቶችን አሠልጥነዋል። ይህን ሥልጠና ያገኙት አስፋፊዎችም በአካባቢያቸው የሚከናወኑ የግንባታ ሥራዎችን ማስቀጠል ችለዋል። ይህ ዝግጅት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ከሚያሳዩ ምሳሌዎች አንዱ በምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ እየተከናወነ ያለው የስብሰባ አዳራሾች ግንባታ ነው።
በ1999 በምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ ከ23,000 በላይ አስፋፊዎች የነበሩ ቢሆንም የስብሰባ አዳራሾቻቸው ግን 51 ብቻ ነበሩ። ብዙ ጉባኤዎች ስብሰባ የሚያደርጉት ሜዳ ላይ፣ በግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ወይም በሌሎች ቦታዎች ነበር። ከዚህ የግንባታ ፕሮግራም በፊት ወንድሞች የስብሰባ አዳራሾችን የሚገነቡት በአካባቢያቸው ባገኙት ቁሳቁስ ማለትም በእንጨት፣ በጭቃ፣ በቆርቆሮ አልፎ አልፎ ደግሞ ከአመድ ጋር በተቀላቀለ ኩበት ነበር። ኤምቡ፣ ኬንያ በሚገኘው ኪንግፖስት ጉባኤ ውስጥ የነበረችው እህት ናንሲ ሩዊታ ሁኔታውን ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “የስብሰባ አዳራሻችን የተሠራው ከቆርቆሮ ነበር። ሙቀት ሲሆን እንደ ምድጃ ይለበልበናል። በዝናብ ወቅት ደግሞ ቆርቆሮው ከመጮኹ የተነሳ ተናጋሪውን መስማት አንችልም ነበር። አሁን ያ ቆርቆሮ ቀርቶ አዳራሻችን በድንጋይ የተሠራ በመሆኑ በጣም ተደስተናል። አዳራሹ ለመማር ምቹ ከመሆኑም በላይ ውበቱ ለሚመለከቱት ሰዎች ሁሉ ምሥክርነት እየሰጠ ነው።”
የምሥራቅ አፍሪካ ወንድሞች አቅማቸው ውስን ለሆነ አገራት በተዘጋጀው ፕሮጀክት ሥር የመጀመሪያውን አዳራሽ የገነቡት ናይሮቢ፣ ኬንያ ውስጥ ነበር። በአስደናቂ ሁኔታ በቀጣዮቹ 25 ዓመታት ውስጥ በክልሉ የተገነቡት አዳራሾች ቁጥር ከ51 ተነስቶ ወደ 1,000 የሚጠጋ ሆኗል።
በምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የሚገኙ ተጨማሪ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን እስከቀጠሉ ድረስ ተጨማሪ የስብሰባ አዳራሾች ማስፈለጋቸው አይቀርም። በምሥራቅ አፍሪካ ንድፍና ግንባታ ክፍል ረዳት የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ቲሞቲ ስቴፈንስ እንዲህ ብሏል፦ “በአሁኑ ወቅት 126 አዳዲስ ስብሰባ አዳራሾችን መገንባትና ለ200 በላይ ነባር አዳራሾች ላይ ከፍተኛ ጥገና ማድረግ ያስፈልገናል። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ይህ ቁጥር በከፍተኛ መጠን ማደጉ አይቀርም።”
በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በመላው ዓለም የሚኖሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመርዳት እየተከናወነ ያለውን ሥራና እየተከፈለ ያለውን መሥዋዕትነት ከልብ እናደንቃለን። ይሖዋ፣ ተጨማሪ የስብሰባ አዳራሾች በመገንባት ንጹሑን አምልኮ ለመደገፍና ለማስፋፋት እንዲሁም ለስሙ ውዳሴና ክብር ለማምጣት የምናደርገውን ጥረት እንደሚባርክልን እርግጠኞች ነን።—ኢሳይያስ 2:3
a አቅማቸው ውስን ለሆነ አገራት የተደረገው ዝግጅት በ2014 የአካባቢ ንድፍና ግንባታ በተባለው ዝግጅት ተተክቷል።