ሰኔ 3, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የ2024ቱ ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ ልዩ የክልል ስብሰባ ጓዴሎፕ ውስጥ ይጀምራል
‘ምሥራቹን ስበኩ!’ ከተሰኙት ልዩ የክልል ስብሰባዎች የመጀመሪያው ከሰኔ 7 እስከ 9, 2024 ቤይ ማዉ፣ a ጓዴሎፕ ውስጥ በሚገኘው ቪሎድሆም አሜዲ ዲትሆ ይካሄዳል። ከሰኔ እስከ ጥቅምት 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ በጠቅላላው 15 ልዩ የክልል ስብሰባዎች ታቅደዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ለ2020 የታቀዱት ልዩ የክልል ስብሰባዎች ከተሰረዙ ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ልዩ የክልል ስብሰባ ይሆናል።
ከተመረጡ አገሮች የሚጋበዙ ወንድሞችና እህቶች በእነዚህ ልዩ የክልል ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። ፕሮግራሙ በአብዛኛው በተለያዩ ቋንቋዎች የሚተላለፍ ሲሆን ይህም በእነዚህ ትላልቅ ስብሰባዎች ለሚታየው ብዝሃነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። ለአብነት ያህል ጓዴሎፕ ውስጥ ፕሮግራሙ በተመሳሳይ ሰዓት በስፓንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በጓዴሎፕኛ ክሪኦል እና በፈረንሳይኛ ይተላለፋል።
ከተለያዩ አገራት የሚመጡትን ልዑካን ለማስተናገድ የሚደረገው ዝግጅት ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ጓዴሎፕን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በዚያ ካሉት 8,546 ወንድሞችና እህቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከ11 አገራት የሚመጡ 1,500 ወንድሞችና እህቶችን ለመቀበል በሚደረገው ሥራ ለማገዝ ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። ከባሏ ጋር እገዛ ለማበርከት ራሷን ያቀረበች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ለእኔ ልዩ ዓመት ነው! መቼም አልረሳውም። ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር በኅብረት በመሥራት በጣም አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል፤ በአዲሱ ሥርዓት ሕይወት ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ቅምሻ ሆኖልኛል። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በመሆኔ በጣም እኮራለሁ!”
በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያለን ሁሉ፣ በ2024 የታቀዱት ልዩ የክልል ስብሰባዎች በአምላክ ሕዝብ መካከል ያለውን አንድነት እንዲያጠናክሩ ብሎም ለሰማዩ አባታችን ለይሖዋ ክብር እንዲያመጡ እንመኛለን።—ፊልጵስዩስ 1:27
a ቀጥሎ በተዘረዘሩት ቦታዎች ልዩ የክልል ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፦ ቡዳፔስት፣ ሃንጋሪ፤ ዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ፤ ሶፊያ፣ ቡልጋሪያ፤ ሳንቲያጎ፣ ቺሊ ቁጥር 1፤ ሳንቲያጎ፣ ቺሊ ቁጥር 2፤ ፕራግ፣ ቼክ ሪፑብሊክ፣ ሬይኪቪክ፣ አይስላንድ፤ ታምፓ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ፊላደልፊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ሳንቶ ዶሚንጎ፣ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ፤ ቤይ ማዉ፣ ጓዴሎፕ፤ ሊዮን፣ ፈረንሳይ፤ ሄልሲንኪ፣ ፊንላንድ ሱቫ፣ ፊጂ እና አሱንሲዮን፣ ፓራጓይ