በእምነታቸው ምሰሏቸው | ኢዮብ
ይሖዋ ከሥቃዩ ገላገለው
በመጨረሻም ጸጥታ ነገሠ። የሚሰማው በአረቢያ በረሃ ውስጥ የሚነፍሰው ሞቅ ያለ ነፋስ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ኢዮብ የተሰማውን ሁሉ ተናግሮ ስለጨረሰ ዝም ብሏል። ሦስቱን ጠያቂዎቹን ኤሊፋዝን፣ በልዳዶስንና ሶፋርን ‘እስቲ ወንድ ከሆናችሁ ተናገሩ’ በሚል ስሜት በብስጭት ሲያፈጥባቸው ይታይህ። እነሱ ግን ጠማማ ንግግራቸው፣ ‘ከንቱ ቃላቸውና’ ጎጂ ወቀሳቸው ውጤት አልባ መሆኑን ሲያዩ መሬት መሬቱን ከመመልከት ውጭ ሌላ ምንም ነገር ሊያደርጉ አልቻሉም። (ኢዮብ 16:3) ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን እንደጠበቀ ለማሳመን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጧል።
ኢዮብ የቀረው ነገር ንጹሕ አቋሙ ብቻ እንደሆነ ተሰምቶት መሆን አለበት። ሀብቱን፣ አሥር ልጆቹን፣ የወዳጆቹንና የጎረቤቶቹን አክብሮት አልፎ ተርፎም ጤንነቱን አጥቷል። ቆዳው ጠቁሯል፤ አፈክፍኳል። ሥጋውም ትል ለብሷል። የትንፋሹ ጠረን እንኳ አስጸያፊ ሆኗል። (ኢዮብ 7:5፤ 19:17፤ 30:30) በመሆኑም ሦስቱ ሰዎች በንጹሕ አቋሙ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ኢዮብ በጣም ተበሳጨ። እነሱ እንደሚሉት ያለ ግብዝ ኃጢአተኛ እንዳልሆነ ለማሳመን ቆርጦ ተነሳ። ኢዮብ በመጨረሻ የተናገረው ሐሳብ አፋቸውን አስይዟቸዋል። ያወርዱበት የነበረው የጎጂ ቃላት ናዳም በስተ መጨረሻ አቆመ። የኢዮብ ሥቃይ ግን አሁንም እንዳለ ነው። አሁንም እርዳታ በእጅጉ ያስፈልገዋል።
ኢዮብ ከደረሰበት ችግር የተነሳ ሚዛኑን ስቶ ነበር። መመሪያና እርማት ያስፈልገው ነበር። እውነተኛ ማጽናኛና ማበረታቻም ያስፈልገዋል። ሦስቱ ሰዎች ግን እንዲህ ያለውን ማጽናኛ አልሰጡትም። አንተስ መመሪያና ማጽናኛ አስፈልጎህ ያውቃል? ወዳጄ የምትለው ሰው ስሜትህን ጎድቶት ያውቃል? ይሖዋ አምላክ አገልጋዩን ኢዮብን እንዴት እንደረዳው ማወቅህ ብሎም ኢዮብ የሰጠውን ምላሽ መገንዘብህ ልብህ በተስፋ እንዲሞላ ያደርጋል።
ጥበበኛ እና ደግ መካሪ
የኢዮብ ታሪክ እስካሁን ያልተጠቀሰ አንድ ሰው ያስተዋውቀናል። በቦታው ኤሊሁ የተባለ ወጣት ነበር። ኤሊሁ በዕድሜ የሚበልጡት ሰዎች ሲከራከሩ ጸጥ ብሎ ያዳምጥ ነበር። ሆኖም የሰማው ነገር አላስደሰተውም።
ኤሊሁ በኢዮብ ተቆጥቷል። ኢዮብ “ከአምላክ ይልቅ ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ስለሞከረ” ኤሊሁ በጣም አዘነ። ያም ቢሆን ኤሊሁ የኢዮብን ስሜት ተረድቶለት ነበር። ሥቃዩንና ቅንነቱን ያስተዋለ ከመሆኑም ሌላ ኢዮብ ደግነት የሚንጸባረቅበት ምክርና ማጽናኛ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። ኤሊሁ በሦስቱ የሐሰት አጽናኞች መበሳጨቱ ምንም አያስገርምም! ኢዮብ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ እንዲሁም እምነቱን፣ ክብሩንና ንጹሕ አቋሙን ሲያጣጥሉ ሰምቷቸዋል። ከሁሉ የከፋው ደግሞ አምላክን እንኳ ክፉ እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርብ ጠማማ ንግግር መናገራቸው ነው። ኤሊሁ ከዚህ በላይ ዝም ብሎ መቆየት አልቻለም!—ኢዮብ 32:2-4, 18
