በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—አልባኒያ እና ኮሶቮ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—አልባኒያ እና ኮሶቮ

 “ይሖዋን እንዲህ በተሟላ ሁኔታ ማገልገል እችላለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር።” እንዲህ በማለት ስሜቷን የገለጸችው የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ከእንግሊዝ ወደ አልባኒያ የሄደችው ግዌን ነች። a

 ግዌን ‘በብሔራት ሁሉ መካከል ያሉ የከበሩ ነገሮችን’ በመሰብሰቡ ሥራ ለመካፈል ወደ አልባኒያ ከተዛወሩት በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አንዷ ናት። (ሐጌ 2:7) እነዚህ ወንጌላውያን እንዲህ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ወደዚያ ተዛውረው ለማገልገል የትኞቹን ማስተካከያዎች አድርገዋል? ያገኟቸው በረከቶች ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በጽናት ለመቋቋም የረዷቸው እንዴት ነው?

ሁኔታቸው ቢለያይም ፍላጎታቸው አንድ ነው

 በአልባኒያ ለማገልገል የመጡት አስፋፊዎች በሙሉ እንዲህ ለማድረግ የተነሳሱበት ምክንያት አንድ ነው፤ ይኸውም ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲሁም ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት ያላቸው ፍላጎት ነው።

 ወደ አልባኒያ ከመዛወራቸው በፊት አገልግሎታቸውን ለማስፋት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል። ይህም በሌላ አገር ማገልገል የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ረድቷቸዋል። ግዌን እንዲህ ብላለች፦ “በመጀመሪያ በምኖርበት ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ የአልባኒያኛ ቡድን ተዛወርኩ። ከዚያም በአልባኒያ በተካሄደ የክልል ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። በኋላም ቋንቋውን ይበልጥ ለመማር አልባኒያ ሄጄ እዚያ የተወሰነ ጊዜ ቆየሁ።”

ግዌን

 ማኑዌላ የ23 ዓመት ወጣት ሳለች አንድን አነስተኛ ጉባኤ ለመርዳት በአገሯ በጣሊያን ወደሚገኝ ሌላ አካባቢ ተዛወረች። እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ ለአራት ዓመት አገለገልኩ። ከዚያም በአልባኒያ ተጨማሪ ሰባኪዎች እንደሚያስፈልጉ ተረዳሁ። ስለዚህ እዚያ ሄጄ ለተወሰኑ ወራት በአቅኚነት ለማገልገል ዝግጅት አደረግኩ።”

ማኑዌላ (መሃል)

 ፌደሪካ የሰባት ዓመት ልጅ ሳለች በአንድ የክልል ስብሰባ ላይ ስለ አልባኒያ የሚገልጽ ሪፖርት ሲቀርብ ሰማች። እንዲህ ብላለች፦ “ሪፖርቱን ያቀረበው ወንድም በአልባኒያ የሚገኙ አስፋፊዎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንዳስጀመሩና ፍላጎት ያላቸው በርካታ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ እንደሚገኙ ገለጸ። ይህን ስሰማ ወላጆቼን ‘አልባኒያ መሄድ እፈልጋለሁ’ አልኳቸው። ይህን ስላቸው መጀመሪያ ላይ ተገርመው ነበር። ሆኖም አባቴ ‘እስቲ ስለ ጉዳዩ ጸልዪ። የይሖዋ ፈቃድ ከሆነ እሱ ጸሎትሽን ይሰማሻል’ አለኝ። ከተወሰኑ ወራት በኋላ በቤተሰብ ደረጃ በአልባኒያ እንድናገለግል ተጋበዝን!” ይህ ከሆነ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። አሁን ፌደሪካ፣ ኦርገስ ከተባለ ወንድም ጋር ትዳር መሥርታለች። ሁለቱም በአልባኒያ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው።

ኦርገስ እና ፌደሪካ

 ጃንፒዬሮ ጡረታ ከወጣ በኋላ ከባለቤቱ ከግሎሪያ ጋር ወደ አልባኒያ ተዛወረ። እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችንን ያሳደግነው በጣሊያን ነው። ሦስቱ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ወደ ሌላ አገር ተዛውረዋል። ‘ወደ መቄዶንያ መሻገር ትችላለህ?’ የሚለውን የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ ስናነብ ልባችን በእጅጉ ተነካ። የጡረታ ገንዘቤን ተጠቅመን በአልባኒያ ማገልገል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ቁጭ ብለን ወጪያችንን አሰላን።”

