“አባትህንና እናትህን አክብር” ሲባል ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለው ትእዛዝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ ይገኛል። (ዘፀአት 20:12፤ ዘዳግም 5:16፤ ማቴዎስ 15:4፤ ኤፌሶን 6:2, 3) ይህ ትእዛዝ የሚከተሉትን አራት ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግን ይጨምራል።
አድናቆት አሳይ። አባትህና እናትህ ለአንተ ሲሉ ላደረጓቸው ነገሮች በሙሉ አመስጋኝ መሆንህን እነሱን ለማክበር ያነሳሳሃል። የሚሰጡህን መመሪያ ከፍ አድርገህ በመመልከት አድናቆትህን ማሳየት ትችላለህ። (ምሳሌ 7:1, 2፤ 23:26) መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆችህን ‘ክብርህ’ እንደሆኑ አድርገህ ልትመለከታቸው ማለትም ልትኮራባቸው እንደሚገባ ይናገራል።—ምሳሌ 17:6
ለሥልጣናቸው ተገዛ። አምላክ ለአባትህና ለእናትህ ሥልጣን እንደሰጣቸው ስለምትገነዘብ በተለይ ልጅ ሳለህ ታከብራቸው ነበር። ቆላስይስ 3:20 ልጆችን አስመልክቶ ሲናገር “በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ጌታን ያስደስተዋልና” ይላል። ኢየሱስም እንኳ በልጅነቱ ወላጆቹን በፈቃደኝነት ይታዘዝ ነበር።—ሉቃስ 2:51
አክብራቸው። (ዘሌዋውያን 19:3፤ ዕብራውያን 12:9) አክብሮት ማሳየት ከምትናገረው ነገርና ከምትናገርበት መንገድ ጋር ተያያዥነት አለው። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ወላጆች እነሱን ማክበር ከባድ እንዲሆንብህ የሚያደርግ ነገር ይፈጽሙ ይሆናል። በዚህ ጊዜም እንኳ ልጆች ወላጆቻቸውን የሚያቃልል ነገር ከመናገር እንዲሁም እነሱን የሚያበሳጭ ድርጊት ከመፈጸም በመቆጠብ እንደሚያከብሯቸው ማሳየት ይችላሉ። (ምሳሌ 30:17) መጽሐፍ ቅዱስ አባትን ወይም እናትን መሳደብ ከባድ ኃጢአት እንደሆነ ይናገራል።—ማቴዎስ 15:4
የሚያስፈልጋቸውን አሟላላቸው። ወላጆችህ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የአንተ ድጋፍ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት የምትችለውን ሁሉ በማድረግ እንደምታከብራቸው ማሳየት ትችላለህ። (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8) ለምሳሌ ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እናቱ እንክብካቤ የምታገኝበትን መንገድ አመቻችቶ ነበር።—ዮሐንስ 19:25-27
አባትንና እናትን ከማክበር ጋር በተያያዘ የተሳሳቱ አመለካከቶች
የተሳሳተ አመለካከት፦ አባትንና እናትን ማክበር ትዳርህን እንዲቆጣጠሩ መፍቀድን ይጨምራል።
እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ከቤተሰብ ዝምድና ይልቅ የትዳር ጥምረት ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራል። ዘፍጥረት 2:24 “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል” ይላል። (ማቴዎስ 19:4, 5) ይህ ሲባል ግን ባለትዳሮች ከወላጆቻቸው ወይም ከዘመዶቻቸው ጠቃሚ ምክር መቀበል የለባቸውም ማለት አይደለም። (ምሳሌ 23:22) ሆኖም ባለትዳሮች ከትዳራቸው ጋር በተያያዘ የዘመዶቻቸው ቦታ እስከምን ድረስ ሊሆን እንደሚገባ ገደብ ማውጣታቸው ተገቢ ነው።—ማቴዎስ 19:6
የተሳሳተ አመለካከት፦ አባትህና እናትህ ገደብ የለሽ ሥልጣን አላቸው።
እውነታው፦ አምላክ ከቤተሰብ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ለወላጆች ሥልጣን የሰጠ ቢሆንም ሰዎች ያላቸው የትኛውም ሥልጣን ገደብ አለው፤ ሰዎች ከአምላክ የሚበልጥ ሥልጣን ፈጽሞ ሊኖራቸው አይችልም። ለምሳሌ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአምላክን ሕግ እንዲጥሱ የሚያደርግ ትእዛዝ በሰጣቸው ጊዜ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” የሚል መልስ ሰጥተዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:27-29) በተመሳሳይም ልጆች “ከጌታ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ” ማለትም የወላጆቻቸው ትእዛዝ ከአምላክ ሕግ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ ወላጆቻቸውን ይታዘዛሉ።—ኤፌሶን 6:1
የተሳሳተ አመለካከት፦ አባትህንና እናትህን ማክበር የእነሱን ሃይማኖት መከተልን ይጨምራል።
እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸው ነገሮች እውነት መሆን አለመሆናቸውን መርምረን እንድናረጋግጥ ያበረታታናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:11፤ 1 ዮሐንስ 4:1) በዚህ መልኩ ምርምር የሚያደርግ ሰው ውሎ አድሮ ከወላጆቹ የተለየ እምነት ለመከተል ይመርጥ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃምን፣ ሩትንና ሐዋርያው ጳውሎስን ጨምሮ የወላጆቻቸውን እምነት ያልተከተሉ የበርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን ታሪክ ይዟል።—ኢያሱ 24:2, 14, 15፤ ሩት 1:15, 16፤ ገላትያ 1:14-16, 22-24
የተሳሳተ አመለካከት፦ አባትህንና እናትህን ለማክበር የቀድሞ አባቶችን ከማምለክ ጋር ተያይዘው በሚደረጉት ባሕላዊ ወጎች ላይ መሳተፍ ይኖርብሃል።
እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” ይላል። (ሉቃስ 4:8) የቀድሞ አባቶችን የሚያመልክ ሰው አምላክን የሚያሳዝን ድርጊት እየፈጸመ ነው። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሙታን ምንም አያውቁም’ ይላል። ሙታን ለእነሱ አክብሮት ለማሳየት ተብሎ ስለሚደረገው ነገር ምንም አያውቁም፤ በተጨማሪም በሕይወት ያሉትን ሰዎች ሊረዱም ሆነ ሊጎዱ አይችሉም።—መክብብ 9:5, 10፤ ኢሳይያስ 8:19