“እኔ በዕድሜ ትንሽ ነኝ፤ እናንተ ግን ትላልቆች ናችሁ” ሲል ኤሊሁ ንግግሩን ጀመረ፤ አክሎም “ለእናንተ ካለኝ አክብሮት የተነሳ ከመናገር ዝም አልኩ፤ ደግሞም የማውቀውን ለመናገር አልደፈርኩም” አላቸው። ከዚህ በላይ ግን ዝም ሊል አልቻለም። ኤሊሁ ንግግሩን በመቀጠል “ዕድሜ በራሱ ሰውን ጥበበኛ አያደርገውም፤ ትክክለኛውን ነገር የሚያስተውሉትም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ብቻ አይደሉም” አለ። (ኢዮብ 32:6, 9) ኤሊሁ ቀጥሎ የተናገረው ረጅም ሐሳብ እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነበር። የተናገረበት መንገድ ከኤሊፋዝ፣ ከበልዳዶስና ከሶፋር ጨርሶ የተለየ ነው። ኤሊሁ ኢዮብን በንቀት እንደማያነጋግረው እንዲሁም ቁስሉ ላይ ሌላ ቁስል እንደማይጨምርበት አረጋገጠለት። በተጨማሪም ኢዮብን በስሙ በመጥራትና አጽናኝ ተብዬዎቹ ያደረጉበትን ነገር በማውገዝ ለእሱ ያለውን አክብሮት አሳይቷል። a በትሕትና “አሁን ግን ኢዮብ፣ እባክህ ቃሌን ስማ” አለ።—ኢዮብ 33:1, 7፤ 34:7
ኤሊሁ እንዲህ ሲል ለኢዮብ ግልጽ ምክር ሰጠው፦ “እነዚህን ቃላት ስሰማ ቆይቻለሁ፦ ‘ከበደል ነፃ ነኝ፤ ንጹሕ ነኝ፤ ጥፋትም የለብኝም። አምላክ ግን እኔን ለመቃወም ምክንያት ይፈልጋል።’” ኤሊሁ “ትክክል እንደሆንክ በጣም እርግጠኛ ከመሆንህ የተነሳ ‘እኔ ከአምላክ ይበልጥ ጻድቅ ነኝ’ ትላለህ?” በማለት ዋናው ችግር ምን እንደሆነ ገለጸ። ኤሊሁ ይህን አስተሳሰብ ዝም ብሎ ሊያልፈው አልቻለም። በመሆኑም “እንዲህ ማለትህ ትክክል ስላልሆነ እመልስልሃለሁ” አለው። (ኢዮብ 33:8-12፤ 35:2) ኤሊሁ፣ ኢዮብ በእጅጉ የተበሳጨው ያለውን ሁሉ በማጣቱ እንዲሁም አጽናኝ ተብዬዎቹ ባደረሱበት በደል የተነሳ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ያም ቢሆን “ቁጣ ወደ ክፋት እንዳይመራህ ተጠንቀቅ” በማለት ኢዮብን አስጠነቀቀው።—ኢዮብ 36:18
ኤሊሁ የይሖዋን ደግነት ጎላ አድርጎ ገለጸ
ኤሊሁ ለይሖዋ አምላክ ጥብቅና ቆሟል። እንዲህ በማለት አንድን መሠረታዊ እውነታ በማያሻማ መንገድ ገለጸ፦ “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው! . . . ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ፍትሕን አያዛባም።” (ኢዮብ 34:10, 12) ኢዮብ እንዳመጣለት አክብሮት በጎደለው መንገድ ቢናገርም አምላክ ያልቀጣው መሆኑ ይሖዋ ፍትሐዊና መሐሪ መሆኑን የሚያሳይ አንድ ማስረጃ እንደሆነ ኤሊሁ ገለጸ። (ኢዮብ 35:13-15) በተጨማሪም ኤሊሁ ስለ አምላክ አስተሳሰብ ሁሉን ነገር እንደተረዳ ከማስመሰል ይልቅ “አምላክ እኛ ልናውቀው ከምንችለው በላይ ታላቅ ነው” በማለት በትሕትና ተናገረ።—ኢዮብ 36:26
