መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የሚያገለግል የሕዝብ ስልክ
ዳያኒ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ የሆነች በብራዚል የምትኖር የይሖዋ ምሥክር ናት። አንድ ቀን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በስልክ እየሰበከች ሳለ፣ ፍላጎት ካሳዩ አንድ ወጣት ባልና ሚስት ጋር ተወያየች። ባልና ሚስቱ ኤሌክትሪክም ሆነ ኢንተርኔት ወደሌለበት ርቆ የሚገኝ አካባቢ ሊዛወሩ እንደሆነ ለዳያኒ ነገሯት። በዚያ ላይ ደግሞ በአካባቢው አንድም የይሖዋ ምሥክር የለም። ባልና ሚስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይታቸውን መቀጠል ስለፈለጉ ዳያኒ በመንደሩ ውስጥ ወዳለው የሕዝብ ስልክ ደውላ እንድታገኛቸው ስልክ ቁጥሩን ሰጧት፤ ከዚያም የሚወያዩበትን ቀንና ሰዓት ወሰኑ።
በተባባሉበት ሰዓት ዳያኒ የሕዝብ ስልኩ ላይ ስትደውል ባልና ሚስቱ አነሱ! ከዚያ በኋላ ባሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሦስት ጊዜ በስልክ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አደረጉ።
በኋላ ግን ዳያኒ ባልና ሚስቱን ልታገኛቸው አልቻለችም። በዚህ ተስፋ ሳትቆርጥ በሳምንት ሦስት ጊዜ የሕዝብ ስልኩ ላይ መደወሏን በመቀጠል ስልኩን ለሚያነሳው ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትናገር ነበር። በውጤቱም በመንደሩ ውስጥ ካሉ በርካታ ሰዎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጀመር ቻለች።
አንድ ቀን ዳያኒ እና ባሏ በሕዝብ ስልኩ ከአንድ ወጣት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ ሳሉ በመንደሩ ያለ የቤተ ክርስቲያን መሪ ውይይታቸውን ሰማ። የሚወያዩት ነገር በደንብ እንዲሰማው ስለፈለገ መጽሐፍ ቅዱስን እያጠና ወደነበረው ወጣት ጠጋ ብሎ ቆመ። ከዚያም ዳያኒን እና ባለቤቷን ማነጋገር ይችል እንደሆነ ጠየቀ። የሰማው ነገር በጣም ስላስደሰተው እሱም መጽሐፍ ቅዱስን መማር እንደሚፈልግ ገለጸ!
በጊዜ ሂደት ዳያኒ እና ባለቤቷ በዚያ ርቆ የሚገኝ መንደር ውስጥ የቤተ ክርስቲያን መሪውን ጨምሮ ከስድስት ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ከጥናቶቻቸው መካከል አንዳንዶቹ ያንኑ የሕዝብ ስልክ በመጠቀም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችንን ተከታትለዋል። እንዲያውም አንዱ ጥናታቸው አግዳሚ ወንበር ሠርቷል፤ ወንበሩን የሠራው ጥናቶች በጥናታቸው ወቅት እንዲቀመጡበት ነው።
ዳያኒ እና ባለቤቷ በዚህ ርቆ የሚገኝ መንደር የመንግሥቱን መልእክት ማድረስ የሚችሉበት አጋጣሚ በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው። ዳያኒ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሰው የሚኖረው በጣም ርቆ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ምሥራቹ እንዲደርሰው ሁኔታዎችን ያመቻቻል።”