የዎርዊክ ፎቶ ጋለሪ 7 (ከመስከረም 2016 እስከ የካቲት 2017)
ይህ የፎቶ ጋለሪ ከመስከረም 2016 እስከ የካቲት 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲሱ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የተከናወነውን የግንባታ ሥራ እንዲሁም ፈቃደኛ ሠራተኞች ይህን ሕንፃ እንዴት መጠቀም እንደጀመሩ ያሳያል።
መስከረም 8, 2016—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ
በዎርዊክ የሚገኙ ሕንፃዎች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በዎርዊክ የሚኖሩት ሰዎች ቁጥር 500 ገደማ ነበር። ይህ ቁጥር የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞችንና ከብሩክሊን የተዛወሩ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞችን ያካትታል።
መስከረም 20, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አንድ የሥዕል ባለሙያ “ለይሖዋ ስም የሚሆን ሕዝብ” የተባለው አውደ ርዕይ መግቢያ ግድግዳ ላይ የሚለጠፉትን የሚያንጸባርቁ ታይሎች ሲመረምር። ታይሎቹ ያረጁ መስለው እንዲታዩ ተደርጓል፤ ይህም ከአውደ ርዕዩ ታሪካዊ ጭብጥ ጋር ይስማማል።
መስከረም 28, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
ከዎርዊክ የተላለፈው የመጀመሪያው የማለዳ አምልኮ ፕሮግራም ሊቀ መንበር የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት ነበር። በዚያን ዕለት ጠዋት ወንድም ሌት በአዲሱ ሕንፃ የግንባታ ሥራ ላይ ለተሳተፉ ከ27,000 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞችና ፕሮጀክቱን በተለያዩ መንገዶች ለደገፉ ሌሎች በርካታ ሰዎች የተጻፈውን የምስጋና ደብዳቤ አንብቧል።
ጥቅምት 3, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አንድ የእንጨት ሥራ ባለሙያ ያለ አስጎብኚ ከሚታዩት ሦስት አውደ ርዕዮች መካከል በአንዱ መግቢያ ላይ የሚለጠፉትን ፊደሎች ሲደረድር። “ለይሖዋ ስም የሚሆን ሕዝብ” የሚል ርዕስ ያለው ይህ አውደ ርዕይ ከ1870ዎቹ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ ያሳያል።
ጥቅምት 5, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
የጽሑፍ ኮሚቴ አባላት ከረዳቶቻቸውና ከጽሑፍ ዝግጅት ክፍል አባላት ጋር ስብሰባ ሲያደርጉ። ክፍሉ ውስጥ የተገጠሙት ትላልቅ ስክሪኖች ወደፊት በሚወጡ ጽሑፎች ላይ እንዲካተቱ የታሰቡ ሥዕሎችን ለማሳየትና በስብሰባው ወቅት በሌሎች ሕንፃዎች ውስጥ ካሉ ዲፓርትመንቶች ጋር ለመነጋገር ያገለግላሉ። ከበርካታ ዓመታት በፊት በስጦታ የተገኘው በፎቶው ላይ የሚታየው ጠረጴዛ ቀደም ሲል ብሩክሊን የነበረ ሲሆን አሁን ወደ ዎርዊክ ተወስዷል።
ጥቅምት 20, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
የአስተባባሪዎች ኮሚቴ ረዳት የሆነ ወንድምና በዚሁ ኮሚቴ አመራር ሥር የሚሠሩ ሌሎች ወንድሞች ከአንድ ቀን በፊት ፊሊፒንስን መትቶ በነበረው ታይፉን ሃይማ (ላዊን) የተጠቁትን ሰዎች ሊረዱ ስለሚችሉበት መንገድ ሲወያዩ። የቪዲዮ ኮንፈረንስ ለማድረግ የሚያስችሉ መሣሪያዎች መገጠማቸው በዋናው መሥሪያ ቤት የሚገኙ ወንድሞች አስቸኳይ ጉዳዮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በፍጥነት መፍትሔ መስጠትና በመላው ዓለም ከሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር መነጋገር እንዲችሉ ይረዳቸዋል።