ኤሊሁ ለኢዮብ ግልጽ ምክር የሰጠው ቢሆንም ያነጋገረው ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ኤሊሁ ኢዮብ አስደሳች ተስፋ እንዳለው ይኸውም ይሖዋ አንድ ቀን ጤንነቱን እንደሚመልስለት ገለጸ። አምላክ ታማኝ አገልጋዩን አስመልክቶ “በወጣትነቱ ጊዜ ከነበረው የበለጠ ሥጋው ይለምልም፤ ብርቱ ወደነበረበት የወጣትነት ዘመኑም ይመለስ” ይላል። የኤሊሁ ደግነት የታየበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ ኢዮብን ቁጭ አድርጎ ከመምከር ይልቅ ተሳትፎ እንዲያደርግ ይጋብዘው የነበረ መሆኑ ነው፤ “ትክክለኛነትህ እንዲረጋገጥ ማድረግ ስለምፈልግ ተናገር” ብሎታል። (ኢዮብ 33:25, 32) ኢዮብ ግን ምንም አልተናገረም። ምናልባትም ዝም ያለው፣ የተሰጠው ምክር ደግነት የሚንጸባረቅበትና አበረታች ከመሆኑ የተነሳ አሜን ብሎ ከመቀበል ውጭ ምንም ምላሽ መስጠት እንደማያስፈልገው ስለተሰማው ይሆናል። እንዲያውም በእፎይታ ስሜት እንባውን አፍስሶ ሊሆን ይችላል።
ከእነዚህ ሁለት ታማኝ ሰዎች ብዙ ትምህርት እናገኛለን። ምክርና ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች እንዴት መርዳት እንደምንችል ከኤሊሁ እንማራለን። እውነተኛ ወዳጅ፣ ጓደኛው ትልቅ ስህተት ሲሠራ ወይም አደገኛ ጎዳና ሲከተል ዝም ብሎ አይመለከተውም። (ምሳሌ 27:6) እኛም እንዲህ ያለ ጓደኛ መሆን እንፈልጋለን። ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዳመጣላቸው ቢናገሩም እንኳ በደግነት እንይዛቸዋለን። እኛ ራሳችን ምክር ሲያስፈልገን ደግሞ የኢዮብ ምሳሌ ምክሩን አልቀበልም ከማለት ይልቅ በትሕትና እንድናዳምጥ ያነሳሳናል። ሁላችንም ምክርና እርማት ያስፈልገናል። እርማት መቀበል ሕይወታችንን ሊያተርፍልን ይችላል።—ምሳሌ 4:13
“ከአውሎ ነፋስ ውስጥ”
ኤሊሁ ስለ ነፋስ፣ ደመና፣ ነጎድጓድና መብረቅ በተደጋጋሚ ጠቅሷል። እንዲያውም ስለ ይሖዋ ሲናገር “የድምፁን ጉምጉምታ፣ ከአፉም የሚወጣውን ነጎድጓድ በጥሞና ስሙ” ብሏል። ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ኤሊሁ ‘አውሎ ነፋስን’ ጠቀሰ። (ኢዮብ 37:2, 9) እሱ እየተናገረ ሳለ እያየለ የሚሄድ የአውሎ ነፋስ ድምፅ መሰማት ጀምሮ የነበረ ይመስላል። በመጨረሻም አስደናቂ ነገር ተከሰተ። ከአውሎ ነፋሱ ውስጥ ይሖዋ ተናገረ!—ኢዮብ 38:1
የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ስለ ፍጥረት የሚሰጠውን ንግግር ማዳመጥ ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው!
በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የይሖዋ ንግግር የተመዘገበባቸውን ምዕራፎች ማንበብ በጣም አስደናቂ ስሜት ይፈጥራል። ከይሖዋ አንደበት የወጣው የእውነት አውሎ ነፋስ የኤሊፋዝን፣ የበልዳዶስንና የሶፋርን የማይረባ ንግግር ጥርግርግ አድርጎ ወስዶታል ሊባል ይችላል። ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ያነጋገራቸው መጨረሻ ላይ ነው። በመጀመሪያ ያተኮረው ኢዮብ ላይ ብቻ ነበር፤ አባት ለልጁ እርማት እንደሚሰጥ ሁሉ ይሖዋም ለሚወደው አገልጋዩ እርማት ሰጠው።
ይሖዋ ኢዮብ የደረሰበትን መከራ ያውቃል። ይሖዋ የሚወዳቸው ልጆቹ መከራ ሲደርስባቸው ምንጊዜም ያዝናል፤ በመሆኑም ለኢዮብ በጣም አዝኖለታል። (ኢሳይያስ 63:9፤ ዘካርያስ 2:8) በሌላ በኩል ደግሞ ኢዮብ ‘ያለእውቀት በመናገር’ ችግሩን እያባባሰ እንዳለ ተገንዝቧል። ስለዚህ ይሖዋ ብዙ ጥያቄዎችን በማቅረብ ለኢዮብ እርማት ሰጠው። ጥያቄውን ሲጀምር “ምድርን በመሠረትኩ ጊዜ አንተ የት ነበርክ? ማስተዋል አለኝ የምትል ከሆነ ንገረኝ” አለው። በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያለው የፍጥረት ሥራ ሀ ብሎ ሲጀምር “አጥቢያ ከዋክብት” ማለትም የአምላክ መላእክት በደስታ ጮኸው ነበር። (ኢዮብ 38:2, 4, 7) መቼም ኢዮብ ይህን እንደማያውቅ ግልጽ ነው።
ቀጥሎም ይሖዋ ስለ ፍጥረት ሥራዎቹ መናገር ጀመረ። ሥነ ፈለክን፣ ሥነ ሕይወትን፣ ሥነ ምድርና ፊዚክስን ጨምሮ በተፈጥሮ ሳይንስ ውስጥ የሚካተቱ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በአጭሩ አስቃኘው። ኢዮብ የሚያውቃቸውን በርካታ እንስሳት አንድ በአንድ ጠቀሰለት፤ ከእነዚህ መካከል አንበሳ፣ ቁራ፣ የተራራ ፍየል፣ የዱር አህያ፣ የዱር በሬ፣ ሰጎን፣ ፈረስ፣ ሲላ፣ ንስር፣ ብሄሞት (ጉማሬ ሳይሆን አይቀርም) እና ሌዋታን (አዞ ሳይሆን አይቀርም) ይገኙበታል። የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ስለ ፍጥረት የሚሰጠውን ንግግር ማዳመጥ ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው! b
ስለ ትሕትና እና ስለ ፍቅር አስተማረው
ይሖዋ ይህን ሁሉ ነገር የነገረው ለምንድን ነው? ኢዮብ ትሕትና መማር ያስፈልገው ስለነበረ ነው። ኢዮብ፣ ይሖዋ እንደበደለው በማሰብ መማረሩ ከአፍቃሪ አባቱ ያርቀዋል፤ ይህ ደግሞ መከራውን ከማባባስ በቀር ምንም የሚፈይድለት ነገር የለም። በመሆኑም ይሖዋ፣ አስደናቂ ነገሮችን ሲፈጥር ኢዮብ የት እንደነበር ብሎም እነዚህን ፍጥረታት መመገብ፣ መቆጣጠር አሊያም ማላመድ ይችል እንደሆነ በተደጋጋሚ ጠየቀው። ኢዮብ የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች እንኳ መቆጣጠር ሳይችል ፈጣሪው ላይ ለመፍረድ እንዴት ይነሳል? የይሖዋ መንገድና ሐሳብ ኢዮብ በውስን አእምሮው ሊረዳ ከሚችለው እጅግ የላቀ አይደለም?
