ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር እነማን ናቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር ኢየሱስ ካቀረባቸው ንግግሮች በአንዱ ላይ የተጠቀሱ በምናብ የተፈጠሩ ገጸ ባሕርያት ናቸው። (ሉቃስ 16:19-31) በታሪኩ ላይ የተጠቀሱት እነዚህ ሰዎች ሁለት የተለያዩ ቡድኖችን ያመለክታሉ፦ (1) በኢየሱስ ዘመን የነበሩትን ኩሩ የሃይማኖት መሪዎች እና (2) ዝቅ ተደርገው ይታዩ የነበሩትን ሆኖም ለኢየሱስ መልእክት በጎ ምላሽ የሰጡትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች።
በዚህ ርዕስ ውስጥ፦
ኢየሱስ ስለ ሀብታሙ ሰውና ስለ አልዓዛር ምን ብሏል?
ሉቃስ ምዕራፍ 16 ላይ ኢየሱስ ሁኔታቸው ሙሉ በሙሉ ስለተለወጠ ሁለት ሰዎች ተናግሯል።
ኢየሱስ የተናገረው ታሪክ በአጭሩ ይህ ነው፦ በቅንጦት የሚኖር አንድ ሀብታም ሰው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ ሰው ደጃፍ ላይ እያመጡ የሚያስቀምጡት አልዓዛር የተባለ አንድ ለማኝ ነበር። ይህ ለማኝ ከሀብታሙ ሰው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ለመብላት ይመኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ለማኙ ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት። ሀብታሙም ሰው ሞተና ተቀበረ። በታሪኩ ላይ ሁለቱም ሰዎች ከሞቱ በኋላም ራሳቸውን እንደሚያውቁ ተደርገው ተገልጸዋል። ሀብታሙ ሰው በሚንቀለቀል እሳት እየተሠቃየ ስለነበር አብርሃምን ‘አልዓዛር የጣቱን ጫፍ ውኃ ውስጥ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ ላከው’ በማለት ጠየቀው። አብርሃም ግን የሀብታሙን ሰው ጥያቄ አልተቀበለውም፤ ከዚህ ይልቅ አሁን የሁለቱ ሰዎች ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንደተቀየረና በመካከላቸው ማንም ሊሻገረው የማይችል ትልቅ ገደል እንደተደረገ ገለጸለት።
ታሪኩ ቃል በቃል የተፈጸመ ነገር ነው?
አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ አንድ ትምህርት ለማስተላለፍ ሲል የተጠቀመበት ምሳሌ ነው። ምሁራንም ቢሆኑ ይህ ታሪክ ምሳሌያዊ እንደሆነ ይስማማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በ1912 በታተመ የሉተር መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝ አንድ ንዑስ ርዕስ ይህ ታሪክ ምሳሌያዊ መሆኑን ይገልጻል። በተጨማሪም በካቶሊክ ጀሩሳሌም ባይብል ላይ የሚገኝ አንድ የግርጌ ማስታወሻ “ይህ ታሪክ፣ በታሪክ ዘመን ውስጥ የኖረን የትኛውንም ግለሰብ አያመለክትም፤ ከዚህ ይልቅ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ነው” የሚል ሐሳብ አስፍሯል።
ኢየሱስ ከሞት በኋላ ስለሚኖር ሕይወት እያስተማረ ነበር? አንዳንድ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በሲኦል እሳት እንደሚሠቃዩ እንዲሁም አብርሃምና አልዓዛር በሰማይ እንዳሉ መናገሩ ነበር? ይህ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳዩ የተለያዩ ማስረጃዎች አሉ።
ለምሳሌ ያህል፦
ሀብታሙ ሰው ቃል በቃል በሚንቀለቀል እሳት ውስጥ እየተሠቃየ ከሆነ እሳቱ በአልዓዛር ጣት ጫፍ ላይ ያለውን ውኃ አያተነውም?
ውኃው ባይተን እንኳ አንዲት ጠብታ ውኃ ቃል በቃል በእሳት እየተሠቃየ ላለ ሰው እፎይታ ልትሰጠው ትችላለች?
ኢየሱስ ይህን ምሳሌ እስከተናገረበት ጊዜ ድረስ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም እንደሌለ በግልጽ ተናግሯል፤ ታዲያ አብርሃም እንዴት በሰማይ ሊኖር ይችላል?—ዮሐንስ 3:13
ይህ ታሪክ ሲኦል መቃጠያ ቦታ እንደሆነ የሚገልጸውን ሃይማኖታዊ ትምህርት ይደግፋል?
አይደግፍም። አንዳንዶች ይህ ታሪክ ቃል በቃል የተፈጸመ ባይሆንም ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ እንደሚሄዱና መጥፎ ሰዎች በሲኦል እሳት እንደሚሠቃዩ የሚያመለክት ነው ብለው ይከራከራሉ። a
እንዲህ ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው? አይደለም።
ሲኦል መሠቃያ ቦታ ነው የሚለው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ከሚናገረው ሐሳብ ጋር አይስማማም። መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ሰዎች ሁሉ ከሞቱ በኋላ በሰማይ አስደሳች ሕይወት እንደሚኖራቸው አሊያም መጥፎ ሰዎች በሲኦል እሳት እንደሚሠቃዩ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት በግልጽ ይናገራል።—መክብብ 9:5
ስለ ሀብታሙ ሰውና ስለ አልዓዛር የሚገልጸው ታሪክ ትርጉም ምንድን ነው?
ይህ ታሪክ ሁለት ቡድኖች ሁኔታቸው ሙሉ በሙሉ የሚቀየርበት ጊዜ እንደሚመጣ ይጠቁማል።
ሀብታሙ ሰው “ገንዘብ ወዳድ” የሆኑትን የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች እንደሚያመለክት ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (ሉቃስ 16:14) እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ሲናገር ቢሰሙም መልእክቱን ተቃውመዋል። በተጨማሪም ተራ የሆኑትን ሰዎች ይንቋቸው ነበር።—ዮሐንስ 7:49
አልዓዛር በአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ የተናቁትን ሆኖም የኢየሱስን መልእክት የተቀበሉትን ሰዎች ያመለክታል።
ሁለቱም ቡድኖች ያሉበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተለውጧል።
የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች የአምላክን ሞገስ እንዳገኙ ይሰማቸው ነበር። ሆኖም የኢየሱስን መልእክት ባለመቀበላቸው እነሱም ሆኑ የሚያቀርቡት አምልኮ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጣ፤ ከዚህ አንጻር እንደሞቱ ሊቆጠሩ ይችላሉ። ኢየሱስና ተከታዮቹ የሚሰብኩት መልእክት ደግሞ እነዚህን ሰዎች ለሥቃይ የሚዳርግ ነበር።—ማቴዎስ 23:29, 30፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29-33
በሃይማኖት መሪዎቻቸው ለረጅም ጊዜ ችላ ተብለው የነበሩት ተራዎቹ ሰዎች አሁን ሞገስ አግኝተዋል። ብዙዎች ኢየሱስ ያስተማረውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት የተቀበሉ ሲሆን ከትምህርቱም ጥቅም አግኝተዋል። አሁን ለዘላለም የአምላክን ሞገስ የማግኘት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል።—ዮሐንስ 17:3