ጃንፒዬሮ እና ግሎሪያ

በጥንቃቄ ዕቅድ አውጥተዋል

 ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው ማገልገል የሚፈልጉ ክርስቲያኖች አስቀድመው በጥንቃቄ ማቀድና ማስተካከያዎችን ማድረግ አለባቸው። (ሉቃስ 14:28) ለምሳሌ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት መንገድ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ግዌን እዚያው እንግሊዝ እያለች ገንዘብ ለማጠራቀም ስትል ከእህቷ ጋር መኖር ጀመረች። በእንግሊዝ ይኖሩ የነበሩት ሶፊያ እና ክሪስቶፈርም እንዲህ ብለዋል፦ “መኪናችንንና አንዳንድ የቤት ዕቃዎቻችንን ሸጥን። በአልባኒያ ቢያንስ አንድ ዓመት መቆየት ፈልገን ነበር።” ደስ የሚለው፣ በዚያ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየት ችለዋል።

ክሪስቶፈር እና ሶፊያ

 አንዳንድ አስፋፊዎች በአልባኒያ ለተወሰኑ ወራት ከቆዩ በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ሥራ በመሥራት ገንዘብ ያጠራቅማሉ። ከዚያም ወደ አልባኒያ ይመለሳሉ። ኤሊዚዮ እና ሚርያም የሚያደርጉት እንዲህ ነበር። ኤሊዚዮ እንዲህ ብሏል፦ “ሚርያም ያደገችው ጣሊያን ውስጥ በሚገኝ የቱሪስት መዳረሻ ነው። በዚያ አካባቢ ጊዜያዊ ሥራ ማግኘት በጣም ቀላል ነው። በበጋ ወቅት ወደዚያ ሄደን ለሦስት ወራት እንሠራለን። ከዚያም ባጠራቀምነው ገንዘብ የቀሩትን ዘጠኝ ወራት አልባኒያ እንኖራለን። ለአምስት ዓመታት በዚህ መልኩ ኖረናል።”

ሚሪያም እና ኤሊዚዮ

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም

 ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ብለው ወደ ሌላ አካባቢ የሚዛወሩ ክርስቲያኖች አዳዲስ ሁኔታዎችን መልመድ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም በሄዱበት አካባቢ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጧቸውን ምክር በመስማትና ምሳሌነታቸውን በማየት ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት ችለዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሶፊያ እንዲህ ብላለች፦ “የአልባኒያ ክረምት ካደግኩበት አካባቢ የከፋ ነው፤ ቤቱ በጣም ይቀዘቅዛል። ስለዚህ የአካባቢውን እህቶች አለባበስ በማየት አለባበሴን አስተካከልኩ።” ግዤጎዥ እና ባለቤቱ ሶና የመጡት ከፖላንድ ሲሆን የሚያገለግሉት በኮሶቮ በምትገኘው ፕሪዝረን የተባለች ውብ ከተማ ውስጥ ነው። b ግዤጎዥ እንዲህ ብሏል፦ “በአካባቢው ያሉ አስፋፊዎች በጣም ትሑት፣ ደግና ታጋሽ ናቸው። ቋንቋውን እንዲሁም ሌሎች ብዙ ነገሮችን እያስተማሩን ነው። ለምሳሌ በርካሽ ዋጋ ዕቃዎችን መግዛት የምንችልባቸውን ሱቆች አሳይተውናል። እንዲሁም ገበያ ወጥተን አስቤዛ መግዛት የምንችልበትን መንገድ ነግረውናል።”