ኢዮብ ከይሖዋ ጋር አልተከራከረም፤ ትክክል መሆኑን ለማሳየት ማስረጃ አላቀረበም ወይም ሰበብ አስባብ አልደረደረም
ይሖዋ የተናገረው ሐሳብ ለኢዮብ ያለውን ጥልቅ ፍቅርም ያሳያል። ይሖዋ ኢዮብን እንዲህ ያለው ያህል ነበር፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ይህን ሁሉ ነገር መፍጠርና መንከባከብ ከቻልኩ አንተን መንከባከብ እንዴት ያቅተኛል? መከራ ሲያጋጥምህ እንዴት እተውሃለሁ? ልጆችህን፣ ሀብትህንና ጤንነትህን እንዴት እወስድብሃለሁ? ያጣኸውን ነገር በሙሉ መልሼ ልሰጥህና ከአስከፊ መከራህ ልገላግልህ የምችለውስ እኔ ብቻ አይደለሁም?’
ኢዮብ ይሖዋ ላቀረባቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጠው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። ኢዮብ አልተከራከረም፤ ትክክል መሆኑን ለማሳየት ማስረጃ አላቀረበም ወይም ሰበብ አስባብ አልደረደረም። ምንም እንደማያውቅ አምኖ ተቀብሏል፤ እንዲሁም ማስተዋል በጎደለው መንገድ በመናገሩ ንስሐ ገብቷል። (ኢዮብ 40:4, 5፤ 42:1-6) ይህ ሁኔታ የኢዮብን አስደናቂ እምነት ያሳያል። ያ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም በይሖዋ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት ይዞ ቀጥሏል። ይሖዋ እርማት ሲሰጠው በትሕትና ተቀብሏል። እያንዳንዳችን ‘እርማትና ምክር ሲሰጠኝ በትሕትና እቀበላለሁ?’ እያልን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። ደግሞም ምክር የማያስፈልገው ማንም የለም። ምክር ስንቀበል ኢዮብን በእምነቱ እንደምንመስለው እናሳያለን።
‘ስለ እኔ እውነቱን አልተናገራችሁም’
ቀጥሎም ይሖዋ ኢዮብን ለማጽናናት እርምጃ ወሰደ። ከሦስቱ አጽናኝ ተብዬዎች መካከል በዕድሜ ታላቅ እንደሆነ የሚታመነውን ኤሊፋዝን “አገልጋዬ ኢዮብ እንዳደረገው ስለ እኔ እውነቱን ስላልተናገራችሁ በአንተና በሁለቱ ጓደኞችህ ላይ ቁጣዬ ነዷል” አለው። (ኢዮብ 42:7) እስቲ ስለ እነዚህ ቃላት ቆም ብለህ አስብ። ይሖዋ ሦስቱ ሰዎች የተናገሩት በሙሉ ውሸት እንደሆነ ኢዮብ የተናገረው ነገር በሙሉ ደግሞ እውነት እንደሆነ መግለጹ ነበር? እንደዚያ እያለ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። c ሆኖም በኢዮብና በሦስቱ ሰዎች መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ኢዮብ ልቡ ተሰብሮ፣ በመሪር ሐዘን ተውጦና በሐሰት ክስ ቆስሎ ነበር። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ እንዳመጣለት ቢናገር የሚያስደንቅ አይደለም። ኤሊፋዝና ሁለቱ ጓደኞቹ ግን እንዲህ ያለ መከራ አልደረሰባቸውም። ትዕቢተኞችና ደካማ እምነት ያላቸው በመሆናቸው ሆን ብለው ክፉ ቃል ተናግረዋል። ንጹሑን ሰው መክሰሳቸው ሳያንስ ይሖዋን ክፉና ጨካኝ አምላክ እንደሆነ አድርገው ገልጸውታል!