ጥቅምት 28, 2016—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ
በጥገና ሕንፃውና በዋናው መግቢያ መንገድ መካከል ያለ ውኃ የሚጣራበት ኩሬ። ይህ ኩሬና በዎርዊክ የሚገኙ ሌሎች ኩሬዎች የተፈጥሮ ዘዴዎችን በመጠቀም በዝናብ ውኃ ውስጥ የሚገኙትን በካይ ነገሮች ያጣራሉ፤ ይህም የተለመደው የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴ የሚጠይቀውን ወጪ 50 በመቶ ለመቀነስ አስችሏል። በተጨማሪም ውኃው ከታከመና ከተጣራ በኋላ በአካባቢው ወደሚገኙ ወንዞች እንዲገባ መደረጉ አካባቢው ለእንስሳትና ለዕፀዋት ጤናማ እንዲሆን ያደርጋል።
ኅዳር 4, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
ዕቃዎችን እንዲያጓጉዙ የተመደቡት ሠራተኞች በማራገፊያ ቦታው ላይ ጭነት ሲያወርዱ። የዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ከብሩክሊን ወጥተው በዎርዊክ ወደሚገኘው አዲሱ መኖሪያቸው በተዛወሩበት ወቅት ወደ 80 የሚጠጉ ሠራተኞች እርዳታ ሰጥተዋል።
ታኅሣሥ 14, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
ዳቦ ጋጋሪዎች በማቡኪያ ዕቃ ውስጥ ያለውን ሊጥ አውጥተው ጠረጴዛ ላይ ሲያስቀምጡ። ሊጡ ከ45 ኪሎ ግራም በላይ ይመዝናል፤ በመሆኑም የማቡኪያ ዕቃውን በቀላሉ ለማንሳትና ሊያጋጥም የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የማንሻ መሣሪያ ተገጥሟል። በተጨማሪም የዎርዊክ ዳቦ መጋገሪያ ሙቀቱንና የአየር እርጥበቱን በመቆጣጠር ሊጡ የሚቦካበትን ጊዜ ለማራዘም አሊያም ለማሳጠር የሚያስችል የኮምፒውተር መቆጣጠሪያ የተገጠመለት መሣሪያ አለው። ይህ ራሱን በራሱ የሚቆጣጠር መሣሪያ በየሳምንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳቦዎችን ለመጋገር የሚጠይቀውን ድካም ይቀንሳል።
ታኅሣሥ 14፣ 2016—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ
የሕንፃ አገልግሎት ሠራተኞች ከጥገና ሕንፃው ቆሻሻ ሲያስወግዱ። በዎርዊክ የሚገኙት ሕንፃዎች በብሩክሊን ከነበሩት ሕንፃዎች በተለየ እርስ በርሳቸው የተገናኙ በመሆናቸው ቆሻሻዎችንና መልሰው አገልግሎት ላይ ሊውሉ የሚችሉ ነገሮችን ለመሰብሰብ የሚያስፈልጉት ሠራተኞችና ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከድሮው ያነሰ ነው።
ታኅሣሥ 14, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አንድ ሸሚዝ ውኃ ከተረጨበት በኋላ በመተኮሻ መሣሪያ ሲተኮስ። በዎርዊክ የሚገኘው የልብስ ንጽሕና አገልግሎት መስጫ ክፍል በየሳምንቱ በአማካይ ከ5,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ልብስና አንሶላ ያጥባል። እነዚህን ልብሶች ለይቶ ወደመጡበት ቦታ ለመመለስ በልብስ ንጽሕና ክፍሉ ውስጥ የሚሠሩት ወንድሞች በኮምፒውተር የሚነበብ የመለያ ኮድ ይለጥፉባቸዋል። የተለጠፉት ኮዶች በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚነበቡ ሲሆን ይህም ልብሶቹ በተገቢው መንገድ መታጠባቸውንና ወደ ትክክለኛው ዲፓርትመንት ወይም የመኖሪያ ክፍል መመለሳቸውን ለማረጋገጥ ያስችላል።
ታኅሣሥ 20፣ 2016—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ
አንድ ሜካኒክ በኃይል ማመንጫ ክፍል ውስጥ ለሚሠራ ማንሻ መሣሪያ ፍተሻና ጥገና ሲያደርግ። እንዲህ ያለው ክትትል የመሣሪያዎቹ ዕድሜ እንዲረዝምና በተጠቃሚዎች ላይ አደጋ እንዳያደርስ ያስችላል።
ጥር 10, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አንድ ቴክኒሽያን “በተግባር የተደገፈ እምነት” በተባለው አውደ ርዕይ ላይ የሚታየውን ማስተዋወቂያ የሚቆጣጠር የኮምፒውተር አፕሊኬሽን ሲሠራ።
ጥር 11, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
የእንጨት ሠራተኞች በ1903 የተሠራ አንድ ብስክሌት “ለይሖዋ ስም የሚሆን ሕዝብ” በተባለው አውደ ርዕይ ላይ ለእይታ እንዲቀርብ ሲያዘጋጁ። በስጦታ የተገኘውና በዎርዊክ የሚገኙ ሠራተኞች በጥንቃቄ እድሳት ያደረጉለት ይህ ብስክሌት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለዋል) እንዲህ ባሉ መጓጓዣዎች ተጠቅመው የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሲያሰራጩ ምን ያህል ጥረትና ድካም ጠይቆባቸው እንደነበር ለማሳየት ያስችላል።
ጥር 12, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
የእንጨት ሠራተኞች “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ከተባለው ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የሚጠቀም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ፊልም ጋር በተያያዘ ለእይታ የሚቀርቡት ቁሳቁሶች የሚቀመጡበትን መስተዋት ሲገጥሙ። በ1914 መታየት የጀመረውን ይህን ፊልም በዚያ ዓመት ብቻ ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተመልክተውታል።
ጥር 12, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
ታሪካዊ ሰነዶችን የሚሰበስቡና ተጠብቀው እንዲቆዩ የሚያደርጉ ባለሙያዎችና አንዲት የሥነ ጥበብ ባለሙያ የዙሪክ ላቲን መጽሐፍ ቅዱስ የ1544 እትም “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም” በተባለው አውደ ርዕይ ላይ ለእይታ እንዲቀርብ ሲያዘጋጁ። ፊት ለፊት መጽሐፍ ቅዱሱ ላይ የሚታየው ቀይ ቀስት ይሖዋ የሚለው የአምላክ የግል ስም የሚገኝበትን ቦታ ይጠቁማል። እነዚህ ባለሙያዎች በቀላሉ ሊጎዱ ለሚችሉ መጽሐፍ ቅዱሶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ገጾቹ እንዳይጨራመቱ ከፖሊስተር የተሠራ እንደ ፕላስተር ያለ ነገር ይለጠፍባቸዋል እንዲሁም አውደ ርዕዩ የሚታይበት ክፍል የሙቀትና የአየር እርጥበት ቁጥጥር ይደረግበታል። በማሳያ መስተዋቶቹ ውስጥ ያሉት ፋይበር ኦፕቲክ መብራቶችም በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉት ወረቀቶች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ በጥንቃቄ ተስተካክለው የተገጠሙ ናቸው።
ጥር 16, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አስጎብኚ የተመደበላቸው ጎብኚዎች 23 ሜትር ከፍታ ካለው ማማ ላይ ሆነው ሙሉውን የዎርዊክ ሕንፃ ሲቃኙ። በቅድሚያ ተመዝግቦ ፕሮግራም ማስያዝን የሚጠይቀው ያለአስጎብኚ የሚደረገው የአውደ ርዕዮቹና የዎርዊክ ሕንፃዎች ጉብኝት የጀመረው ሚያዝያ 3፣ 2017 ነው። መጎብኘት የሚፈልጉ ሁሉ ድረ ገጻችን ላይ ገብተው ስለ እኛ > ቢሮዎች እና ጉብኝት በሚለው ሥር ቀጠሮ ማስያዝ ይችላሉ።
ጥር 19, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
