ዳግመኛ መወለድ ሲባል ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ዳግመኛ መወለድ” የሚለው አገላለጽ ዳግም የተወለደው ግለሰብ ከአምላክ ጋር የነበረው ግንኙነት አዲስ መልክ እንደሚኖረው ያመለክታል። (ዮሐንስ 3:3, 7) አምላክ ዳግመኛ የተወለዱትን ሰዎች ልጆቹ አድርጎ ይወስዳቸዋል። (ሮም 8:15, 16፤ ገላትያ 4:5፤ 1 ዮሐንስ 3:1) ሕጋዊ በሆነ መንገድ በጉዲፈቻ እንደተወሰዱ ልጆች ሁሉ እነዚህም ሰዎች የነበሩበት ሁኔታ ይለወጣል፤ በሌላ አባባል የአምላክ ቤተሰብ አባል ይሆናሉ።—2 ቆሮንቶስ 6:18
ዳግመኛ መወለድ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ “አንድ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ብሏል። (ዮሐንስ 3:3) በመሆኑም አንድ ሰው ዳግመኛ መወለዱ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ለመግዛት ዝግጁ እንዲሆን ያስችለዋል። ይህ መንግሥት የሚገዛው ከሰማይ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ‘እንደ አዲስ መወለድ’ በሰማይ የተጠበቀውን ርስት ለመውረስ ዝግጁ እንደሚያደርግ የሚገልጸው ለዚህ ነው። (1 ጴጥሮስ 1:3, 4) ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ‘አብረው እንደሚነግሡ’ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:12፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21, 22
አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ ዳግመኛ የሚወለዱት ሰዎች “ከውኃና ከመንፈስ” እንደሚወለዱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:5) ይህ አገላለጽ በመጀመሪያ በውኃ መጠመቅን ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅን ያመለክታል።—የሐዋርያት ሥራ 1:5፤ 2:1-4
ዳግመኛ የተወለደው የመጀመሪያው ሰው ኢየሱስ ነበር። በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ቀብቶታል (ወይም አጥምቆታል)። በመሆኑም ኢየሱስ በሰማይ የመኖር ተስፋ ያለው የአምላክ ልጅ ሆኖ ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ተወልዷል። (ማርቆስ 1:9-11) አምላክ፣ ኢየሱስን መንፈሳዊ አካል ይዞ ከሞት እንዲነሳ በማድረግ ይህን ተስፋ ፈጽሟል።—የሐዋርያት ሥራ 13:33
ዳግመኛ የተወለዱ ሌሎች ሰዎችም መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት በውኃ ተጠምቀዋል። a (የሐዋርያት ሥራ 2:38, 41) ከዚያም በሰማይ የመኖር የተረጋገጠ ተስፋ የሚኖራቸው ሲሆን አምላክ እነሱን ከሞት በማስነሳት ይህን ተስፋ ይፈጽመዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:42-49
ሰዎች ዳግመኛ መወለድን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት
የተሳሳተ አመለካከት፦ አንድ ሰው መዳን ለማግኘት ወይም ክርስቲያን ለመሆን ዳግመኛ መወለድ አለበት።
እውነታው፦ የክርስቶስ መሥዋዕት መዳን የሚያስገኘው ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ለሚገዙ ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ ለሚኖሩ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎችም ጭምር ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2፤ ራእይ 5:9, 10) በሁለተኛው ቡድን ውስጥ የታቀፉ ክርስቲያኖች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።—መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:1-5
የተሳሳተ አመለካከት፦ አንድ ሰው ከፈለገ ዳግመኛ መወለድ ይችላል።
እውነታው፦ ከአምላክ ጋር ዝምድና የመመሥረትና መዳን የማግኘት በር የተከፈተው ለሁሉም ሰዎች ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4፤ ያዕቆብ 4:8) ዳግመኛ የሚወለዱትን ማለትም በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡትን የሚመርጠው ግን አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዳግመኛ መወለድ “የተመካው በአንድ ሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን ምሕረት በሚያደርገው አምላክ ላይ” እንደሆነ ይናገራል። (ሮም 9:16) ‘ዳግመኛ መወለድ’ የሚለው አገላለጽ ‘ከላይ መወለድ’ ተብሎም ሊተረጎም ይችላል፤ ይህም ዳግመኛ የሚወለዱት ሰዎች ይህን መብት የሚያገኙት ‘ከላይ’ ወይም ከአምላክ መሆኑን ያረጋግጣል።—ዮሐንስ 3:3፣ የግርጌ ማስታወሻ
a መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ የተጠመቁት ቆርኔሌዎስና አብረውት የነበሩት ሰዎች ብቻ ናቸው።—የሐዋርያት ሥራ 10:44-48