ከዚህ አንጻር ይሖዋ እነዚህ ሰዎች ብዙ ወጪ የሚያስወጣ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ መጠየቁ የሚያስገርም አይደለም። ሰባት ኮርማዎችና ሰባት አውራ በጎች እንዲያቀርቡ አዟቸዋል፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሥዋዕት ነበር፤ ምክንያቱም ከጊዜ በኋላ የወጣው የሙሴ ሕግ ሊቀ ካህናቱ መላው ብሔር በደለኛ እንዲሆን የሚያደርግ ኃጢአት ቢሠራ አንድ ኮርማ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 4:3) በሙሴ ሕግ ሥር መሥዋዕት ሆነው ከሚቀርቡት እንስሳት መካከል ብዙ ወጪ የሚያስወጣው ኮርማ ነው። ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ይሖዋ የኢዮብ ከሳሾች የሚያቀርቡትን መሥዋዕት ለመቀበል ፈቃደኛ የሚሆነው በመጀመሪያ ኢዮብ ለእነሱ ከጸለየ እንደሆነ ገልጿል። d (ኢዮብ 42:8) ኢዮብ አምላኩ እሱን ደግፎ ሲናገር መስማቱና የይሖዋ ፍትሕ ሲያሸንፍ ማየቱ ምንኛ አስደስቶት ይሆን!
“አገልጋዬ ኢዮብም ለእናንተ ይጸልያል።”—ኢዮብ 42:8
ኢዮብ የታዘዘውን ነገር እንደሚያደርግ ይኸውም ስሜቱን እጅግ የጎዱትን ሰዎች ይቅር እንደሚል ይሖዋ ተማምኖ ነበር። ኢዮብም ቢሆን ያደረገው ይህንኑ ነው። (ኢዮብ 42:9) ታዛዥ መሆኑ ንጹሕ አቋሙን እንደጠበቀ የሚያሳይ ከሁሉ የላቀ ማስረጃ ነበር። ደግሞም ታዛዥነቱ አስደናቂ በረከቶች አስገኝቶለታል።
“ከአንጀት የሚራራ”
ይሖዋ ከኢዮብ ጋር በተያያዘ “ከአንጀት የሚራራና መሐሪ እንደሆነ” አሳይቷል። (ያዕቆብ 5:11 የግርጌ ማስታወሻ) እንዴት? ይሖዋ ጤንነቱን መልሶለታል። ኢዮብ ልክ ኤሊሁ እንደተናገረው “በወጣትነቱ ጊዜ ከነበረው የበለጠ ሥጋው” ሲለመልም ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስበው! በስተ መጨረሻ ቤተሰቡና ወዳጆቹ ድጋፍ አደረጉለት፤ አዘኑለት እንዲሁም ስጦታ አመጡለት። ይሖዋ የኢዮብን ሀብት እጥፍ አድርጎ መለሰለት። ከሁሉ የከፋው የኢዮብ ቁስል ልጆቹን ማጣቱ ነበር፤ ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገለት? ኢዮብና ሚስቱ ከዚህ በኋላ አሥር ልጆች በመውለዳቸው የተወሰነ ማጽናኛ አግኝተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም! በተጨማሪም ይሖዋ በተአምር የኢዮብን ዕድሜ ጨምሮለታል። ከዚህ በኋላ ኢዮብ 140 ዓመት ኖረ፤ እስከ አራት ትውልድም ድረስ ልጆችንና የልጅ ልጆችን አየ። ዘገባው “በመጨረሻም ኢዮብ ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ” በማለት ይደመድማል። (ኢዮብ 42:10-17) በገነት ውስጥ ደግሞ ኢዮብና ሚስቱ ሰይጣን የነጠቃቸውን አሥር ልጆች ጨምሮ ከመላው ቤተሰባቸው ጋር በድጋሚ ይገናኛሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29