ለደስታ የሚያበቁ ብዙ ምክንያቶች

 ወደ ሌላ አገር የሚዛወሩ ክርስቲያኖች በአካባቢው ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የቅርብ ወዳጅነት የመመሥረትና ተሞክሯቸውን የማወቅ አጋጣሚ ያገኛሉ። ሶና እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ ፍቅር ምን ያህል ኃይል እንዳለው ተመልክቻለሁ። ወንድሞች ስለ ይሖዋ በተማሩበት ወቅት እምነታቸውንና አኗኗራቸውን ሙሉ በሙሉ እንደቀየሩ መመልከቴ እምነቴን አጠናክሮታል። በጉባኤው ውስጥ ተፈላጊ እንደሆንንና ቦታ እንዳለን ይሰማናል። አብረውን የሚያገለግሉት ወንድሞችና እህቶች ጓደኞቻችን ሆነዋል።” (ማርቆስ 10:29, 30) ግሎሪያ እንዲህ ብላለች፦ “በማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚጠሉ ሰዎች መራራ ተቃውሞ የደረሰባቸው ብዙ እህቶች አውቃለሁ። ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር ሳይ ልቤ በጥልቅ ይነካል።”

ግዤጎዥ እና ሶና

 በሌላ አገር የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች በአገራቸው ቢሆኑ ኖሮ የማያገኟቸውን ትምህርቶች የመማር አጋጣሚ አግኝተዋል። ለምሳሌ ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል ሲሉ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር ደስታ እንደሚያስገኝ ተምረዋል። ስቴፋኖ እንዲህ ብሏል፦ “አገሬ እያለሁ አብዛኛውን ጊዜ የምሰብከው በኢንተርኮም ነበር፤ የምጠቀመውም አጫጭር መግቢያዎችን ነው። አልባኒያውያን ግን ቡና ፉት እያሉ ረዘም ያለ ሰዓት ማውራት ይወዳሉ። በጣም ዓይናፋር ስለሆንኩ መጀመሪያ አካባቢ እንዴት እንደማወራ ግራ ገብቶኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ለሰዎች ትኩረት መስጠትን ተማርኩ። አሁን ከሰዎች ጋር ማውራት ያስደስተኛል። አገልግሎቴ ከቀድሞ ይበልጥ አርኪ ሆኖልኛል።”

አሊዳ እና ስቴፋኖ

 ሊያ እና ባለቤቷ ዊልያም ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ አልባኒያ ተዛውረዋል። ሊያ እንዲህ ብላለች፦ “እዚህ ማገልገላችን አመለካከታችንን እና እይታችንን አስፍቶልናል። ስለ እንግዳ ተቀባይነት፣ ስለ አክብሮትና ስለ ጓደኝነት ብዙ ትምህርት አግኝተናል። መስበክ፣ ጥቅሶችን ማብራራትና ሐሳባችንን መግለጽ የምንችልባቸውን አዳዲስ መንገዶች ተምረናል።” ዊልያም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አልባኒያን የሚጎበኙ ብዙ ሰዎች ውብ የሆኑትን የባሕር ዳርቻዎች ሲያዩ በጣም ይደሰታሉ። እኔ በበኩሌ በአልባኒያ የሚገኘውን የአልፕስ ተራራ መውጣት በጣም ያስደስተኛል። ከአልባኒያ በጣም የምወደው ግን ሰዎቹን ነው። በክልላችን ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ መንደሮች ምሥራቹ የሚደርሳቸው በልዩ ዘመቻዎች ወቅት ብቻ ነው። ወደ እነዚያ አካባቢዎች ስንሄድ አንዳንድ ጊዜ ከጥቂት ቤተሰቦች ጋር በመወያየት ብቻ ሙሉ ቀን እናሳልፋለን።”

ዊልያም እና ሊያ

 ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረው የሚያገለግሉ አስፋፊዎች ከሁሉ የላቀ ደስታ የሚያስገኝላቸው ሰዎች ምሥራቹን ሲቀበሉ ማየት ነው። (1 ተሰሎንቄ 2:19, 20) በወጣትነቷ ወደ አልባኒያ የተዛወረችው ሎራ እንዲህ ብላለች፦ “ለተወሰነ ጊዜ ያህል በፊዬር ከተማ አገልግዬ ነበር። በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ 120 አዳዲስ ሰዎች ለሌሎች ለመስበክ ብቃቱን አሟሉ፤ ከእነዚህ መካከል 16ቱ የእኔ ጥናቶች ነበሩ!” ሳንድራ የተባለች ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ገበያ ውስጥ ለምትሠራ አንዲት ሴት መሠከርኩ። ይህች ሴት የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ ወደተወለደችበት መንደር ተመለሰች። ለመጨረሻ ጊዜ በተነጋገርንበት ወቅት 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዳስጀመረች ነግራኝ ነበር።”

