ከ165,000 በላይ የጽሑፍ ጋሪዎች
የይሖዋ ምሥክሮች በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁት ከቤት ወደ ቤት በመሄድ በሚያካሂዱት የስብከት ሥራ ነው፤ አሁን ደግሞ በአደባባይ ላይ ማራኪ ከሆኑ የጽሑፍ መደርደሪያዎች አጠገብ ቆመው ማየት እየተለመደ መጥቷል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ ዓይነቱ የስብከት ዘዴ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። ኅዳር 2011 የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በጽሑፍ መደርደሪያ ጠረጴዛዎችና ጋሪዎች አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች ማሳወቅ ጀመሩ። ይህ ዘዴ በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ሌሎች ከተሞችም በፍጥነት ተስፋፋ።
እስከ መጋቢት 2015 ድረስ 165,390 ጋሪዎች በዓለም ዙሪያ ወደሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ተልከዋል። በተጨማሪም በሺህ የሚቆጠሩ መደርደሪያዎች፣ ጠረጴዛዎችና ኪዮስኮች ተሰራጭተዋል።
አሁንም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች የሚያሳውቁበት ዋነኛው መንገድ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የሚከናወነው የስብከት ሥራ ነው። ይሁንና የጽሑፍ ጋሪዎችን ተጠቅሞ መስበክ በጣም ውጤታማ እየሆነ መጥቷል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ፔሩ ውስጥ ራውል የሚባል ሰው በጽሑፍ ጋሪ አጠገብ የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ አላቸው፦ “እስካሁን የት ነበራችሁ? ለሦስት ዓመታት ያህል የይሖዋ ምሥክሮችን ስፈልግ ነበር! ጋሪያችሁን ስመለከት አምላክን አመሰገንኩ።”
የይሖዋ ምሥክሮች ራውል ወደሚኖርበት አካባቢ እየሄዱ በተደጋጋሚ ይሰብኩ የነበረ ቢሆንም በሳምንቱ መሃልም ሆነ ቅዳሜና እሁድ ራውልን ቤቱ አግኝተውት አያውቁም ነበር። ራውል ቀደም ሲል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና እንደነበረ ገልጾ አሁን ጥናቱን መቀጠል እንደሚፈልግ ተናግሯል። በመሆኑም ጥናቱን መቀጠል የሚችልበት ሁኔታ ተመቻቸለት።
ቡልጋሪያ ውስጥ አንድ ወጣት ባልና ሚስት ከአንድ የጽሑፍ ጋሪ ላይ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ወሰዱ። በቀጣዩ ሳምንትም ተመልሰው በመምጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ እና ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተባሉትን ሁለት መጻሕፍት ወሰዱ። በዚያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ባልና ሚስቱን ምን ያህል ልጆች እንዳሏቸው ጠየቋቸው። “እስካሁን አልወለድንም፤ ስንወልድ ግን ልጆቻችንን ስለ አምላክ ማስተማር እንፈልጋለን። እንዲህ ያሉ መጻሕፍትን እንፈልግ ነበር” በማለት መለሱላቸው።
ዩክሬን ውስጥ የወታደር ልብስ የለበሰ አንድ ሰው በጽሑፍ ጋሪ አጠገብ ወደቆሙት የይሖዋ ምሥክሮች ጠጋ ብሎ “ልጆች፣ አርማጌዶን የሚመጣው መቼ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። ሰውየው በዩክሬን በነበረው ግጭት በንቃት ይሳተፍ ነበር። የዓለም ሁኔታ አርማጌዶን በቅርቡ እንደሚመጣ ያስገነዘበው ቢሆንም ‘አምላክ ቶሎ እርምጃ የማይወስደው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮበት ነበር። ወጣቶቹ ሴቶች፣ አምላክ በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ እስካሁን እጁን ያላስገባበት ጥሩ ምክንያት እንዳለውና በቅርቡ ግን ክፉዎችን በሙሉ እንደሚያጠፋ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሱ አስረዱት። ሰውየው መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ወሰደ።
በመቄዶንያ፣ አንድ ወጣት በጽሑፍ ጋሪ አጠገብ ለቆሙ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሔቶቻችንን አግኝቶ እንደሚያውቅ ገልጾ አሁን ግን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ እንደሚፈልግ ነገራቸው። ከዚያም በቀጥታ ወደ ቤተ መጻሕፍት ሄዶ መጽሐፉን ማንበብ እንደሚጀምር ገለጸላቸው።
ሰውየው ከሁለት ሰዓታት በኋላ ተመልሶ የመጣ ሲሆን ከመጽሐፉ ላይ 79 ገጾችን አንብቦ ነበር። “ይህ መጽሐፍ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል! ከማምንባቸው ትምህርቶች መካከል አብዛኞቹ የተሳሳቱ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ከዚህ መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት ሐሳብ በሙሉ ትክክል እንደሆነ ይሰማኛል። ስለ ሕይወት ያለኝን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ለውጦታል!”