ይሖዋ ኢዮብን አትረፍርፎ የባረከው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ሲነግረን “ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል” ይላል። (ያዕቆብ 5:11) ኢዮብ ያጋጠመው መከራ ብዙዎቻችን ልናስበው እንኳ ከምንችለው በላይ ነው። “ጽናት” የሚለው ቃል ኢዮብ ፈተናውን ችሎ በማለፍ ብቻ እንዳልተወሰነ ይጠቁመናል። የጸናው እምነቱና ለይሖዋ ያለው ፍቅር ሳይቀዘቅዝ ነው። ኢዮብ ከመመረር ይልቅ ሆን ብለው የጎዱትን ሰዎች ጭምር ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነበር። አስደናቂ የሆነውን ተስፋውንም ሆነ ውድ የሆነውን ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መኖር ችሏል።—ኢዮብ 27:5
ሁላችንም መጽናት ያስፈልገናል። ሰይጣን ኢዮብ ላይ እንዳደረገው ሁሉ እኛንም ተስፋ ሊያስቆርጠን ይሞክራል። ሆኖም በእምነት ከጸናን፣ ትሑትና ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኞች ከሆንን ብሎም ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን እኛም ውድ የሆነውን ተስፋችንን አጥብቀን መያዝ እንችላለን። (ዕብራውያን 10:36) ሰይጣንን ለማሳፈርና አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን ለማስደሰት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ኢዮብን በእምነቱ መምሰል ነው!
a ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር በጣም ረጅም ሐሳብ ተናግረዋል፤ ከኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ዘጠኙ ምዕራፎች የእነሱን ንግግሮች የያዙ ናቸው። ሆኖም ዘገባው አንድም ቦታ ላይ ኢዮብን በስሙ እንደጠሩት አይገልጽም።
b አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይሖዋ እውነታውን በቀጥታ የሚያስቀምጡ አገላለጾችን ተጠቅሟል፤ ሌሎች ቦታዎች ላይ ግን ዘይቤያዊ አገላለጾችን ተጠቅሟል። (ለምሳሌ ኢዮብ 41:1, 7, 8, 19-21ን ተመልከት።) ሁለቱንም ዘዴዎች የተጠቀመው ለአንድ ዓላማ ይኸውም ኢዮብ በፈጣሪው ኃይል እንዲደመም ለማድረግ ነው።
c እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ኤሊፋዝ የተናገረውን አንድ ሐሳብ ጠቅሷል። (ኢዮብ 5:13፤ 1 ቆሮንቶስ 3:19) ኤሊፋዝ የተናገረው ነገር በራሱ እውነተኛ ነበር፤ ሆኖም ይህ ሐሳብ በኢዮብ ላይ እንደሚሠራ አድርጎ መግለጹ ትክክል አልነበረም።
d ኢዮብ ሚስቱን ወክሎ እንዲህ ያለ መሥዋዕት እንዲያቀርብ እንደተጠየቀ ዘገባው አይገልጽም።