ታሪካዊ ሰነዶችን የሚሰበስብና ተጠብቀው እንዲቆዩ የሚያደርግ አንድ ባለሙያ በቀላሉ የማይገኝን የኪንግ ጀምስ ቨርዥን የ1611 እትም መጽሐፍ ቅዱስ በማሳያ መስተዋቱ ውስጥ ሲያስቀምጥ። ማሳያዎቹ በዎርዊክ የሚገኙ ሠራተኞች ለዚሁ ዓላማ ያዘጋጇቸው ናቸው።
ጥር 19, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አንዲት የግራፊክ ሥነ ጥበብ ባለሙያ አንድን ባርኔጣ በማሳያ መስተዋት ውስጥ ስታስቀምጥ። ባርኔጣው ከ100 ዓመታት በፊት የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በበላይነት ይከታተል የነበረው የጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ነው። “ለይሖዋ ስም የሚሆን ሕዝብ” የተባለው አውደ ርዕይ ክፍል የሆነው ይህ ጋለሪ የይሖዋ ምሥክሮች በ19ኛው መቶ ዘመን የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ያደረጉትን ጥረት ያሳያል።
ጥር 20, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አንድ አንባቢ በድምፅ ቀረጻ ቡድኑ በመታገዝ “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም” በተባለው ያለአስጎብኚ የሚታይ አውደ ርዕይ ላይ የሚደመጠውን ንባብ ሲቀዳ። በብሩክሊን የነበረው የቀረጻ ክፍልና የቀረጻ መሣሪያዎቹ ተነቃቅለው ወደ ዎርዊክ በመጡ ከአንድ ሳምንት ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ የቀረጻ ስቱዲዮው ሥራውን ጀምሯል። ይህ ስቱዲዮ (በፓተርሰን የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል የሚገኙት ዋና የቀረጻ ስቱዲዮዎች ቅርንጫፍ ነው) አዲስ ዓለም ትርጉምን፣ መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም jw.org ላይ የሚወጡ ርዕሶችን ጨምሮ ሌሎች የኦዲዮ ቅጂዎችን ለመቅዳት ያገለግላል።
ጥር 27, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
የእንጨት ሥራ ባለሙያው ረዳት የሆነች አንዲት ሠራተኛ የፎቶግራፍ ማሳያውን ጠርዞች ቀለም ስትቀባ። “ለይሖዋ ስም የሚሆን ሕዝብ” የተባለው አውደ ርዕይ ክፍል የሆነው ይህ ማሳያ በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ታሪካዊ ፎቶግራፎች ያሳያል።
የካቲት 15, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አንዲት የሥነ ጥበብ ባለሙያ የይሖዋ ወዳጅ ሁን በተባለው ተከታታይ ቪድዮ ላይ የሚታየውን የካሌብን ገጸ ባሕርይ ምስል ቀለም ስትቀባ። ይህ ሞዴል የይሖዋ ምሥክሮች በተለይ ልጆችን ለማስተማር ብለው ያዘጋጇቸው ጽሑፎችና ፕሮግራሞች በሚታዩበት ጋለሪ ውስጥ ይቀመጣል።
የካቲት 15, 2017—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች
አንድ የእንጨት ሥራ ባለሙያ “ለይሖዋ ስም የሚሆን ሕዝብ” በተባለው አውደ ርዕይ ላይ የሚታዩ ፎቶግራፎችንና በፕላስቲክ የተጻፉ ፊደሎችን ሲቆራርጥ። የእንጨት ሥራ ባለሙያዎችን፣ የኮምፒውተር ፕሮግራመሮችን፣ ዲዛይነሮችን፣ የኤሌክትሪክ ባለሙያዎችን፣ ወለል የሚያነጥፉ ሠራተኞችን፣ የቪዲዮ ቀረጻ ባለሙያዎችንና ጸሐፊዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ250 የሚበልጡ ሠራተኞች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ከሦስቱ አውደ ርዕዮች ጋር በተያያዙ ሥራዎች ተካፍለዋል።