ሎራ

ሳንድራ

ይሖዋ ጽናታቸውን ባርኮላቸዋል

 ከበርካታ ዓመታት በፊት ወደ አልባኒያ የተዛወሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሁንም እዚያው እያገለገሉ ነው፤ በአገልግሎታቸውም በጣም ደስተኞች ናቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች የዘሩት ዘር ከዓመታት በኋላ ፍሬ ሲያፈራ ሲመለከቱ በጣም ይደነቃሉ። (መክብብ 11:6) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ክሪስቶፈር እንዲህ ብሏል፦ “ወደ አልባኒያ ልክ እንደተዛወርኩ አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያስጀመርኩትን ሰው ከጊዜ በኋላ አገኘሁት። መጀመሪያ አካባቢ ያደረግናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶች በዝርዝር ማስታወሱ በጣም አስገረመኝ። አሁን እሱና ባለቤቱ የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ፌደሪካም እንዲህ ብላለች፦ “ወደ አንድ ጉባኤ ስሄድ አንዲት እህት ወደ እኔ መጥታ አስታውሳት እንደሆነ ጠየቀችኝ። ከዘጠኝ ዓመታት በፊት መሥክሬላት እንደነበር ነገረችኝ። ለካ ወደ ሌላ ከተማ ከተዛወርኩ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር፤ ከዚያም እድገት አድርጋ ተጠመቀች። አልባኒያ ከመጣን በኋላ ባሉት የመጀመሪያ ዓመታት አገልግሎታችን ፍሬያማ እንዳልሆነ ይሰማኝ ነበር። ግን ለካ ተሳስቻለሁ!”

 ወደ አልባኒያ እና ወደ ኮሶቮ የተዛወሩ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋ ጥረታቸውን ስለባረከላቸው እንዲሁም አርኪ የሆነ ሕይወት ስለሰጣቸው አመስጋኝ ናቸው። ኤሊዚዮ በአልባኒያ ለበርካታ ዓመታት ካገለገለ በኋላ ተሞክሮውን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጸው እንዲህ ብሏል፦ “እኛ ሰዎች ዓለም አስተማማኝ አድርጎ የሚቆጥራቸውን ነገሮች ካገኘን ሕይወታችን አስተማማኝ እንደሚሆን ማሰብ ይቀናናል። ሆኖም ይህ ቅዠት ነው። በሌላ በኩል ግን የይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕይወታችን ዓላማ ያለውና አስተማማኝ እንዲሆን ይረዱናል። ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገሌ ይህን ለማስታወስ ይረዳኛል። ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደማበረክትና ዋጋ እንዳለኝ ይሰማኛል። ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ግብ ያላቸው እውነተኛ ጓደኞች አሉኝ።” ሳንድራም ተመሳሳይ ሐሳብ አላት፤ እንዲህ ብላለች፦ “ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ በተዛወርኩበት ወቅት ይሖዋ ለረጅም ጊዜ የነበረኝን ሚስዮናዊ የመሆን ምኞት እንዳሳካልኝ ተሰማኝ። ወደ አልባኒያ በመምጣቴ ተቆጭቼ አላውቅም። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ደስተኛ ነኝ።”

a በአልባኒያ ስለተካሄደው የስብከቱ ሥራ ታሪክ ለማንበብ የ2010 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍን ተመልከት።

b ኮሶቮ የምትገኘው ከአልባኒያ በስተ ሰሜን ምሥራቅ ነው። ኮሶቮ ውስጥ የአልባኒያ ቀበልኛ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች አሉ። በአልባኒያ፣ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ኮሶቮ ውስጥ ላሉ የአልባኒያ ቀበልኛ ተናጋሪዎች ለመስበክ ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። በ2020 በስምንት ጉባኤዎች፣ በሦስት ቡድኖችና በሁለት ቅድመ ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 256 አስፋፊዎች ነበሩ።