ጥር 17, 2020
ደቡብ ኮሪያ
ደቡብ ኮሪያ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ላልሆኑ ሰዎች ለየት ያለ ምሕረት አደረገች
ታኅሣሥ 31, 2019 የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በቅርቡ ከእስር የተፈቱት በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ 1,879 ሰዎች ለየት ያለ ምሕረት እንደሚደረግላቸው ገለጸ። ወንድሞቻችን የወንጀል ሪከርዳቸው ባይሰረዝላቸውም መንግሥት ከሌሎች ገደቦች ነፃ አድርጓቸዋል። ይህ ልዩ ምሕረት ሊገኝ የቻለው በ2018 የሕገ መንግሥት አጣሪ ፍርድ ቤቱ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት አለመስጠት ወንጀል ሳይሆን መብት እንደሆነ በመደንገጋቸው ምክንያት ነው።
የኮሪያ መንግሥት የእስር ቆይታቸውን በጨረሱ ወንጀለኞች ላይ የአምስት ዓመት ገደብ ይጥላል። በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት የማይሰጡ ሰዎችም የወንጀል ሪከርድ ስለሚኖራቸው ቀደም ሲል መንግሥት በወንድሞቻችንም ላይ እንዲህ ያለ ገደብ ይጥል ነበር። በመሆኑም ወንድሞቻችን መንግሥት የሚሰጣቸውን ሕጋዊ ፈቃዶች ለማግኘት ፈተና መፈተንም ሆነ በአንዳንድ የሥራ መስኮች መቀጠር አይችሉም ነበር።
በደቡብ ኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ የሚያገለግለው ወንድም ሆንግ ዴ ኢል እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥት እነዚህን ገደቦች ስላነሳልን አመስጋኞች ነን። ይህ ውሳኔ መንግሥት በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ የታሰሩ ወንድሞቻችን ወንጀለኞች አለመሆናቸውን ሙሉ በሙሉ ለመቀበል እየተቃረበ መሆኑን የሚያሳይ ነው።”
ወደፊትም የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ተጨማሪ አዎንታዊ ውሳኔዎችን እንደሚያደርግ ተስፋ እናደርጋለን። እስካሁን ላገኘናቸው ድሎች ታላቅ ሕግ ሰጪ የሆነው ይሖዋ ግርማና ክብር ሊቀበል ይገባዋል።—ራእይ 4:11