በአትላንታ ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገላቸው
“የድርጅታችሁ አባላት የአምላክን መንግሥት ለማገልገል ያላቸውን ፍላጎትና ጉጉት በጣም አደንቃለሁ። የይሖዋ ምሥክር ለሆኑ ሰዎችም ሆነ ለማኅበረሰቡ የምታከናውኑትን የበጎ አድራጎት ሥራና የምታበረክቱትን አስተዋጽኦ ከፍ አድርገን እንደምንመለከትና በእጅጉ እንደምናደንቅ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።”
ይህን ደብዳቤ የጻፉት በዩናይትድ ስቴትስ ጆርጂያ ውስጥ የምትገኘው የአትላንታ ከንቲባ የሆኑት ካሲም ሪድ ናቸው። ደብዳቤው የተጻፈው በከተማይቱ ውስጥ በሚካሄዱት ሦስት ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አቀባበል ለማድረግ ነው።
በተመሳሳይም የአትላንታ ከተማ ምክር ቤት በስብሰባው ላይ የሚገኙ ልዑካንን ለመቀበል አንድ መግለጫ አውጥቶ ነበር። መግለጫው እንዲህ ይላል፦ “በዓለም ዙሪያ፣ የተለያየ ዘር ያላቸውና የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ስምንት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ፤ ይሁንና አንድ የሚያደርጉ የጋራ ግቦች አሏችሁ፤ . . . የሁሉ ነገር ፈጣሪ የሆነውንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን አምላክ ይኸውም ይሖዋን ማክበር [ትፈልጋላችሁ።]”
በዚህች ከተማ ውስጥ በሐምሌና በነሐሴ 2014 ሦስት ትላልቅ ስብሰባዎች ተካሂደዋል፤ ሁለቱ ስብሰባዎች የተካሄዱት በእንግሊዝኛ ሲሆን አንደኛው ደግሞ በስፓንኛ ነው። በስብሰባው ላይ ቢያንስ ከ28 አገሮች የመጡ ልዑካን ተገኝተዋል፤ ራሽያኛ እና ጃፓንኛ የሚናገሩ ልዑካንን ለመርዳት ሲባል በእንግሊዝኛ የቀረቡት ፕሮግራሞች በቀጥታ በእነዚህ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በአጠቃላይ በእነዚህ ሦስት ስብሰባዎች ላይ የተገኙት ሰዎች ብዛት 95,689 ነበር።
በ2014 የይሖዋ ምሥክሮች በዩናይትድ ስቴትስ በተለያዩ ቦታዎች የተካሄዱትን 16 ስብሰባዎች ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በዘጠኝ አገሮች 24 ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች አድርገዋል።